እንተባበር!

0
699

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ዘመኑ የሥልጣኔ እንደመሆኑ፣ ቴክኖሎጂውም ለመቀራረብና አብሮ ለመሥራት ምቹ እንደመሆኑ የሴቶች መብትና ተሳትፎ ላይ የሚሠሩ ሊተባበሩ የሚገባበት ጊዜ ላይ ነን። በደል ሲፈጸምበትም ሆነ ዕኩል ሳይታይ ቀርቶ ተጠቃሚነቱ ዝቅተኛ የነበረ የሕብረተሰብ ክፍል፣ እኩል እንዲሆን መሥራት ያለበት ተበደልኩ ወይም አነስኩ የሚለው ወገን ብቻውን መሆን የለበትም።

ከሥርዓተ ፆታ ጋር በተገናኘ የሚፈፀሙ መድሎዎችንም ሆኑ በሴት ላይ የሚፈጸምን በደል ለማስቀረት፣ ሴቶች ብቻቸውን ያን ያህል ውጤታማ መሆን ስለሚያስቸግራቸው ወንዶችም በዕኩል በተግባሩ ላይ ቢያካፍሉ መልካም ነው። በሴቶች ጉዳይ የሚካሄዱ ሥልጠናዎች ላይም ሆነ በሥራ መስክ ተቀጥረው እንዲሠሩ ሴቶችን ብቻ መምረጡ እነሱን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ቢሆንም፣ መብት ነፋጊዎቹ ቁጥራቸው እንዲቀንስ ወንዶቹን ማካተትም ይጠቅማል።

የወንዱን አስተሳሰብ የበለጠ ወንድ ስለሚረዳና የሚያደርገውን ነገር ለምን እንደሚያደርገው የተሸለ ስለሚገነዘብ ኢ-ፍትሓዊ ነገሮችን ለማስቀረትም ሆነ ለመቀነስ ወሳኝ ይሆናል። በዳይ የሚባለው ወገን አካል የሆነ ሰው አንበድላቸው ቢል፣ አትበድሉን ብላ በጅምላ ከምትናገር ሴት በላይ ተቀባይነት እንደሚኖረው የሚናገሩ አሉ።

ይህ አይነት የማስተማሪያም ሆነ የማቀቢያ መንገድ በወንዶች የበላይነት ተይዟል በሚባለው ዓለማችን ላይ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ መንገድ መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ጉዳዩ የሴቶች ብቻ ባለመሆኑም፣ እነሱ እኩል ተጠቃሚ ቢሆኑ አገር ብሎም ዓለማችን እኩል ታድጋለች ብሎ መገንዘብ ከኹሉም ይጠበቃል።
ሰውን ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት በፆታም ሆነ በቀለምና በዘር እየለያዩ መፈረጁ ተገቢ ባለመሆኑም፣ ኢ-ፍትሓዊ ተግባር ተፈፅሟል ብሎ የሚያምን ማንም ቢሆን ትግሉን እንዲቀላቀል ማስቻል ይጠበቃል።

ሴቶች በፆታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው መድሎና በደል በርካታ ቢሆንም፣ ካለፉት 100 ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ እንደመጣ ይነገራል። በአንዳንድ ማኅበረሰብ ዘንድ ኹነቱ ባለበት መሆኑ ባይካድም፣ በአብዛኛው ዘንድ መጠነኛም ቢሆንም ለውጥ መኖሩ ይታመናል። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ባህሉና የኢኮኖሚ አቅም ውስንነቱ እንቅፋት ሁኖ የተፈለገው ደረጃ ላይ ባይደረስም፣ እንደአጀማመሩ ውጤቱ አበረታች መሆኑን የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው።

የሴቶችን እኩልነት ለማምጣት ገና ብዙ መሠራት ያለባቸው ተግባሮች ቢቀሩም፣ ራሱ ወንዱ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲያፋጥነው ማድረጉ የበለጠ ውጤታማ እንደሚደርግ ዕሙን ነው። ከዚህ በበለጠም ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በተናጥል ከሚጥሩ፣ በመተባበር አቅማቸውን አንድ አድርገው ቢሠሩ ይበልጥ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን ይችላሉ። የጎንዮሽ መነቋቆርና መተማማቱን ትተው፣ ለጋራ አጀንዳ ልዩነታቸውን አቀራርበው ቢሠሩ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለሠው ልጆች በጎ ውጤትን ያስገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here