የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሪል ስቴት ልማት እና ግብይትን የሚቆጣጠር ዐዋጅ ማዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያዘጋጀው የሪል ስቴት ልማት ዐዋጅ፣ በሪል ስቴት አልሚዎች እና ተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ እና አሠራሩን በሕግ የተደገፈ ለማድረግ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ታደሰ ከበበ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም እስካሁን በሕግ ማቀፍ የተደገፈ የሪል ስቴት ልማት ሥርዓት አለመኖሩን የገለጹት ታደሰ፣ ዘርፉ በሕግ ባለመመራቱ በአልሚዎችና በገዥዎች መካከል የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ መስተዋሉን ጠቁመዋል።
የሪል ስቴት አልሚዎችን በወጥነት መምራትና መቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ተከትሎ፣ በአልሚዎች እና በገዥዎች መካከል አለመተማመን እና የማጭበርበር ኹኔታዎች ማጋጠማቸው ተገልጿል። ከዚህ በፊት ከቤት ገዥዎች ብር ሰብስበው የሚጠፉ የሪል ስቴት አልሚዎች ማጋጠማቸውን የገለጹት ታደሰ፣ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሪል ስቴት ልማት ዐዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የቤቶች ልማት አስተዳደር ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የተዘጋጀው ዐዋጅ በፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ አስተያየት ተሰጥቶበት ረቂቁ መጠናቀቁን ጠቁመዋል። ዐዋጁ ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር መሠረት ክለሳ ማድረግ በማስፈለጉ ክለሳ እንደተደረገበት ተናገረዋል። ረቂቅ ዐዋጁ የተጠናቀቀ መሆኑን ተከትሎ ለሚመለከተው አካል ተመርቶ በተያዘው በጀት ዓመት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ዐዋጁ መሠረታዊ የሆኑ የሪል ስቴት ልማት ጉዳዮች ላይ የሕግ ማዕቀፍ የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ማልማት የሚችለው አካልም ምን ማሟላት እንዳለበት እና ሪል ስቴት አልሚ ለመባል ምን ያክል ቤት መገንባት እንዳለበት ይደነግጋል ተብሏል። ከዚህ በፊት በዘፈቀደ መሬት ያለው ወይም ገንዘብ ያለው አካል የሪል ስቴት አልሚ የሚሆንበትን ኹኔታ ያስቀራል የተባለው ዐዋጅ፣ በዐዋጁ ከሚደነገገው አሠራር ውጪ የሚከናወኑ የሪል ስቴት ልማቶች ላይ ገደብ እንደሚጥል ተመላክቷል።
ረቂቅ ዐዋጁ አልሚዎች እና በመንግሥት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በማጠናከር በኢትዮጵያ የሚታየውን የቤት ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ተብሎለታል። ዐዋጁ በሪል ስቴት ልማት ላይ የመንግሥት ድጋፍ እና የአልሚዎች ትብብር የሚጨምር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በከተሞች የሚታየውን የቤት ችግር ለመቅረፍ፣ ቤቶችን በመንግሥትና በግል ትብብር (public & private partnership) ለማልማት ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
የሪል ስቴት ልማት ዐዋጁ በሪል ስቴት ግብይት ላይ መሠረታዊ የሕግ ማዕቀፎችን የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ አልሚዎች ከቤት ፈላጊዎች የሚያስከፍሉትን ቅድመ ክፍያ ላይ በሕግ የተደገፈ አሠራር ይዘረጋል ተብሏል። እስካሁን ያለው የቅድመ ክፍያ አፈጻጸም በሕግ ማዕቀፍ ያልተደገፈ እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ መሆኑን ታደስ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በመንግሥት የሚለሙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቤት ፈላጊውን ፍላጎት እያሟሉ ባለመሆኑ፣ በዘርፉ ላይ በመንግሥትና በግል ትብብር ቤቶችን ማልማት እንደሚያስፈልግ እና የውጭ ባለሀብቶችን በቤት ልማት ላይ መሳብ እንደሚገባ ታደሰ ጠቁመዋል።
ተጨማሪ ጽሁፎች
የብሔራዊ ባንክ መመሪያ አክስሮናል ሲሉ የሪልስቴት አልሚዎች ቅሬታ አቀረቡ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



