ኢትዮ ቴሌኮም ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የልዩ ቅናሽ አገልግሎት ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
ኢትዮ ቴሌኮም ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ያዘጋጀው የልዩ ቅናሽ አገልግሎት ማዕቀፉ መጽደቁን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደገለጹት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተዘጋጀው የልዩ ቅናሽ አገልግሎት ተማሪዎችን ለማበረታት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተዘጋጀው የልዩ ቅናሽ አገልግሎት መጽደቁን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ አገልግሎቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል። አገልግሎቱ ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲበረታቱ እና ለጥናት ጊዜ አጋዥ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካዘጋጀው የልዩ ቅናሽ አገልግሎት በተጨማሪ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን እና ማሻሻያዎችን እያዘጋጀ መሆኑን እና እንደየአስፈላጊነቱ ይፋ እንደሚሆን ተጠቁሟል። ደርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የመጣውን የአዲስ አገልግሎት እና የነባር አገልግሎት ማሻሻያ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጥር 23/2013 የድርጅቱን የ2014 የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ጊዜ ተናገረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም 244 ፕሮጀክቶች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፣ 6.5 በመቶ የሚሸፍኑት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው ተገልጿል። እንዲሁም 87 በመቶ የሚሸፍኑት ፕሮጀክቶች በሒደት ላይ ሲሆኑ፣ 6.5 በመቶ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር መቋረጣቸው ተገልጿል።
ለ127 ዓመታት በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ሆኖ ዓመታትን የዘለቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌኮም አገልግሎት የሚጋራው እና የሚወዳደረው ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተከትሎ፣ ከአዲሱ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ጋር ለመወዳደር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ፍሬሕይወት ጠቁመዋል። ድርጅቱ ወደፊት ከሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ ለሚገጥመው የውድድር ገበያ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ፍሬሕይወት፣ የአገልግሎት ውድድሩ ሲጀመር ኢትዮ ቴሌኮም ያዘጋጃቸውን የመወዳደሪያ አገልግሎቶች ለገበያ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።
ደርጅቱ በ2014 ግማሽ ዓመት 28 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 86.4 በመቶ ማሳካት የቻለ ሲሆን፣ ገቢው ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6.7 በመቶ ዕድገት አለው ተብሏል። የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 78.8 ሚሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን፣ የወጭ ቅናሳ ስትራቴጂ በመቅረጽ ተግባራዊ በማድረግ በስድስት ወራት 1.2 ቢሊዮን ብር ወጭ ቅነሳ ማድረጉ ተመላክቷል።
በሰሜኑ ጦርነት ሰለባ በሆኑት በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ፣ እንዲሁም የጸጥታ ችግር ባለባቸው በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎቶች በመቋረጣቸው እና በመውደማቸው አራት ቢሊዮን ብር ማጣቱን ድርጅቱ አስታውቋል። በ10 ክልሎች ሦስት ሺሕ 473 የቴሌኮም አገልግሎት ሳይቶች በጸጥታ ችግር አገልግሎት አቋርጠው በመቆየታቸው ይገኝ የነበረውን 3.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያጣ ሲሆን፣ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመገንባታ ያወጣው 328.9 ሚሊዮን ብር መሆኑን አሳውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ያስተዋወቀውና የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጠው ቴሌ ብር 13.1 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራቱን እና አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 5.1 ቢሊዮን ብር ማዘዋወሩ ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014



