በይደር የቆው የፍፃሜ ውድድር

0
396

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ አገራዊ አጀንዳዎች መካከል እግር ኳስን የተመለከተው የተለየ ነበር። ውድድሩ የዋንጫ ሲሆን፣ የተደረገው ደግሞ በወረዳና በከተማ መካከል ነው። በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ውስጥ ባሉት ሳንኩራ ወረዳና በቅበት ከተማ አስተዳደር መካከል የተካሄደው የዋንጫ ውድድርን በርካቶች ሲጠብቁት የነበረ ነው ተብሏል።

የ2014 የስልጤ ዞን የሻምፒዮና ውድድሩን የመንግሥት ባለስልጣናት ጭምር ካሉበት ሆነው በቀጥታ ሲከታተሉት የነበረ ሲሆን፣ እውነት ይሁን አይሁን ባይረጋገጥም አቶ ሬድዋን ሁሴንም መመልታቸው ተወርቷል። ስለጨዋታው አብዛኛው ሕዝብ የሠማው ከተጠናቀቀ በኋላ ቢሆንም፣ ኹለት ቀን ፈጅቶ ማለቁ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።

በተያዘለት ቀጠሮ መሠረት ጥር 17 ማምሻውን የተጀመረው ውድድር ዜሮ ለዜሮ በመጠናቀቁ ግርግር ተፈጥሮ ነበር። አንዳንዶች በመሀል የድንጋይ ውርወራ የተስተናገደበት ያልተጠበቀ ክስተትን አስተናግዷል በሚል ሒደቱን ሲተቹት ነበር። በሌላ በኩል ወንድማማች ማኅበረሰቦችን ለማራራቅ የተጠነሰሰ ጉዳይ እንደነበር አድርገው የሚያቀርቡም ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ፣ ምሽቱን ያለውጤት የተጠናቀቀው ውድድር ግድ አሸናፊው ሊለይ ይገባ ስለነበር ፍፁም ቅጣት ምት በየተራ መሰጠት ይጠበቅ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ መጀመሪያ ማን ሊመታ ነው የሚሉ አይነት ሐሳቦች በተመልካችም ሆነ ተጋጣሚዎች አዕምሮ ውስጥ በሚመላለሱበት ወቅት ያልተገመተ ውሳኔ ተሰጥቷል። “ስለመሸ ፍፁም ቅጣት ምቱ ለበነጋታው ይሸጋገር” ተብሎ በቴክኒክ ኮሚቴው በይደር እንዲቆይ ተደርጓል።

ለኹለተኛ ቀን ለፍፁም ቅጣት ምት ብቻ ሜዳ እንዲገኙ የተደረገው መብራት ጠፍቶ ይሁን ጭራሹኑ ሜዳው መብራት ስለሌለው እንደሆነ ባይታወቅም፣ ሌላ የተደበቀ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ነው በማለት አስተያየታቸውን የሠጡ አሉ።

በሌላ በኩል፣ በይደር መቆየቱን የሠሙ የተለያየ ቀልድ አዘል ሐሳባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርተዋል። በርካቶች 47 ደቂቃዎች የቆየ ጨዋታ እንደሙሉ ጨዋታ ይቆጠራል ወይ ያሉ ሲሆን፣ መብራት ባይኖር እንኳን ለፍፁም ቅጣት ምት የስልክ ባትሪ አሊያም ሻማ ማብራት በቂ አልነበረም ወይ ብለው ነገሩን ያፌዙበት ነበሩ። ጨዋታው ተቋርጦ መምሸቱን የጠቀሱም ሲኖሩ፣ አንዳንዶች የሰላት ሰዓት ስለደረሰ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ያን ያህል እንዲመሽ የሆነውና ለበነጋታው የተቀጠረው ተመልካቾችም ይሳተፉበት ስለነበረ ነው በማለትም በጉዳዩ ለመቀለድ የሞከሩም ነበሩ።

በበነጋታው ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ሳንኩራዎች ከሜዳ ሳይገኙ ይቀራሉ። በዚህም ምክንያት ቅበቶች በፎርፌ አሸነፉ ተብሎ ዋንጫ እንደበሉ ይፋ ሲደረግ የሳንኩራ ደጋፊዎችን ያስቆጣል። ንዴታቸውን ቤት ሆነው ማቀዝቀዝ ስላልፈለጉም ለተቃውሞ አደባባይ መፈክር ይዘው ወጥተዋል። “የሳንኩራ ደጋፊዎች የሻገተ ፔናሊቲ አንመታም” ፣ “ፍትሕ ለእግር ኳስ፣ በ50 ደኪካ የዋንጫ ጨዋታ የጨረሰ፣ ፔናሊቲ ያሳደረ” የሚሉ መፈክሮችን አንግበው የተቃውሞ ሠልፍ አካሂደዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here