“‹‹ኢ-መደበኛ አደረጃጀት›› በሚል ሰበብ በፋኖ ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ ይቁም“:-ባልደራስ

0
608

አርብ ጥር 27 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፤ ህዝብን ያላማከለ ድርድርም አገርን አይጠቅምም ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡

ፓርቲው ፋኖ በጭንቅ ጊዜ አገርን ከወረራ እና ከብተና የሚታደግ፣ በሠላም ጊዜ በየሙያ ዘርፉ ተሰማርቶ ሠላማዊ ኑሮውን የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው ሲልም ነው የገለፀው።

በዚህም መሠረት ፋኖ በጊዜያዊነት ተሰባስቦ በአገር ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሙሉ በሙሉ እስከሚወገድ በዱር በገደሉ እየተሰማራ፣ አካባቢውንና አገሩን ከጥቃት የሚከላከል ህዝባዊ ኃይል እንጂ፣ ቋሚ የሆነ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም ብሏል፡፡

ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርሮ በነበረበት ጊዜ ይህ እውነታ በውል ታይቷል ያለው ፓርቲው ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ፤ ለአገሩ ሉዓላዊነት የደም መስዋዕትነት ለመክፈል በከፍተኛ ወኔ ዝግጁ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረውን ፋኖ፣ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” በሚል ፍረጃ ወከባና ትንኮሳ እየተፈፀመበት እንደሚገኝ ነው ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ያመላከተው፡፡

ይህ ድርጊት ባልተቋጨው ጦርነት በየምሽጉ በተጠንቀቅ የሚገኙትን ፋኖዎች የሚነካ ብቻ ሳይሆን፤ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላትን አንድነት፣ ሞራልና ቅስም የሚሰብር ነው ሲል የወቀሰው ባልደራስ በሌላ በኩል ጫናውና ትንኮሳው ህወሓትን፣ ኦነግ ሸኔ እና ሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖች እና ኃይሎችን ተጠቃሚ እና ደስተኛ እንዲሁም ሞራላቸውን የሚያነቃቃ ነው ሲልም አውግዟል፡፡

ከፌዴራል መንግሥቱ የመከላከያ ኃይል ውጭ ያሉትን ታጣቂዎች ዕጣ ፈንታ በሚመለከት፣ ከጦርነቱ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚቀረጽ ፖሊሲ መወሰን ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡

ይህ እስኪሆን ድረስ በፋኖ ላይ በተናጠል የሚፈፀሙ ትንኮሳዎች እንዲቆሙ ባልደራስ ጠይቋል፡፡

ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዕዋትነት ከፍለው የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ በተጠንቀቅ የቆሙ ልጆቹን ማንም እንዲነካበት አይፈልግም ያለው ፓርቲው፣ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በጎረቤት አገር ድርድር እየተካሄደ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለፀ እንደሚገኝና ለህዝብ ግልጽ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ድርድሩን ከጥርጣሬ ነጻ ለማድረግ ሰባት ምክረ ሃሳቦችን መግለጫ ላይ አቅርቧል፡፡

ከእነዚህም መካከል ድርድሩ ለህዝብ ግልጽ ይደረግ፣ በጦርነቱ የተጎዱት የአፋር እና አማራ ክልላዊ መስተዳድሮች በድርድሩ ጉልህ ሚና ይኑራቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ዲያስፖራ ኢትዮጵያ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሂደቱን በታዛቢነት ይከታተሉ እና ለመገናኛ ብዙሃን በቂ መረጃ የሚደርስበት እድል ይፈጠር የሚሉት ሃሳቦችን ተካተውበታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here