ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት በአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት ዕገዛ በአማራ ክልል ለአምስት ዓመት የሚቆይ የ6 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች ከፈፃሚ አካላት ጋር መፈራረሙ ተገለጸ፡፡
ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በነበረው ፕሮግራም፣ በተለያዩ ዘርፎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲፈጽም እንዲሁም፣ የተለያዩ የጤናና የትምህርት ተቋማት ግንባታ ሲሠራና ኹሉን አቀፍ የምግብ ዋስትና ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡
በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች ስለተጠኑ በድርጅቱ የሚፈጸሙ ፕሮጀክቶች በሕብረተሰቡ ፍላጎት መሠረት ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡
በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን እንዲችሉና በሒደትም ከድኅነት እንዲወጡ ለማድረግ ይሠራልም ነው የተባለው።
ድርጅቱ በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ መንግሥትን የመደገፍ ተግባራት እንደሚፈጽም ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ በሚሠራበት አካባቢ ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባና በክልሉ በርካታ ወረዳዎች በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የተጎዱ ስለሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የድጋፍ ተደራሽነት ማስፋት እንዳለባቸው ተጠይቋል፡፡
ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በሴቶች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በውኃ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በግብርና እና በሌሎችም ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ተነግሯል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014


