ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች 165.7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

0
591

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ በግማሽ ዓመቱ ሪፖርት ካቀረቡ 25 የልማት ድርጅቶች የምርት/አገልግሎት ሽያጭ ብር 165.7 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ብር 166.5 ቢሊዮን መገኘቱ ነው የተገለጸው።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የ74 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ ተመላክቷል። በትርፍ ረገድ ከታክስ በፊት ብር 22 ቢሊዮን ለማትረፍ ታቅዶ፣ ብር 29 ቢሊዮን በማትረፍ የዕቅዱ 133 በመቶ ስለተፈጸመ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ መብለጡን አሳውቋል።
በምንዛሬ ግኝት ረገድ 2.7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 2.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በመገኘቱ የዕቅዱን 91 በመቶ መፈጸሙንና ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ በ62 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት በ20 ተጠሪ የልማት ድርጅቶች ለ12,100 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በቋሚ፣ በኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ መደቦች በድምሩ ለ10,589 ዜጎች (7,757 ወንዶች እና 2,325 ሴቶች) የሥራ ዕድል ሊፈጠር መቻሉ በግምገማው ወቅት ተገልጿል።

በልማት ድርጅቶች አስተዳደር በዋና ዋናዎቹ አፈጻጸሞች በፕራይቬታይዜሽን አንጻር ለክልል እንዲተላለፉ የተደረጉ የአርባ ምንጭ እርሻ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካና የአባያ እርሻ ልማት የርክክብ ልዩነት ዋጋ ትመና መከናወኑ፣ ኢትዩ-ቴሌኮምን በከፊል እና ዐሥር የስኳር ፋብሪካዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዛወር በተያዘው ዕቅድ መሠረት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውም ተገልጿል።

የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ በግማሽ ዓመቱ ለአስተዳደሩ ተጠሪ በሆኑ የልማት ድርጅቶች አንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ 2.3 ቢሊዮን ብር የገንዘብ፣ የተለያዩ የቁሳቁስና የሙያ አገልግሎት ድጋፍ መደረጉ እንዲሁም፣ የልማት ድርጅቶች በየዓመቱ ከሚያገኙት ትርፍ ለመንግሥት የሚያስገቡትን በተመለከተ በ2ዐ14 በጀት ግማሽ ዓመት ብር 4.7 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 4.6 ቢሊዮን ገቢ መደረጉ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here