በደሴ ከተማ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅርንጫፍ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ

0
701

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው የሕውሓት ቡድን ወድሞና ተዘርፎ የነበረው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በደሴ ከተማ የሚገኘው ቅርንጫፍ፣ ከውድመቱ አገግሞ ዳግም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በደሴ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት በጦርነቱ ምክንያት 2.6 ቢሊዮን ብር የሚገመት ውድመት እንደደረሰበት አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር)፣ ለጤና ተቋማት የሕክምና ግብዓትና መድኃኒቶችን ከማቅረብ ጎን ለጎን፣ በጦርነቱ ወድሞና ተዘርፎ የነበረው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደሴ ቅርንጫፍ ዳግም ወደ ሥራ ተመልሷል ማለታቸው ተሠምቷል።
በመሆኑም፣ 190 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ወደ ቅርንጫፍ ደርሰው ለጤና ተቋማት እየተሠራጩ ሲሆን፣ በተለይም ለእናቶችና ለሕፃናት የሚውሉ የሕክምና ግብዓቶችን ጨምሮ፣ ለስኳርና ለደም ግፊት ሕሙማን የሚውሉ መድኃኒቶች እንደሚገኙበት መብራራቱም ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይም፣ በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማት ከነበሩበት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ጥረት እንደሚደረግ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ በኹሉም የአገሪቱ የጤና ተቋማት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here