“የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር ዳግም ሥራ ይጀምራሉ“:- የትምህርት ሚኒስቴር

0
584

አርብ ጥር 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልደያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢዜአ እንደገለጹት በአማራ ክልል ህውሃት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልደያ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ አቋርጠዋል።

የህወሃት ቡድን በወረራ በቆየባቸው ወራት ዩኒቨርሲቲዎቹን ዘርፎና አውድሞ መሄዱን አስታውሰው በዳግም ጥገና ሥራ እንዲጀምሩ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በመንግስት ድጋፍና ባላቸው አቅም አስፈላጊ ግዥዎችንና ጥገናዎችን እንዲያካሔዱ ከማድረግ ባለፈ አማራጭ የትምህርት ማስኬጃ መንገዶችንም እንዲያስቡና ወደ ሥራ እንዲገቡ አሁንም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የወሎ፣ የመቅደላ አምባና የወልደያ ዩኒቨርሲቲዎች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ተማሪዎችን በመቀበል ዳግም ሥራ የሚጀምሩ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎችን ቀድመው በመቀበል ሌሎችንም በሚያወጡት መርሃ ግብር መሰረት የሚቀበሉ ይሆናል።

በህወሃት ወረራ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ተዛብቶ የቆየው የአካዳሚክ ካሌንደር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ይስተካከላል ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል።

የአካዳሚክ ካላንደሩን በማስተካከል በዩኒቨርሲቲዎች የተሳካ የመማር ማስተማር ሂደት እውን ለማድረግ አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here