በደብረ ብርሃን ከተማ 12 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 130 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጠ

0
343

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስድስት ወር ውስጥ ከ12 ቢሊዮን በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 130 ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደተሰጣቸው ተገለጸ።

በ2014 በጀት ዓመት በስድስት ወር ውስጥ 12 ቢሊዮን ካፒታል ያስመዘገቡት 130 የሚሆኑት ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠታቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳዳር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርሃን ገብረሕይወት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ባለሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ነው። ባለሀብቶቹ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች መካከል በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ 33፤ በኮንስትራክሽንና በኬሚካል ኢንዱስትሪ 26፤ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 10፤ በቱሪዝም ዘርፍ ኹለት፤ በእንጨትና ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ 25፤ በሌሎች 12 እንዲሁም በተጨማሪ በማኑፋክቸሪንግ እና በሆቴል ዘርፍ መሆኑን ብርሃን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ኃላፊው ብርሃን በተያያዘ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ብዛት ከ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በቁጥር የ20 ባለሀብቶች ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

በ2013 በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ለኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ብዛት 150 የነበረ ሲሆን፤ በ2014 በጀት ዓመት በስድስት ወር ውስጥ ደግሞ 130 ባለሀብቶች በመሆናቸው በቁጥር በ20 ቅናሽ ማሳየቱን ነው ኃላፊው ጠቁመዋል።
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል የሚሉት ብርሃን፤ ለችግሩ መንስኤ ደብረ ብርሃን ከተማ በኹለት ወራት ውስጥ ባለሀብቶቹ አትኩሮታቸው በጦርነት ጉዳይ ላይ ስለነበር ነው ብለዋል።

የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘታቸው ለሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፤ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ለ25 ሺሕ 489 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ብርሃን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በ2013 በጀት ዓመት ለኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ያስመዘጉቡት ካፒታል ከዘንድሮው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሦስት ቢሊዮን ቅናሽ ዐሳይቷል ነው የተባለው።

ይህን በተመለከተም ኃላፊው በ2013 የተመዘገበው ካፒታል 15 ቢሊዮን ብር እንደነበር ገልጸው፤ በ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ደግሞ 12 ቢሊዮን ብር በላይ ቢመዘገብም የሦስት ቢሊዮን ብር ቅናሽ ዐሳይቷል ሲሉ ነው ያብራሩት።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳዳር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት በ2013 በጀት ዓመት በገለጸው የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም፤ 24 ፋብሪካዎች ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ቢጠናቀቅና ማሽን ቢገጠምላቸውም ወደ ሥራ እንዳልገቡ፤ እንዲሁም “ከሰብስቴሽን” ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮች የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ባለመዘርጋቱ ከ10 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ፋብሪካዎች ሥራ እንዳልጀመሩ ጠቁሞ ነበር።

ይህን በተመለከተም አዲስ ማለዳ ጉዳዩ ከምን ደረሰ? ስትል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፤ ብርሃን ገብረሕይወት ወደ ሥራ አልገቡም ተብለው የነበሩት 24 ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ባይባልም ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል። ለአብነትም በጋርመንት፤ በብረታ ብረት እና በሌሎች አገልግሎት ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ መብራት የሚጠብቁና ገና ማሽን አዝዘው ያላስገቡ ፋብሪካዎች መኖራቸውንም ኃላፊው አልደበቁም።

ከ10 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉና ‹አልተጠናቀቁም› ተብለው የነበሩ ፋብሪካዎችን በተመለከተም አሁንም ‹ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም። የተወሰነው ግን ተጠናቋል› ሲሉ ነው አክለው ያብራሩት።

ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው የሚሉት ብርሃን፤ ዋነኛው ችግር ከመብራት ‹‹ሰብስቴሽኑ›› እስከ ኢንዱስትሪው ድረስ ያለው የመስመር ዝርጋታ ክፍተት ነበር ብለዋል። ወደ 92 የሚሆኑ ፋብሪካዎችን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ የመብራት ፖሎች መተከላቸውን ተናግረው ገመዱ ሲቀጠል ችግሩ እንደሚቀረፍ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here