ኢትዮጵያ – በድኅረ አድዋ ድል

Views: 236

የአድዋ ድል ዘንድሮ 124ኛ ዓመቱን ይዟል። ድሉ መጀመሪያ ይሰጠው ከነበረው ግምትና በብዙኀኑ ከነበረው እሳቤ አሁን ከ124 ዓመታት በኋላ ብዙ ለውጦችን ሊያሳይ እንደሚችል እሙን ነው። እንደውም ዛሬ ዛሬ ሌላ መልክ የያዘ ይመስላ። ይህም ‹የአድዋ ድል የማን ነው› የሚል ጥያቄን ያስነሳ ሲሆን፣ የብሔር ፖለቲካ ጸንቶ ክፍፍልና መለያየት በጉልህ በሚታይበት ጊዜ፣ አድዋም በዛ ውጪ የመታየት እድል ስላልገጠመው ነው። ነገሩ ታድያ በድሉ ወይም ከድሉ በፊት ከሆነው ይልቅ፣ ከድሉ በኋላ በተከሰተው ሁሉ የሚመዘን ይመስላል።

ታድያ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ በውስጥ እንዲሁም በውጪ ምን ዓይነት መልክ ነበራት፣ በታሪክስ ድሉ እንዴት ይታያል፣ ውዝግቦቹ በምን ተነሱ፣ እንዴትስ ነው ድሉ ዛሬ ላይ እየተከበረ ያለው በሚለውና በልዩነቶቹ መካከል አስታራቂ መፍትሔ ካለ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል። እነዚህንም የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ የታሪክ ምሁራንን በማናገር፣ መጻሕፍትን በማገላበጥና የቀደሙ ሕትመቶችን በመቃኘት ነገሩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርእሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

‹‹…እንዲህም እስኪሆን ድረስ ከሌሊቱ 11 ሰዓት የጀመረ እስከ 4 ሰዓት ድረስ ተኩሱ አላባራም። ድምጹም እንደ ሐምሌ ዝናም እንደማያባራው ነበር። በኖኅ ጊዜ ሰማዩ ተነድሎ መሬቱን አጠፋው እንደሚባለውመ እንደዚያ ይመስላል እንጂ፣ በሰው እጅ የተተኮሰ አይመስልም። መድፉም ሲተኮስ ጢሱ የቤት ቃጠሎ መስሎ ይወጣ ነበር። የተኩሱ ጢስ ብዛት የኹለቱንም ወገን ሰልፈኛ ሁሉ ከዛፍ ጥላ ስር እንደተቀመጠ ሆኖለት ዋለ። ነገር ግን ከብዙው በጥቂቱ ጻፍን እንጂ የአድዋን ጦርነት ዐይናችን እንዳየው፣ ጆሯችን እንደሰማው መጻፍ አይቻለንም››

ይህ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በ1988 ካሳተመው ‹የአድዋ ውሎ› ከተሰኘና የአድዋ ዘመቻና ጦርነት በሦስት የዐይን ምስክሮች በተተረከበት መጽሐፍ ነው። በዚህም መጽሐፍ ከሦስቱ የዐይኝ ምስክሮች መካከል ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ የተባሉት ‹ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ ካስነበቡትና በ1959 ከታተመ፣ እንደ ቅርስም ከተመዘገበ መጽሐፍ የተቀነጨበ ነው።

እንግዲህ አድዋ እንዲህ ባለ አሳዛኝና ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነበር ኢትዮጵያ በድል የተወጣችው። ይህም በዓለም ፊት አንጸባርቃ እንድትታይ አድርጓል። ድሉ ጥቁሮች በነጮች ላይ የተጎናጸፉት ድል በመሆኑ፣ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው አስችሏል። የታሪክ ማሁራኑም ‹‹የአድዋ ትልቁ አብነት አንዲት አፍሪቃዊት አገር ነጻነቷን በኃይሏ ተከላክላ ለማከበር መቻሏ ነበር።›› ሲሉ ያወሱታል።

የአድዋ ድል- በታሪክ
አውሮፓውያን አፍሪካን በመቀራመት እንቅስቃሴያቸው የአፍሪካ አገራትን የቅኝ ግዛታቸው በማድረግ በብዙ እንደተሳካላቸው ታሪክ ምስክር ነው። ከዛም በላይ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራትም ዛሬ ድረስ የዘለቀ የቅኝ ግዛት አሻራ ይታይባቸዋል። የቅኝ ግዛት የአፍሪካ አገራትን በቋንቋ፣ በባህል፣ በአኗኗር ስርዓትና የእኔ የሚሉት መገለጫን በማሳጣት፣ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ላይ ጭምር ተጽዕኖ በማድረግ ዛሬም ድረስ የቤት ሥራን ሰጥቷቸው ይገኛል።

ኢትዮጵያም ይህን ሉዓላዊነትና ክብር ላለማስደፈር ከጣልያን ጋር ብቻ ሳይሆን ኢንግሊዝን ጨምሮ በየዘመኑ ‹ኃያላን› ከተባሉ መንግሥታት ጋር የተለያዩ ውጊዎችን ገጥማለች። ታድያ የእኒዚህ ኢትጵያን ለመውረርና በቅኝ ግዛት ለመያዝ የተመኙ የአውሮፓውያን፣ የጥረትና ሙከራቸው ሁሉ ማሰሪያ ተደርጎ ይቆጠራል፤ የአድዋ ድል።
ባህሩ ዘውዴ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከ1847 እስከ 1983› በሚል ርዕስ ባስነበቡት የታሪክ መጽሐፋቸው፣ የአድዋ ድልን የቅኝ አገዛዝ ማዕበልን የመታ ነው ይሉታል። ይህንንም እንደታሪክ ባለሞያ ሊሰጡት ከሚችሉት ማብራሪያ በተጨማሪ፣ በአድዋ ጦርነት ትረካው ለጣልያን ግልጽ ወገናዊነት የሚሳይ ነው ያሉትን ጆርጅ በርክሌ የተናገረውን እንዲህ ጠቅሰዋል፤

‹‹ከሰፊው የፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የአድዋ ጦርነት ከአፍሪካ ምድር አዲስ ኃይል መነሳቱን የሚያበስር ይመስላል። የዚያች አኅጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ሊሆኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል። እንዲያውም አሁን ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም፣ ይህ ሁኔታ (አድዋ) ጨለማይቱ አኅጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮፓ ላይ የምታደርገው አመጽ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነውም ተብሏል።››

የአድዋ ድል በታሪክ ዛሬም ድረስ በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ያገነነ እና ያከበረ ድል ሆኖ መዝለቅ ችሏል። ብቸኛ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ነው በሚል ያሰፈሩት የታሪክ ጸሐፍያንም አሉ። ይህም ሁሉ ሲደማመር አድዋን በታሪክ ትልቅ ስፍራ ይዞ እናገኘዋለን።

በዚሁ ላይ የሚያክሉት ባህሩ ዘውዴ፣ የድሉ አብነት በተለይም የነጮች የበላይነት ከአስከፊ የዘር መድልዎ ፖሊሲ ጋር በተቆራኘባቸው አካባቢዎች ኢትዮጵያ የክብር ፋና ሆና ታይታለች። አልፎም ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ ለሚጠራ ከነጮች ተጽእኖ ነጻ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንስኤ ሆኖ እንደነበርም በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል።

ታድያ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ ውጪ ላሉ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም ለነጮችም ጭምር አስደናቂና ክብር ያገኘ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከግራና ከቀኝ የተለያዩ ሐሳቦች የሚነሱበት ድል ነው። በአንድነት የተገኘ ድል እንደመሆኑ በአንድነት ሲወደስም አይታይም። በብሔር ፖለቲካ እየታመሰች ባለችው የአሁኗ ኢትዮጵያም፣ ድሉን ሁሉም በቀረበው ሽንቁር በኩል እያየ የሚያብራራው ሆኗል። ለዚህም መንስኤ የሆነውና ይህ ሁሉም መሆን የጀመረው፣ ከአድዋ ማግስት በታዩ ኩነቶች መሆኑን የሚስረዱ ደግሞ ይገኛሉ።

በአድዋ ድል ማግስት
አሁንም ከባህሩ አውዴ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሐፍ እንጥቀስ። በዛው መጽሐፍ ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ ወይም ማግስት የነበረችበትን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ዳስሰዋል። እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል፤ ‹‹…ይሁን እንጂ በፖለቲካ ረገድም ሆነ ከግዛቷ ይዞታ አንጻር አድዋ ለኢትዮጵያ ፍጹም ነጻነትን አረጋገጠላት ለማለት ያዳግታል። ይህም አድዋ በብዙ አንጻር አንጸባራቂ ድል የሆነውን ያህል የኢትዮጵያ መሪዎች ለዘመናት የጓጉለትን የባህር በር አላስገኘላቸውም።››

ይህ የድሉ ማግስት ነጻነት ፍጹማዊ ያለመሆኑ ሌሎችም ገጽታዎች እንደነበሩትም ባህሩ እንዲህ ሲሉ ጠቅሰዋል፤ ‹‹ዙሪያውን የከበቧት የአውሮጳ ቅኝ ገዥዎች በነጻነቷ ላይ ቀላል ነው የማይባል ገደብ አበጅተውባት ነበር። እሷን ሳያማክሩና ሳያሳትፉ በግዛቷ ላይ ውል ይዋዋሉ፤ ጥቅም ይካለሉ ነበር። ኢትዮጵያ ነጻ መንግሥት ነኝ ብላ ወደ መንግሥታት ማኅበር ለመግባት ስትፈልግም ብዙ አሳር ነው ያገኛት። የሥልጣኔ ደረጃሽ ዝቅተኛ ስለሆነ ለማኅበር አባልነት ብቁ አይደለሽም ተብላ ደጅ መጥናት ነበረባት።››

ይህ እንግዲህ ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ጋር በነበራት ግንኙነትና በውጪአዊ ገጽዋ ከአድዋ በኋላ የነበረችበት ሁኔታ ፍንጣቂ ነጸብራቅ ነው። በምጣኔ ሀብት ረገድም ኢትዮጵያ ከኢምፔሪያሊዝም ሙሉ ለሙሉ ነጻ እንዳልነበረች በመጽሐፍ ሰፍሮ ይገኛል። ባህሩ በጥቂት ቃላት የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ነው ያኖሩት፤ ‹‹አውሮፓውያን በአድዋ ድል የተዘጋባቸው የመሰለውን የኢኮኖሚ በር፣ በንግድና በሞኖፖል ውሎች አማካይነት ገርበብ ለማድረግ ቻሉ።››

ፖለቲከኛና የታሪከ ተመራማሪው ኢብራሂም ሙሉሸዋ፣ ድኅረ ድል አድዋን በኢትዮያ ውስጥ ምን መልክ እንደነበረው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው አጠር ያለ ቆይታ አብራርተዋል። በዚህም ድኅረ አድዋ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አፄ ምኒልክ ኃይላቸው የመጨረሻ ደረጃ የደረሰበት ነው ሲሉ ያነሳሉ። ‹‹እስከሚታመሙ ድረስ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ጊዜ ነው።›› ያሉት ኢብራሂም፣ ከአድዋ በፊት ያደረጉት መስፋፋት ብዙ አካባቢዎችን በቁጥጥራቸው ስር እንዲያውሉ አግዟቸዋል፤ ያም ቀጥሎ ለመጣው የአድዋ ጦርነት የበለጠ ኃይል ይዘው እንዲዘምቱ አስችሏቸዋል በማለት፣ ቅድመ አድዋ እና ድኅረ አድዋ ድል የነበረውን ሁኔታ ያስቃኛሉ።

የአድዋ ድል ማግስት ለምኒልክ የበለጠ ኃይልና ሥልጣን ከመስጠቱ በተጓዳኝ የተረጋጋ አገዛዝ እንዲፈጥሩ አድርጓል። ይህም የአድዋ ማግስት የምኒልክ ሥልጣን ኹለት ውጤቶችን በኢትጵያ ላይ አምጥቶ ነበር። አንደኛው እንደ አገር ምሥረታና እንደ አገር ማጽናት ነው። ኢብራሂም እንዳሉት፤ ድሉን እንዲሁም ምኒልክን በበጎ ዐይን ለሚመለከቱና ለሚረዱ፣ የአድዋ ድል አገርን የማቅናት ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ‹‹ነገር ግን…›› አሉ፣ ‹‹ነገር ግን የምኒልክን ሁኔታ በበጎ ጎን ለማይረዳና ምኒልክ አገር ወረሩ ብሎ ለሚል አካል፣ አድዋ አሉታዊ ተጽእኖ ነው ያመጣበት። ምክንያቱም ምኒልክ የበለጠ ኃል ያገኙበት ጊዜ ስለሆነ››

ይህ በግልጽ ታሪኩን ለሚቃኝ የሚታይ ሁኔታ መሆኑን የሚጠቅሱት ኢብራሂም፣ ጉዳዩ ይህ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚል አይደለም ባይ ናቸው። እንደ እርሳቸው የግል እምነትም፣ ድኅረ አድዋ ድል የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ አፄ ምኒልክና ሌሎችም መሪዎች የኢትዮጵያን አንድነትን ለማምጣት ከሄዱበት መንገድ አንጻር የሚታይ ነው።

በተለይ የተወሰነን አካባቢ ባህል፣ ቋንቋ እና ሀይማኖት በሌሎች ላይ በመጫን አገራዊ ለማድረግ መሞከር ይታይ ነበር ይላሉ። ታድያ እነዚህ ከጅምሩ በእነዛ መንገዶች ባይኬድ ኖሮ፣ ዛሬ የሚታዩ ጭቅጭቆች አይነሱም ነበር። ተመሳሳይ መልክ በመፍጠር አንድነትን ለማምጣት ከመሞከራቸውና ያም ሳይሳካ ከመቅረቱ በላይ፣ አሻሽሎ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ላይ የታዩ ክፍተቶችም ችግሩን እንዳባሰው ነው ኢብራሂም የሚያስረዱት።

‹‹ያንን ማድረግ ስላልቻሉ አመጽን ጋበዘ። እናም የተለያየ ብሔርተኝነት እንዲወጣ አደረገ። ይህ እንደማይሳካ ሲታወቅ ኃይለሥላሴ እንኳ አላስተካከሉም፤ ያንኑ ለመጫም ያደረጉት ነገር አልተሳካም። ከዛ ቀጥሎ አመጽ በአመጽ ሲደራረብ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር አደረሳት።›› ኢብራሂም እንዳሉት ነው። በጥቅሉ በየጊዜው በቂና አጥጋቢ መልስ ባለመሰጠቱ፣ ድኅረ አድዋ ኢትዮጵያ መረጋጋት አንሶ አመጽ የሞላት፣ በአድዋ ድል ላይም ክርክርና ውዝግብ የሚነሳባት አድርጓታል።
ነገሩ ተጻራሪ ይመስላል። በአንድ ጎን የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ገናና አድርጓታል። በሌላ በኩል ለውስጥ ሰላምና አንድነት ዛሬ ድረስ የዘለቀ ምለሽ ከአድዋ አልተገኘም። ለዚህ ኢብራሂም አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ‹‹[ኢትዮጵያ] ከውጪ ጠንካራ ከውስጥ ደካማ ናት። ሌሎችን የምንስብባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከውስጥ ግን ባለ ብዝኀነትን ማስተዳደር ስለሚያቅተን እንወድቃለን።›› ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።

ታድያ የዓለም አቀፉ የድኅረ አድዋ ኢትዮጵያ ሁናቴ ኢትዮጵያን አንጸባራቂ አድርጎ ሲያወጣት፣ በውስጥ ግን የተለያዩ ጭቅጭቆች መካከል የሚዶል ርዕስ ሆኖ ከርሟል። ለምን አድዋን የማይቀበሉ ኢትዮጵያውያን ተገኙ የተባለ እንደሆነ፣ ጉዳዩ ያለው ከመሪው ጋር እንደሆነ ይነሳል። ይህ ደግሞ በኹለት ጽፎች መካከል ተወጥሮ የሚያረግብ ማእከል የሆነ ሐሳብና ወደ ማእከል የሚስብ ሰው በመጥፋቱ ነው።ይህም በጽንፍ ጉዳዩን ወጥሮ ይዞ ያለ ሐሳብ፣ አፄ ምኒልክን እንደ መልአክ ፍጹም አድርጎ በማቅረብና እንደ ሰይጣን በክፋት በመመሰል መካከል ነው።

የአድዋ ድል – በውዝግብ አውድ
አዲስ ማለዳ ባለፈው ዓመት 2011/የካቲት 23 ለንባብ በበቃው 16ኛ እትሟ፣ ነገረ አድዋን በሐተታዋ ይዛ ወጥታለች። በዛም ላይ በአድዋ ታሪክ ላይ የጠራ አንድነትና መግባባት እንደሌለ ያነጋገረቻቸው የታሪክ ባለሞያዎችና አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል። በአድዋ ድል ዙሪያ ውዝግቦች የሚነሱትም፣ ታሪክ ጸሐፊዎች የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በግልፅና በሚዛናዊነት አላሰፈሩም በሚል ወቀሳ ነው።

የታሪክ መዛግብቱ በጦርነትና በድል ታሪኩ ላይ የእያንዳንዱን የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝብ ታሪክ በሚዛናዊነትና በግልፅ ከማስፈር ይልቅ፣ አፄዎቹን ጨምሮ የጦር መሪዎቹ ላይ ብቻ ማትኮራቸው ሕዝብ የእኔ ነው ብሎ ትኩረት እንዳይሰጠው አድርጓል ብለው የሚያምኑ ስለመኖራቸውም ተገልጿል።

የታሪክ አጥኚ የሆኑት ሳሙኤል አሰፋ፤ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ይህ የተከሰተው በታሪክ አተረጓጎም ምክንያት ነው ሲሉ ያነሳሉ። ለዚህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ተጠያቂዎች ፖለቲከኞች ናቸው። እንደ ሳሙኤል ገለጻ፣ ታሪክን የሚተረጉሙት ፖለቲከኞች ናቸው። የአድዋ ድል የመከፋል አንዱ ምክንያታችን እንዲሆን ያደረገውም፣ ባለፉት 27/28 ዓመታት በብሔር ክፍፍል የተነሳ፣ እንደውም የአድዋ ድል የአንድ ብሔር ነው በሚል እየተደረገ ያለው ገለጻ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ሆኖም ይህ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ወዲህ በጥቂቱም ቢሆን መሻሻል የታየበት መሆኑን ሳሙኤል ያመላክታሉ። ይህም በአድዋ ከዘመቱ የጦር መሪዎች መካከል አምስቱ የኦሮሞ ተወላጆች መሆናቸው በብዛት እየተሰማና እየተነገረ ሲሄድ፣ በተወሰነ ደረጃ ውዝግቡን እንዳቀዘቀዘው ነው ከእይታቸው በመነሳት ያወሱት። ይህም ታድያ ከምኒልክ ጎን ለጎን ሠራዊቱን ሲመሩ የነበሩ አዋጊዎችና መሪዎች ታሪክ በጉልህ ሊነገር እንደሚገባ ሳያመላክት አይቀርም።

በድሉ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ሁሉ መመስከንና መወደስ እንዲሁም መከበር አለባቸው የሚሉት ሳሙኤል፣ በተለመደው ስርዓት ደግሞ ለጥፋት ተጠያቂ እንደመሆነው ሁሉ ለአሸናፊነትም አንን ኃይል ያሰባሰበ መሪ እንደሚወደስ ይጠቅሳሉ። ይህም ነው ምኒልክን የበለጠ ሥማቸው ጎልቶ እንዲነሳ ያደረገው። ለድልም ሆነ ለውድቀትም ኃላፊነትን የሚወስዱ ሰው እርሳቸው ስለነበሩ።

‹‹ሌሎች ፊት አውራሪዎች እንደሚነሱት ሁሉ፣ ትልቁ ክሬዲት ወደዋናው መሪ መሄዱ አይቀርም። እርግጥ ነው የሃይማቶች ድረሻም ነበር። ጣይቱም እዛ ውስጥ ድርሻ ነበራቸው። ብዙዎቹም አብሮ ሥማቸው ይነሳል። ሌሎቹ የተነሱት በበቂ መጠን አይደለም የሚል አካል፣ ያልተነሱትና ያልተወሱትን ማንሳት ይኖርባቸዋል።›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

የአድዋ ድልን በማሰብ ሂደት ውስጥ አሁን ላይ ሥማቸው ገንኖ ከሚታወቁ እንቅስቃሰዎች መካከል ጉዞ አድዋ አንደኛው ነው። የጉዞ አስተባባሪና ከመሥራቾች መካከል የሆነው ያሬድ ሹመቴ፣ በአድዋ እና በኢትዮጵያዊነት በኩል አየር ላይ የሚናፈሰው ሐሳብ እና መሬት ላይ ያለው እውነት አይገናኝም ሲል ባለፈው ዓመት የየካቲት 23 የአዲስ ማለዳ እትም ላይ እይታውን አካፍሏል።

ለዚህ ማሳያ ሲል ጠቅሶት የነበረው፣ ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ከተለያዩ ወገኖች ዛቻዎች ስለነበሩ ስጋት እንደነበረባቸው ነው። ነገር ግን በተግበር ሲጓዙ ስጋቱ እውን ሆኖ እንዳልገጠማቸውና በሕዝቡ ፍቅር እየተላቀሱ አይረሴ በሆነ ልዩ ጉዞ አድዋ ላይ መድረሳቸውን ተናግሯል።

ያሬድ ቀድሞ ስለነበረው ዛቻና ስጋት ሲያስረዳ፣ ‹‹አንዱ ‹የአድዋንና የምኒልክን ታሪክ አንፈልግም (አንቀበልም) በእኛ ክልል ውስጥም አታልፏትም› የሚል ሲሆን፣ ኹለተኛው ‹የአድዋ በዓል መከበር ያለበት አድዋ ሳይሆን አዲስ አበባና አንኮበር ነው› የሚል ነው። ሦስተኛው ደግሞ ‹በእኛ ክልል አልፋችሁ አድዋ ላይ አትገቧትም› የሚል ነበር›› ሲል ጠቅሷል። ታድያ ጉዞውን ጀምረው በመንገዳቸው ላይ ግን፣ ከአዲስ አበባ ከወጡ ጀምሮ ባሉት 80 ኪሎ ሜትሮች ውስጥ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ደግሰው እንደተቀበሏቸውና በሰላም እንዲገቡ ተመኝተው እንደሸኗቸው፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ሲያልፉም ሕዝቡ በደስታ ሲቀበላቸው እንደነበር እንዲሁም በትግራይ ክልልም ነዋሪው በፍቅር ሲያስተናግዳቸው እንደነበር በመግለፅ የሕዝቡን አንድነት ስለማረጋጋጣቸው ይመሰክራል።

እንደውም ‹‹በምቾት የሚያንገላታ ሕዝብ ነው የገጠመን›› ያለው ያሬድ፣ በየደረሱበት ደስታ እንደነበርና ሲለዩዋቸው በፍቅር ተቃቅፈው የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ እንደገጠሟቸው፣ በወቅቱ ሐሳቡን ላካፈለው ለአዲስ ማለዳው ስንታየሁ አባተ አስረድቷል።

‹‹በረገጥንበት መሬት በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ተቀብለውናል ሙሉ የጉዞ ቀናት የአድዋ በዓል ይመስል ነበር›› ሲልም ስላጋጠማቸው ኢትዮጵያዊ አንድነት በማንሳት፣ ሕዝቡ አንድ መሆኑንና ሌሎች የፖለቲካና የልማት ጥያቄዎች የሚመለከታው በራሳቸው መንገድ እንዲመለሱ፣ ሕዝቡ ግን በኢትዮጵያዊነት ላይ ልዩነት እንደሌለው ማስተዋላቸውንም አክሏል።

እንግዲህ በግል ሐሳብ እንዲሁም ትምህርትን መሠረት ባደረገ ጽንሰ ሐሳብ ደረጃ፣ አድዋ ላይ የተለያዩ እሳቤዎች እንዳሉ ሲነሳ፣ በጉዞ አድዋ መንገዶችን አቋርጠው የሄዱ ተጓዦች ደግሞ ‹እውነታው ሌላ ነው!› የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። ይህን ሁሉ ማጥራትና መመልከት ግን አሁንም እንዳልተሠራ የቤት ሥራ የታሪክ ሰዎችን ጨምሮ የመንግሥት አካላትና ይመለከተኛል ለሚሉ ሁሉ የሚጠብቃቸው ጉዳይ ነው።

የአድዋ ድል አከባበር
«ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና እኔም ይኽንን በዓል እንዲህ አድርጌ ማክበሩ፤ እናንተንም ማድከሜ እግዚአብሔር በቸርነቱ ሰባት ዓመት ሙሉ በእረፍትና በጤና ስላኖረን፣ ስለዚህ ነገር ማክበር ይገባል ብዬ ነው። እንጂ ለጥጋብና ለትዕቢት፣ ሠራዊት በዛ የጦር መሣሪያ በረከተ ለማለት አይደለም።…»
ይህን ያሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው። ይህንንም የተናገሩት የአድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረበት እለት ሲሆን፣ ይህም የሆነው በድሉ ሰባተኛ ዓመት ወይም በ1895 ነው።

አሁን ላይ የአድዋ ድል በብሔራዊ ደረጃ ያውም በወጣቶች ተነሳሽነትና በሕዝብ ፈቃደኝነት የሚከበር በዓል ሆኗል። ልዩነቶችና መስማማት ላይ ያልተደረሰባቸው ወይም በመግባባት ያልታለፉ ብዙ ሐሳቦች ቢኖሩም፣ ወጣቶች በአገር ፍቅር ስሜት አድዋ ላይ የዘመቱ እናቶች አባቶቻቸውን ማክበር ላይ በስፋት ሲሳተፉ ይታያሉ።
አብዱልቃድር መሐመድ ሰዓሊ ነው። 14 አባላት ያሉት ‹ኅብር› የተሰኘ የሥነጥበብ ቡድን አባል ነው። የዛሬ ኹለት ዓመት የተቋቋመው ቡድኑ፣ የመጀመሪያ ሥራውን ያደረገው ‹ዝክረ አድዋ› በሚል ርዕስ በ14 ሰዓልያን የተሠሩ የስዕል ሥራዎችን ለእይታ በማቅረብ ነው። ‹‹አድዋ የኢትዮጵያ ድል ባይሆን ኖሮ ወይ የሌላ አገር ድል ቢሆን ኖሮ፣ እንዴት ነበር የሚያከብሩት በሚል ነው የተነሳነው።›› የሚለው አብዱልቃድር፣ በኢትዮጵያ ግን ድሉ ሌሎች እጅ ቢገባ የሚኖረውን ያህል ዋጋ ያልተሰጠው እንደሆነ በቁጭት ይናገራል። በአንጻሩ ሊሆን እንደሚገባና ክብር ለአድዋ እንደሚያሻ ግን፣ በስዕል ሥራዎች ሰዎች እንዲረዱት ለማድረግ ነው እየሠራን ነው ሲል ያነሳል።

ዘንድሮም ዝክረ አድዋ ቁጥር ኹለት የስዕል አውደ ርዕይ፣ ባሳለፍነው ሐሙስ የካቲት 19/2012 ኤግዚቢሽን ማእከል አጠገብ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዝየም ለእይታ ክፍት ሆኗል። ባለፈው ዓመት ስዕሎቻውን የጎበኙ ሰዎች የሰጧቸው ግብረ መልስ ለዘንድሮ እንዲገፉ እንዳበረታታቸውና፣ በአድዋ ለዛሬ ኢትዮጵያ የተከፈለውን ዋጋ ብዙዎች እንዲያውቁ ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ እንደተበረታቱ አያይዞ ጠቅሷል።

እንደ አብዱልቃድር ሁሉ የአድዋ ድል በዓልን በተለያዩ የጥበብ ክዋኔዎች አስበው የሚያልፉ እንደ ‹‹ክብረ አድዋ›› ያሉ ክዋኔዎችም ሳይጠቀሱ አያልፉም። ‹ብጌ› ወይም ‹ብጋራ› በሚል ከታሪክ ተካፋይና ተጋሪ ለመሆን፣ የካቲት 23 የበዓሉ እለት በባህላዊ አልባሳት፣ ዝማሬና ስርዓት ታጅቦ በአዲስ አበባ የሚደረግ ጉዞ አለ። ጉዞውም አራዳ ጊዮርጊስ ከሚገኝበት የምኒልክ አደባባይ ተነስቶ እስከ አድዋ ድልድይ የተለያዩ ትርዒቶች እየቀረበበት የሚያልፍ ሲሆን፣ ይህም ከዓመት ዓመት እየሰፋና እየደመቀ የታየ ነው። የፌስቲቫል መልክ ይዞም ይገኛል።

ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ጥበባዊ ክዋኔዎች በአድዋ ድል ሥም ይዘጋጃሉ። በጎ አድራጎት ሥራዎች ይሠራሉ፣ ደም በመለገስ የደም ስጦታ ይሰጣል፣ ሌላም ሌላም። ይህ ሁሉ የአድዋ ድልን እንዴት ማክበር እንደሚገባና ያንንም ከታሪክ ማስታወሻነት በተጓዳኝ እንዴት ጥቅም እንዲያስገኝ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ ነው። ድሉ በፖለቲካ መነጽር እየታየ፣ በብሔር እየተቃኘ፣ በተለያዩ ጽንፎች እየተወጠረ ከሚሰጠው ትርጉምና ከሚፈጥረው ውዝግብ ባሻገር፣ ለቱሪዝም፣ ጎብኚን ለመሳብና ተጨማሪ ለአገር የሚጠቅሙ ገቢዎች ለማግኘት እንደ አንድ ትልቅ መንገድ ሊታሰብም ይገባል። የአፍሪካ አገራት ይህ ቢሆን ዐይናቸውን ሳያሹና ሳያቅማሙ በደስታ የሚታደሙበት አውድ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

መፍትሄው ምንድን ነው?
ታድያ የአድዋ ድልን አከባበር በኢትዩጵያ ሊያስገኘው የሚችለው ጥቅም እንዳለ ሆኖ፣ አገራዊ መግባባት ይቀድማልና፣ ብዙዎች በዛ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህም የሰከነ ትውልድ መፍጠር አንዱና ወሳኝ መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል። ያም እንዲሆን የፖለቲካ ስርአትን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህም በታሪክ ላይ ሰከን ብሎ ወደመወያየት፣ ቀጥሎም ወደ መግባባት የሚያደርስ መንገድ ይሆናል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ በተለያየ ጊዜ ለመገናኛ ብዙኀን በሚሰጡት አስተያየት፣ በታሪክ ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ የመፍትሔ መንገዶች ያስረዳሉ። በተለይም የታሪክ ትምህርት ክፍሎች የጋራ መድረክ ፈጥረው መምከር እንዳለባቸው፣ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ያሉ የታሪክ ትምህርት ክፍሎችን መጠናከር እንዳለባቸውና ብቁ የታሪክ ምሁር ማፍራት እንደሚገባ ያሳስባሉ። ለዚህም የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የማቋቋምን አስፈላጊነት ይጠቅሳሉ።

የመገናኛ ብዙኀንንም ሳያነሱ አያልፉም። መገናኛ ብዙኀን በተደራሽነት አቅማቸው ታሪክ ነክ በሆኑ ዘገባዎች ላይ ጥንቃቄ በማድረግና ባለሙያዎችን በሚገባ በመጠየቅ እውነታን ማቅረብ እንደሚጠበቅባው ይገልጻሉ።

ታሪክ አጥኚው ሳሙኤል አሰፋ በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል ወደ ጋራ መግባባት የሚወስደንን መንገድ ይጠርግ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው በመጥቀስ፣ ትርክቶቻችን ላይ መስማማት ላይ ካልመጣን በቀር ግን ያ የሚሆን አይደለም ብለዋል። በዚህም ጽንፍ የረገጠ የብሔር ትርክትን ማለዘብና ብሔራዊ አንድነት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። የታሪክ ባለሞያዎችም ተስማምተው አንድ ሐሳብ ይዘው መውጣት ይኖርባቸዋል።

ፖለቲከኛና የታሪክ ባለሞያ ኢብራሂም ሙሉሸዋ መፍትሔ ይሆናል ያሉት፣ እንደ ቀደሙት ሁሉ ውይይት ነው። ‹‹ውይይት ያስፈልገናል። ይህ ጥሩ ያ መጥፎ በሚል ግን መሆነ የለበትም።›› ብለዋል። በተለይም ምኒልክን መልዐክም ሰይጣንም አድርጎ አለማቅረብ ያስፈልፋል። ትልቅ አገር አስረክበውናልና የሚገባቸውን ክብር ሊያገኙ ይገባል። ነገር ግን የአፄ ምኒልክን አሠራር የተቃወሙ ሰዎችም ከመሬት ተነስተው እንዳልሆነ በማወቅ፣ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማተናገድ ያስፈልጋል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

‹‹ብዙ ጊዜና ብዙ ቦታ እንዳልኩት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሳይሆን የታሪክ ፖለቲካ ነው ያለው። የሚያጣላን ታሪክን በፖለቲካ መነጽር ማየት ነው። በትክክለኛው ታሪክ ለመረዳት ከፖለቲካ ነጻ መሆን ያስፈልጋል።›› ብለዋል። የመገናኛ ብዙኀንና ጋዜጠኞችም የተለየ ሐሳብን ሳይፈሩ፣ ሁሉንም ማስተናገድ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ የአድዋ ድልን ባወሳችበት የ2011 የየካቲት 23 እትሟ ላይ ሐሳብ ከሰጧት መካከል፣ ያሬድ ሹመቴ መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሐሳብ አቀብሏል። በዚህም መለያየት ለሰላም ዋስትና አይሆንም ብሎ የሚያምነው ያሬድ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ‹እንለያይ› ብለው ከተለያዩ በኋላ ወደ ጦርነት ለመግባት ዓመታት አልወሰደባቸውም ሲል በምሳሌ አስረድቷል። መከራ ከመምጣቱ በፊት መሰባሰቡና አንድነትን ማጠንከሩ ይበጃል ሲልም መክሯል። እንዲህ ዓይነት በዓላት ከአደባባይ ተሻግረው ከቤተሰብም ጋር በየቤቱ ቢከበሩ የበለጠ የኢትዮጵያዊነት አጠንካሪ እንደሚሆኑም ያምናል።

ከዛ ባለፈ አስተያየት የሰጡ የታሪክ ምሁራንም፣ ታሪኩ አሁንም የሕዝቡን ተሳትፎ መሰረት አድርጎ ቢጻፍ የሚል የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com