በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የኤሌክትሪክ አውቶቡስን ሥራ ላይ ለማዋል ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ማስታወቁ ተዘግቧል። ትራንስፖርት ቢሮው፣ በውጭና አገር ውስጥ ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ለአውቶቡስ ግዥ የሚውል ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እየሠራ ነውም ተብሏል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሠጡት አውቶቡሶች ሌሊት ባትሪያቸውን ሞልተው (ቻርጅ አድርገው) ቀኑን በሙሉ ያለምንም የጊዜ ብክነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይረዳል ነው የተባለው። አውቶቡሶቹ የሙከራ ትግበራ የሚደረግባቸው በሸገር እና አንበሳ አውቶቡሶች ሲሆን፣ ከሸጎሌ ዴፖ ቅርበት ያላቸው አራት ኮሪደሮች ልየታ መከናዎኑ ተዘግቧል።
የመጀመሪያው ኮሪደር ከአዲሱ ገበያ እስከ ቄራ ሲሆን፣ ኹለተኛው ኮሪደር መነሻውን ዊንጌት አድርጎ መዳረሻው አየር ጤና እንደሚሆን ነው የተነገረው። ሦስተኛው ኮሪደር ከለገሃር ተነስቶ መዳረሻው ድል በር ሲሆን፣ አራተኛው ኮሪደር ደግሞ ከአውቶቡስ ተራ እስከ አስኮ ይሆናል ተብሏል።
ከዴፖው ያላቸው ርቀት፣ ‹‹ከBRT›› ኮሪደሮች ጋር ያላቸው ትስስር እና ገበያ አካባቢዎች መሆናቸው ለኮሪደሮች የሙከራ ትግበራ መመረጥ እንደመስፈርት መቀመጡም ተጠቁሟል። በቀጣይ በከተማዋ ሌሎች ተጨማሪ ኮሪደሮችን በማጥናት የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ሥራ የሚከናወን መሆኑ ተብራርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014


