በኢትዮጵያ ውስጥ መፍትሔ ያላገኙና ከባድ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ በርካታ ችግሮች አሉ። ከረፈደ በኋላ መፍትሔው ቢቀርብ እንኳ፣ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንደሚባለው ኹሉ በጭራሽም ለመቀየር ዕድል የማናገኝባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ተትረፍርፈዋል። ለዚህም አብነት ይሆን ዘንድ በጦርነቱ ምክንያት ብቻ እንኳ የደረሠውን ችግር ማንሳት ይቻላል።
መንግሥት፣ የግል ባለሃብቶች፣ እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸው ባይካድም፣ የጦርነቱን ሠለባዎች ከችግሮቻቸው ለማውጣት የተቻለ ግን አይመስልም።
መንግሥት፣ ማኅበረሠቡን ከነዚህ ጦርነት ወለድ ችግሮች ለማላቀቅ ቅድሚያ ሠጥቶ ሊተገብራቸው ከሚገቡ ነገሮች ይልቅ፣ ቀስ ብለው ቢከወኑ ዕምብዛም ወደ ኋላ ሊጎትቱን የማይችሉ ክንዋኔዎች ላይ በማተኮር የተጋነነ በጀት ሲመድብና ወጭ ሲያደርግ ተስተውሏል።
ፋታ የማይሠጡ ማኅበራዊና አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ ሠትቶ መሥራት የመጀመሪያ ተግባር መሆን ሲገባው፣ ቀስ ተብሎ በሒደት ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ማተኮሩ ላይ በርካቶች ቅሬታቸውን ሲያነሱ ይደመጣል።
ለበርካቶች የቅሬታ መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ፣ ለዕድሳቱ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና ጥር 15/2014 ለምርቃት የበቃው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመዘጋጃ ቤት ሕንፃ ነው።
በ1957 እንደተሠራ የሚነገርለት ይህ የመዘጋጃ ቤት ሕንፃ ብዙ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ ዕድሳት የተደረገለት፣ ለተከታታይ ወራት በተካሔደ ጦርነት ዜጎቿ ለሕልፈተ ሕይወት በተዳረጉባት፣ ኢኮኖሚዋ በደቀቀባትና ብዙ መፍትሔ የተጠሙ ችግሮች ባሉባት ኢትዮጵያ ላይ ነው።
መዘጋጃ ቤቱ የታደሰው 2.2 ቢለዮን ብር ወጪ ተደርጎበት መሆኑን በምርቃቱ ዕለት ተገኝተው የነበሩ ባለሥልጣናት የተናገሩትን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ መሠንበታቸው አይዘነጋም።
ታዲያ በጉዳዩ ላይ ሲሠነዘር የነበረው የብዙኀኑ አስተያየትና ቅሬታ፣ በዕድሳቱ ጥራት ወይም አስፈላጊነት ላይ አልነበረም። አስተያየትና ቅሬታዎቹ የመነጩት ይህን ያህል ገንዘብ አውጥቶ አሁን ላይ ሕንጻ ከማደስና ከመገንባት ይልቅ፣ በዜጎች ላይ የደረሱ ጦርነት ወለድ ችግሮችን ቅድሚያ ሠጥቶ መፍታትና ሌሎች ነገሮችን ደረጃ በደረጃ ማከናወን መልካም ነው ከሚል ቅንነት ነው።
የመዘጋጃ ቤቱን ዕድሳት በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ “ያደስነው ሕዝባችንን ጭምር ነው። ድንግዝግዝ ከሆነ ከሚያራርቀን አስተሳሰብና ብልሹ አሠራር ርቀን ሕዝባችንን ባማረና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳየንበት ነው” ብለው ነበር።
ይህ የከንቲባዋ ንግግር፣ በከተማዋ የሚገኙና ችግር ያልደረሠባቸውን ሰዎች የሚያስደስት ቢመስልም፣ በጦርነቱ ምክንያት ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያላማከለ መሆኑ ለብዙዎች ቅሬታ መነሻ ሲሆን ተስተውሏል።
“ታደሰ” የተባለው የትኛው ሕዝብ ነው? በጦርነት ቤት ንብረቱ ተዘርፎ ችግር ላይ ያለው? በድርቅ ምክንያት መሠቃየት ከጀመረ ሠንበትበት ያለውና የውኃ መሳቢያ ፓምፕ እንኳ ማግኘት ያልቻለው? የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው ትምህርቱን ለመጀመር የተቸገረው? መጠለያ አጥቶ ጎዳና ላይ የወደቀው? ወይስ የትኛው ሕዝብ ነው? የሚሉ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች የሠሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ናቸው።
የመዘጋጃ ቤቱ ዕድሳትን በተመለከተም ከንቲባዋ፣ “የተሠራው ሥራ በጥልቀትና በውስብስብነቱ ስንመለከተው ይህ ታሪካዊ ሕንጻ መልሶ ተገነባ እንጂ ታደሰ አይገልጸውም” ሲሉ ተሠምተዋል።
ዘመን ተሻጋሪ ሕንፃዎችን መገንባትና ያረጁትን ማደስ ለአገር ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ዕሙን ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ሕንፃ ከማደስና ከመገንባት በፊት “የተደቀኑባቸውን ወቅታዊ ችግሮች ሊሻገሩ የሚችሉ ዜጎችን መገንባት” ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ብዙዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ከተማ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከመሬታቸው ለልማት በሚል ተነስተው ከ15 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ፣ ካሳም ሆነ ቤት ያልደረሳቸው ሰዎች ቅር መሠኘታቸውን በተለያየ የትስስር ገጾቻቸው ሲያስነብቡ ተስተውለዋል።
እንደ አብዛኛዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ ቅሬታቸው የመዘጋጃ ቤቱ ዕድሳት ላይ ሳይሆን ፋታ ሊሰጠው የማይችለው የእነርሱ ችግር ቅድሚያ አለማግኘቱ ላይ ነው።
ቅድሚያ መፍትሔን የሚሹ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች አፋጣኝ መፍትሔን የሚሹ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸው ለማንም የተደበቀ አይደለም። መፍትሔ እንደሚያሻቸው ታውቆ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ርብርብ ቢያደርጉባቸውም፣ ከማኅበረሰቡ ጀርባ አልላቀቅ ካሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከልም የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።
በሱማሌ ክልል በተከሠተ ድርቅ ምክንያት 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው፣ እንዲሁም 230 ሺሕ የሚሆኑ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ለሞት አደጋ መጋለጣቸውን ነዋሪዎቹ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማቶች ደጋግመው እየተናገሩ ይገኛሉ።
ሌላው፣ በጦርነቱ ቀጠና የነበሩ፣ አሁንም ቢሆን ዳግም ጦርነት በተከፈተባቸው የአፋርና አማራ ክልል አካባቢ ያሉ ሰዎችን፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ከዓመታት በላይ በኦነግ ሸኔ ጥቃት እየተሠነዘረብን ቢሆንም በመንግሥት በኩል መፍትሔ አልተሰጠንም የሚሉ ዜጎችን ችግር ማንሳት ይቻላል።
በሌላ በኩልም፣ አዲስ አበባ ከተማ መዘጋጃ ቤት መታደሱ ለሁላችንም መልካም ቢሆንም ቅድሚያ መፍትሔ ሊሠጠን ይገባ ነበር የሚሉት፣ ከዓመታት በፊት ከመሬታቸው ለልማት ሲነሱ መንግሥት ምትክ እንደሚሠጣቸው ቢያሳውቃቸውም ካሳና ቤት ያላገኙ፣ እንዲሁም የቤት ዕጣ ደርሷቸው ቤቱን ሠርተው ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ ያልቻሉና የብር ዕጥረት የገጠማቸው፣ በዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በ20/80 ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኙ አርሶ አደሮች መሬታቸው ለልማት ተብሎ ሲወሰድ፣ መንግሥት ቤቱን ሠርቶና አጠናቆ እንደሚሰጣቸው ቃል በገባላቸው መሠረት ለዓመታት ቢጠብቁም፣ ቤት እንዳልደረሳቸው፣ የደረሳቸውም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ የተሠጣቸው በመሆኑና በራሳቸው ለማጠናቀቅም የብር ዕጥረት ስላጋጠማቸው ቤታቸውን በሕገ ወጥ መንገድ የሚሸጡ ሰዎችም እንዳልጠፉ ስትዘግብ መቆየቷ ይታወቃል።
በጦርነቱ ምክንያት፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትና ኪሳራ ቀላል የማይባል እንደሆነና፣ ዳግም ለማቋቋም በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚያስፈልግ መንግሥት ራሱ በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጽ መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም።
በመሆኑም በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ የሠነበተው፣ በአንድ በኩል በድርቅ፣ በሌላ በኩል በርሃብና በጦርነት ምክንያት አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚናገሩ ዜጎች መፍትሔ ሳይሰጣቸው፣ ለመዘጋጃ ቤት ያን ያክል ወጭ ማውጣት ተገቢ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው።
የዚህ የሕንፃ ዕድሳት ጊዜውን ጠብቆ ያልተከናወነና ቅድሚያ መተግበር ያለባቸውን ችግሮች ችላ ያለ መሆኑን ያብራሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌጥዬ ያለው ናችው።
ጌጥዬ “አዲስ አበባ ውስጥ ያለው አስተዳደር ምን ጊዜም ኢትዮጵያ ሲዖል ውስጥ ሆና እያለ ገነት ውስጥ እንዳለች አድርጎ ማሳየት ይፈልጋል” ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባም በጣም በርካታ ችግሮች አሉ የሚሉት ጌጥዬ፣ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ሕዝቡ በብዙ ቅንጡ ኹኔታዎች እንደሚያልፍ አድርጎ ማሳየት ይፈልጋል ያሉ ሲሆን፣ እንደ አጠቃላይ ሲታይ መንግሥት አገሪቱ መከራ ውስጥ ብትሆንም፣ መከራውን ትቶ በጎ በጎውን ነገር ብቻ የማሰብ ዝንባሌ ነው የሚታይበት ሲሉ አብራርተዋል።
ጌጥዬ “ታደሰ” የተባለው መዘጋጃ ቤት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ የተሠራ ሕንፃ መሆኑን አስታውሰው፣ በዘመኑ የተሠሩት ሕንፃዎች ደግሞ በጣም ጠንካራ ስለሆኑ ለመዘጋጃ ቤቱ ዕድሳት ሲደረግለት ይህን ያክል ወጭ መደረጉ አላሳመናቸውም።
ከጌጥዬ አስተያየት በአጠቃላይ መረዳት የተቻለው፣ መዘጋጃ ቤቱ መታደሱ የሚያስከፋ ነገር መሆኑን ሳይሆን፣ ሌሎች በግንባር ቀደም ሊሠሩ የሚገባቸው አገራዊና ሰብዓዊ ችግሮች እያሉ በደቀቀ ኢኮኖሚ ውስጥ ባለች ኢትዮጵያ ይህን ያክል ወጭ ማውጣቱ ተገቢ አለመሆኑን ነው።
መንግሥት ለተለያዩ የቅንጦት ጉዳዮች የሚበጅተው ብር የሚሰበሰበው ከሕዝቡ ነው የሚሉት ጌጥዬ፣ ወቅቱ በቅድሚያ የተራቡና በጦርነት ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የምናስብበት እንጂ ሕንፃ የሚታደስበት ባለመሆኑ፣ የሕዝቡ ንብረት እየባከነ ነውና ዝም ብሎ ማለፍ ሳይሆን መጠየቅ አለበት በማለት ነው የግል አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።
በዚህ ወቅት መደረግ ያለበት ለቅንጦት የሚሆን አንድ ሕንፃ ማደስ ነው ወይስ የሕልውና ትንቅንቅ ውስጥ ያሉ ወገኖችን መርዳት? ሲሉ የጠየቁት ጌጥዬ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በጣም በርካታ ምግብ ለማግኘት የሚቸገር ማኅበረሰብ እንዳለ ራሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ ነው ያሉት።
በሱማሌ ክልል ድርቅ ተከስቶ በርካታ ሰዎችና እንስሳት ድጋፍ በሚሹበት ወቅት፤ በወለጋ በርካታ ዜጎች ንብረታቸው እየተዘረፈና እየተገደሉ ባሉበት ወቅት፣ በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ዕርዳታ በሚያስፈልግበት ወቅት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ዳግም ጦርነት በተከፈተበትና ሕዝቡ ተፈናቅሎ ባለበት ወቅት፣ ከሕዝብ የተሰበሰበውን ብር ማባከን እና “ለሕንፃ ዕድሳት 2.2 ቢሊዮን ብር አወጣን” ማለት ቀልድ መሆኑን ነው የገለጹት።
መንግሥት በጦርነቱ ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ዕርዳታ እያደረኩ ነው ቢልም ከደረሰው ጉዳት ጋር ሲነጻጸር በቂ አይደለም የሚሉት ጌጥዬ፣ በጦርነቱ ምክንያት የትምህርት ተቋማት በመውደማቸው ትምህርት ማስቀጠል ባልተቻለበት አገር ሕንፃ ማደስ ወቅቱን ያልጠበቀ ተግባር ነው ብለዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ጌጥዬ በመጨረሻም ይህ የተጋነነ ወጪ በጦርነት የደቀቀውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይባስ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ የማይቀር መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር አባል እና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ስሜነህ ቤሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይም በጦርነቱ ውድመት ደርሶበት ባሽቆለቆለበት ወቅት የሕዝብን ገንዘብ ለቅንጦት ነገሮች መበጀት ኢኮኖሚው ላይ የበለጠ ማሽቆልቆል እንደሚያስከትል ነው ያስረዱት።
እንኳንስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በጣም እያሽቆለቆለ ባለበት ወቅት፣ ሠላም በሠፈነበት፣ ኢኮኖሚ በሚያድግበት፣ የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ጣሪያ ባልነካበት፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡ ኑሮ በተሻሻለበት ወቅትም ቢሆን፣ ባላደጉት አገራት ለቅንጦት ነገሮች ገንዘብ መበጀት ተገቢነት የለውም ሲሉም ነው አክለው ያብራሩት።
በአገራችን ሀብት ያለአግባብ የማባከን ችግር እንደሚስተዋል የጠቀሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ይህ ብክነት በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኩል የሚስተዋል ስለሆነ መሆን የሌለበትና መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው በማለት ነው ምክራቸውን ያካፈሉት።
ቀድመው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም እንኳ በወቅቱ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር የሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የመድኃኒት ድጋፍ፣ የወደሙ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ግንባታ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
በመጨረሻም፣ የእናቶች መደፈርና የተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቅ ነው የቅድሚያ ጉዳይ መሆን ያለበት ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ለመዘጋጃ ቤቱ ዕድሳት የወጣው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ የቅንጦት ወጪዎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ሊጤኑ ይገባል ሲሉ ሙያዊ ምክራቸውን አካፍለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014



