“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ከሰሞኑ አሳዛኝ ታሪኮችን ሰማን፤ ዐየን። ቶሎ የመርሳትና በአዲስ አጀንዳ የመወሰድ አባዜ እንደ ሕዝብ የታደልነው <ባህሪ> እየመሰለብን ነው። ባይሆን ኖሮ ቢያንስ ከሀና ላሎንጎ ጀምሮ የስንት ወጣትና ሕፃናት ሴቶች ሕይወት በከንቱ ተቀጠፈ፤ ያለፍትህ ታለፈ።
ገደላት፣ አሲድ ደፋባት፣ በጩቤ ወጋት፣ አቃጠላት…እንዲህ ያለ ዜና ሲሰሙ ሰዎች ምን ይላሉ? ድንቅ የሚለኝ ይህ ጉዳይ ነው። ለምን ብለው ይጠይቃሉ፤ ለምን ብሎ ጥያቄ ምንድን ነው? ለምን ገደላት? ለምን አሲድ ደፋባት? ለምን በጩቤ ወግቶ ሕይወቷን ነጠቃት? ለምን? ለምን? ለምን?
ሰዎች ይህን ጥያቄ የሚያነሱት <አሃ! ለዛ ነው እንዴ?> ብለው ለገዳይ ሽፋን ሊሰጡ ነው። ገዳይን አይዞህ የማለት ያህል ሊያፅናኑ ነው።
ለምን ተገደለች? እርሷ ምንም አጥፍታ አይደለም። ገምዳላ ፍርድ በሞላበት አገር ሞት ቅጣት ከሆነ ለስንቱ በተገባ! ደግሞ አጥፍታም ከሆነ ጥፋቷ ሴት መሆኗ ነው። ሴትነት ብሔር ቢሆን ኖሮ…ዛሬ ምድረ የማኅበራዊ ሚድያ ድምፅ ነኝ ባይ ሲጮህ ይውል ነበር። ሴትነት ዘር ቢሆን ኖሮ በቃልም፣ በተግባርም ጥቃት የሚደርስበት ዘር ተብሎ በሽብር ሕግ ይዳኝ ነበር። ከሰብአዊነት ቢቆጠር ለሞትና ጥቃት ሲዳርግ ሰንደቅ ዝቅ ተደርጎ ይውለበለብ ነበር።
ከዛ ይልቅ ግን <ለምን?> ተብሎ ይጠየቃል። ለምን ሳቀችለት? ምን ዋሸችው? ለምን እሺ አለችው? ለምን መንገድ ላይ ብቻዋን ሄደች? ከአጥፊው የከፋ በደልን ጠያቂ ይፈፅማል። የእርሱን ግፍ ትቶ የእርሷን ታሪክ ይበዘብዛል።
ይልቅ ይበቃል ማለት ነው። ካልሆነ ብሔር እንጥቀስ፣ ዘር እንቁጠር። ልብ የሚባለው እንዲያ ከሆነ…ለምን ብለው የሚጠይቁ ብሔሯንም አብረው ይጠይቁ። ያኔ ጉዳቷ ያንገበግበንና ይበቃል ያሰኘን ከሆነ!
ሃምሳ በመቶ ሥልጣን ሴቶች ይዘዋል በሚባልላት አገር…ፖለቲከኛና ሹም ሴቶች ወንድ አመራሮችን ይጠብቃሉ፤ ካልተለፈፈ ዝም ነው፤ በአለቆቻቸው ካልተባለ አይከተሉም። እንግዲያው ሹመታችሁ ምናችን ነው? ባትጠቅሙን እንኳ ለጉዳታችን ድምፅ ካልሆናችሁ ምንድር ናችሁ?
በጓዳ በዝምታ እየሠራችሁ ይሆን? እንግዲህ በአደባባይ ለተፈፀመ በደል የጓዳ መልስ መፍትሄ አያመጣም። ውጤቱን፣ ፍርድና ዳኝነቱን፣ ሕግና አካሄዱን በአደባባይ አሳውቁ፤ አሰሙን። አለበለዚያ ማዕበል እናስነሳለን ብለን እናስፈራራ ይሆን? ድንጋይ እናንሳ? መብታቸውን ያስከበሩና የተፈሩት እንዲያ ያደረጉት ናቸውና!
እባካችን ሰዎች! ለምን ማለትን ትተን ይበቃል እንበል፤ እባካችሁ ከቤተ መንግሥት እስከ ፍርድ ቤት፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እስከ ወረዳ ያላችሁ ባለሥልጣኒት ሴቶች ይበቃል ከቃል የዘለለ እንዲሆን አድርጉ! እባካችሁ በሴት ልጅ አምላክ!
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014


