“ከኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው አካሏ ተጎድቷል” አራጋው ሲሳይ ጋዜጠኛ

0
919

ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ ይባላሉ። ለበርካታ ዓመታት በመንግሥትና በግል ሚዲያዎች በመሥራት መረጃዎች ለሕዝብ ሲያደርሱና ሕብረተሰብን በሙያቸው ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው። ይህን ዕውቀታቸውን ተጠቅመው የማኅበረሰቡን ችግር ያስተዋሉት እኚህ ባለሙያ፣ በተቻላቸው አቅም ጉዳተኞችንና ድጋፍ ፈላጊዎችን ለመርዳት ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ግብረ -ሠናይ ተቋም መሥርተዋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱን ለመታደግ እንቅስቃሴ የጀመሩ ቢሆንም፣ ወቅቱን በማገናዘብ ትኩረታቸውን በጦርነቱ ለተጎዱ ካደረጉ ሠነባብተዋል። በዚህም ሥራ በርካታ ተጎጂ ያሉባቸውን ሥፍራዎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል፤ ከለጋሾች ያገኙትንም ተቋማቸውን ወክለው በየቦታው በአካል ተገኝተው አድርሰዋል። በዚህ ተግባራቸው ወቅት ስላስተዋሉት ጉዳት፣ እንዲሁም ተጎጂው አሁን ላይ የተካሄዱ ለውጦችን ተከትሎ ምን ዓይነት ሥነ-ልቦና ውስጥ እንዳለ የተመለከቱትን እንዲያጋሩ የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ስለራስዎ ቢያስተዋውቁን?
አራጋው ሲሳይ ነው የምባለው። የወሎ ቤተ-አማራ የበጎ አድራጎት ድርጅት የኮሚቴ አስተባባሪ ነኝ። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እሠራ ነበር። የተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች ላይ ካገለገልኩ በኋላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙሉ ጊዜዬን ወደበጎ አድራጎት ሥራ አድርጌያለሁ። በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ የሚቻልበትን ኹኔታ ለማመቻቸት እየሠራሁ እገኛለሁ።

ከአንድ ዓመት ወዲህ ሙሉ በሙሉ ትኩረቴን ወደበጎ አድራጎቱ አዙሬያለሁ። በአገራችን የተከፈተውን አስከፊ ጦርነት ተከትሎ ለከፍተኛ ሞት፣ መፈናቀል፣ እንግልትና ሥደት የተዳረጉ ወገኖች የሠብዓዊ ዕርዳታና ድጋፍ የሚያገኙበትን ኹኔታ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና ባልደረቦቻችን ጋር በመሆን በመተጋገዝ እየሠራን እንገኛለን። ኹሉም ትኩረቱን ጦርነቱ ላይ አድርጎ የሚሠራ ከሆነ፣ ከጦርነቱ በላይ በረሃብና እንግልት የሚያልቀው ሰው በርካታ ስለሚሆን እነሱ ላይ ትኩረት አድርገን ለመሥራት በማሰብ ነው ማኅበሩን ያቋቋምነው።

አሁን ጦርነቱ ያለበትን ኹኔታ እንዴት ያዩታል?
አሁን ላይ እንደመንግሥት አገላለጽ የጦርነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቋል። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሲተረጎም፣ ጦርነቱ አልቋል ዓይነት ዕሳቤ ያለው ዓይነት አቋም ነው መንግሥት የያዘው። ይሁንና አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ጦርነት እንደቀጠለ ነው። በተለይ በወሎ ራያና አፋር አብዓላ አካባቢ፣ እንዲሁም ሰሜን ጎንደር የአማራ ገበሬ አሉባቸው የሚባሉ አካባቢዎች ላይ የሕወሓት ትህነግ ቡድን ሠፍሮ ሕዝቡን ለከፋ ጉዳት ዳርጎታል። ከዚህ ቀደም ከነበረው የባሰ የከፋ ችግር ላይ ሕብረተሰቡ መውደቁን ማወቅ ተችሏል። አፍኖ መውሰድ፣ መዝረፍ፣ መግደሉና መድፈሩ ተባብሶ ነው የቀጠለው። ከባድ መሣሪያን በመጠቀም ጭምር ንጹኃን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ጭምር እየፈጸሙ ነው የሚገኙት።

ሲጀመር ጦርነቱ አንደኛ ምዕራፍ የሚያስብለው ደረጃ ላይ አልደረሰም። አንደኛ ምዕራፍ ለማስባል አስቻይ ኹኔታዎች ምንድን ናቸው ብሎ መንግሥት ኹኔታዎችን ገምግሞ የተናገረው አይመስለኝም። በግዴለሽነት ወይም እንዳሻው የመናገር ኹኔታ ያለ ነው የሚመስለኝ። የመንግሥት መንበር እስካልተደፈረ ድረስ ወራሪው ደርሶበት ከነበረው ስለራቀና እስካላሰጋው ድረስ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል የተባለ ይመስላል። በተጨባጭ መሬት ላይ ተወርዶ ከሕዝቡ ችግር የሚታየው ግን ጦርነት አልቋል የሚባልበት ኹኔታ ላይ እንዳልሆንን ነው። ጦርነቱ አሁን እንደቀጠለ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

በአንፃሩ ግን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሆነ ቦታ ላይ አልፈው እንዳይሄዱና ባሉበት እንዲረጉ በሚል ትዕዛዝ ቆመዋል። ሕዝቡ ግን በተቃራኒው ለዕልቂት እየተዳረገ እንዳለ ነው እኔ ተዟዙሬ ከተመለከትኩት ለመታዘብ የቻልኩት።

ሕዝቡ ሕይወቱን ሠጥቶ አገርን ከታደገ በኋላ ጦሩ እንዲቆም መደረጉ በሕዝቡ ሥነ-ልቦና ላይ የፈጠረው ምንድን ነው?
ጦሩ ባለበት ይርጋ በመባሉ የተከሠተው ችግር በርካታ ነው። ከቀጠለው የሕዝብ ዕልቂት በተጨማሪ የሚያስከትለው ቀውስም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ችግሩ በይበልጥ የደረሠበት የአማራና የአፋር ሕዝብ እንዲህ መደረጉ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ያጠፋበታል።

ለወደፊት ተስፋ እንዳያደርግና በራሱ ለመከላከል እንዲዘጋጅም ያደርገዋል። መንግሥት ሊታደገው እንደማይችል ሕዝቡ ተረድቶታል። ስለዚህ ለሚመጣው ትግል ራሳቸውን ዝግጁ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው ያሉት። በተለይ የፋኖ አደረጃጀት ከቀበሌ ጀምሮ፣ እስከ ዞንና ክልል ድረስ መዋቅሩን በመዘርጋት ለመሥራትና ተበታትኖ የነበረውን ወደ አንድ ለማምጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ሥልጠናዎችንና በቂ ዝግጅት የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆኑ ተገንዝቤያለሁ። ይህ ሊሆን የቻለው ትልቁ ምክንያት መንግሥት አሁን ሕዝቡን መጠበቅ እንደማይችል ስለተገነዘቡ ነው። ከእንግዲህ ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል መንግሥት ይችላል የሚል አመኔታን ስላጡ ራሳቸውን በራሳቸው ለመከላከል ዝግጅት እያደረጉ ነው ያሉት።

በአንጻሩ የሕወሓት ቡድን ከእስካሁኑ በበለጠ ሁኔታ ራሱን እያደራጀ ነው። የአፋርና አማራ ክልል ይዞታዎች ላይ ጭምር ምሽጎችን በኤክስካቫተር ጭምር እያስቆፈረ ይገኛል። በቅርብ ርቀት የፀጥታ ኃይሎችም እያዩት ይሁንታ የተሠጠው ይመስል ዝም ተብሎ በከፍተኛ ኹኔታ ለዳግም ወረራ እንዲዘጋጅ እየተደረገ ነው።

ወታደራዊው ኹኔታ እንደሚታወቀው የአድርግና አታድርግ ኹኔታ ነው። አድርግ የተባለ ያደርጋል፤ አታድርግ ሲባል ደግሞ ወታደሩ ሥራውን ያቆማል። አፈግፍግም ሲባል ወደኋላ ይሄዳል። ጠላት ከፊታቸው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነገ ሊበላቸው እየተሰናዳ መሆኑን እያወቁ ምንም ማድረግ ሳይችሉ ከርቀት ሆነው እየተመለከቱ ነው። መንግሥት ኢመደበኛ ሲል የሚጠራው አደረጃጀት ከአገላለጹ ጀምሮ ችግር ቢኖርም፣ ሕዝብን ለመታደግ በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው።

ከመንግሥት መዋቅር ውጭ ኾኖ ሲዋጋ የነበረውን ታጣቂ ለመከፋፈልና ለማጥፋት የሚጥሩ እንዳሉ ይነገራል። ይህን ሒደት ሕዝቡ እንዴት ነው የተረዳው?
እነዚህን ታጣቂዎች በተለይም ፋኖ የሚባሉ ትክክለኛ የሕዝብ መሪ የነበሩን ባለፉት ዓመታት እስከመግደል የሚደርስ ዕርምጃ ሲወሰድባቸው ነበር። አደረጃጀቱ እንዲበተን፣ እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ እንዲበላሽ፣ ከሕዝብም ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ሲሠራ ነበር። በዚህም ምክንያት በሕዝብ መካከል ውዥንብር ነበር። “ሊገሏችሁ፣ ሊዘርፏችሁ፣ ሊያግቷችሁ ነው” በሚል ቅስቀሳ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ከሕዝብ ለማራቅና እርስ በርስ ለማጣላት ተሞክሮ ነበር። በዚህ በኩል በተወሰነ ደረጃ መንግሥት ተሳክቶለት ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ምክንያትም በራሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በርካታ የፋኖ መሪዎች የተገደሉበት ጊዜ ነበር።

አሁን ላይ እኔ ባደረኳቸው እንቅስቃሴዎች መረዳት እንደቻልኩት፣ በትልልቅ ውጊያዎች ላይ ከመከላከያና ልዩ ኃይሎች ይልቅ ቀድሞ ከተሞች ላይ ሲገባ የነበረው ፋኖ ነበር። በበርካታ አውደ ውጊያዎች ግንባር ቀደም ሆኖ ሲዋደቅ እንደነበር ሕዝቡ ራሱ ነው የሚመሰክርላቸው። ለአብነት ያህል ደቡብ ምዕራብ ወሎ ግንባር በነበረ ውጊያ ከሌሎች የፀጥታ አካላት በፊት የፋኖ አደረጃጀት ነበር አካባቢዎቹ ገብቶ የተቆጣጠረው። ሕዝቡ እጅግ የተለየ ክብር እንደሚሰጣቸው ነው የተመለከትኩት። ከሌሎች የመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሕዝቡን እንደታደጉት ኹሉም ስለሚያውቅ ሕዝብ ልቦና ውስጥ ገብተዋል። ይህ ኾኖ ሳለ ለማሸማቀቅ የሚሞከረው ነገር እነሱ የሚመልሱበት ቢሆንም፣ በሕዝቡ ዘንድ ግን ተቀባይነታቸውን የሚያሳጣ አይደለም። እንደውም አሁን ሕዝቡ ራሱ ለፋኖ ይከላከላል ብዬ ነው የማስበው። ከእንግዲህ በኋላ ፋኖን ለማሰናከል መሞከር ከሕዝብ ጋር ለመጣላት ማሰብ ነው ብዬ ነው የማስበው።

ወደሕዝቡ ችግር እንመለስና በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበረው ነዋሪ አሁን በምን ኹኔታ ነው ያለው?
እኔ አሁን የወሎ ቤተ አማራ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚባል ማኅበር ውስጥ ኹኜ ነው እየተንቀሳቀስኩ ያለሁት። ድርጅቱ ከአንድ ዓመት በፊት የአንበጣ መንጋ የሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱን ክፍል ባጠቃበት ወቅት ተጎጂ ገበሬዎችን እንታደግ በሚል እነሱን ለመርዳት የተቋቋመ ነበር። አሁን ላይ ግን በተለይ ከጦርነቱ በኋላ የችግሩ አሳሳቢነት እየገፋ በመምጣቱና አስቸኳይ የሠብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ነበረብን። በወቅቱ መንግሥት በሚፈለገው ደረጃ ቀርቦ ሕዝቡን እየታደገ ስላልነበር የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ነበር ስንሠራ የነበረው። በሥራችን ምክንያት በጣም የተለያዩ አካባቢዎችን ዙረን አይተናል። በወሎ ኹሉም ግንባሮች ላይ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ግንባር ዞረን ጉዳቱንም ሆነ የሕዝቡን ነባራዊ ኹኔታ በማየት የቻልነውንም ያህል ለመርዳት በቅተናል። ያሰባሰብነውን ይዘን በየከተማው ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ስናደርግ ነበር።

በሥራችን እንደታዘብነው፣ አሁንም ድረስ አመራሩ ከነበረው ችግር አልተማረም። ለሕዝብ እየተባሉ የሚሔዱ ድጋፎች በትክክል እየደረሱ አለመሆኑን ለመረዳት ችለናል። በእኛ በኩል ያመጣነውን ራሳችን በአካል ቦታው ድረስ እየሔድን ለሚገባቸው ስለምናከፋፍል ምንም ችግር አልነበረብንም። ሌላው በተለይ በመንግሥት በኩል የሚፈጸመው ግን በርካታ ቅሬታ እንደሚቀርብበት ከሰማነው ትችት ለማወቅ ችለናል። መንግሥት ድጋፍ አደረኩባቸው የሚልባቸው ቦታዎች ሔዶ ማጣራት እንደሚቻለው፣ ኹሉም ቦታ ማለት በሚቻል መልኩ ቅሬታ ይቀርብበታል። በተለይ ከጦርነቱ በቅርብ ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች በሚኖሩ ከፍተኛ ቅሬታ ይቀርባል። መንግሥት የሚያሰባስባቸው እህሎች በአግባቡ ለሕዝቡ እየደረሱ ስላልሆነና መጋዘን ውስጥም ስለሚጠራቀሙ ወራሪው ኃይል በደረሰ ቁጥር እንዲወስዳቸው መደረጉ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ብዙ ክፍተት አለ፤ ሕዝቡ ተርቦ እያለቀሰ እህል እንዲዘረፍ ሲደረግ ነበር።

ሌላው፣ የተሰበሰበ ሐብት ባግባቡ እንዲከፋፈል ባለመደረጉ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል። የመንግሥት አመራሩ የሚመጡ ዕርዳታዎችን እንዲሸጡ የማድረግ ሁኔታዎች ነበሩ። በዚህ ጦርነት ወቅት በአሳፋሪ ኹኔታ ያልተማሩ አመራሮች እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ሲሠሩ ነበር። በሦስተኛ ደረጃ የደረሰውን ጉዳትና ውድመት የሚመጥን ድጋፍና አስተዋጽዖ መንግሥት ሲያደርግ አልነበረም። ይህ አቅም አጥቶ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም፣ እኔ ግን በፍፁም አላምንበትም። አቅም ኑሮት ማድረግም እየቻለ ግን በግዴለሽነት ማለት በሚያስችል ኹኔታ ከጦርነት የተረፉ ሕዝቦችን መታደግ አልቻለም። ከሞላ ጎደል ግን፣ የግል ድርጅቶችም ሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ተባብረው አሁን ያለበት ደረጃ ተደርሷል። አሁን ላይ ነው የበለጠ ድጋፍ የሚያስፈልገው።

ተፈናቅሎ የነበረ ተመልሶ ወደየቤቱ ሲገባ ምንም ነገር አላገኘም። የሚቆረጥመው ጥሬ እንኳን የለውም። በወራሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ የሚበላው ተዘርፎ፣ ቤቱ ተቃጥሎ፣ ንብረቱ ወድሞና ተዘርፎ ባዶ ኦና ቤት የጠበቀውም በርካታ ሕዝብ ነው። ቤተሰቡን ያጣ የት እንዳሉ የማያውቅ ብዙ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ዕጦትም እያስጨነቃቸው ነው። የሥነ-ልቦናውንም ሆነ የኢኮኖሚውን ሥብራት ለመጠገን ብዙ መሠራት ይኖርበታል። ለመልሶ ግንባታ የተለያዩ ኮሚቴዎች በመንግሥትም ሆነ በተለያዩ አካላት ሲቋቋሙ ቢሰማም፣ አስፈላጊውን ዕርዳታ ሲያደርሱና ውጤታማ ሲሆኑ ግን አይታይም። ጉዳዩ የኹሉንም ድጋፍ የሚፈልግና ትኩረት ተሠጥቶ ሊሠራበት ይገባል ብዬ ነው የማስበው።

እስካሁን የሚከፋፈሉ ዕርዳታዎች ጊዜያዊ የማቆያ እንደመሆናቸው በቂ አለመሆኑን የሚናገሩ በርካታ ናቸው። አብዛኞቹ ተጎጂዎች መልሰው ሊቋቋሙ የሚችሉባቸው ማረሻ በሬዎችና የሚያረቧቸው ከብቶችን አጥተው፣ እንዲሁም ቤታቸው ተቃጥሎባቸው የሰው እጅ እየጠበቁ እንደመሆናቸው እነሱ በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለመደገፍ የተሠራ ተግባር አለ?
እስካሁን ባለው ኹኔታ እንደዚህ ቋሚ የሆነ የማቋቋም ሥራዎች ላይ የታዘብኩት ምንም ዓይነት ነገር የለም። በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ሰዎችን በማግኘት ስናጠያይቅ መንግሥት ለስድስት ወር የሚሆን እህል በየወሩ 15 ኪሎ ገደማ ስንዴ ሊሰጥ ቃል ከገባው ውጭ ምንም ነገር የለም። ይህ ‹የሴፍቲ ኔት› ዓይነት ድጋፍም ቢሆን ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ አይደለም። በቋሚነት ማቋቋሙ ላይ ግን እስካሁን ድረስ የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ምንም የተረዳሁት ነገር የለም። በተለይ በጦርነቱ በጅምላ ቤቶች የወደሙባቸው አካባቢዎች አፋር ካሳጊታ አካባቢ፣ ወሎ ሐይቅ፣ ሊሶና መርሳ አካባቢ ከፍተኛ ውድመት ተከስቷል። እነዚህ ዓይነት አካባቢዎች ላይ ቢያንስ የክረምቱ ጊዜ ከመምጣቱና የበለጠ ለችግር ከመዳረጋቸው በፊት ከአሁኑ ቢታሰብበት መልካም ነው። መንግሥት በዚህ ደረጃ ይችላል አይችልም የሚለው እንዳለ ሁኖ፣ ጊዜያዊ ተገጣጣሚም ሆኑ ተንቀሳቃሽ ቤቶችን ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር ተጎጂዎች እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል።

አ.ብ.ቁ.ተ. ይባል የነበረው ብድርና ቁጠባ ተቋም እስካሁን ከማንኛውም ባንክ በላይ የወለድ ምጣኔ እያደረገ ሕዝቡን ሲበዘብዝ ነበር። ብዙ አርሶ አደሮች በሥራው ተማረው ሕይወታቸውን እስከማጥፋት ደርሰው እንደነበር የራሱ የክልሉ የመንግሥት ሚዲያ ሲዘግበው የነበረ ነው። አሁን ላይ ግን ስማቸውን የሚያድሱበት ሕዝቡንም የሚክሱበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት የፋይናንስ ተቋማት ከወለድ ነፃ በማድረግም ሆነ አደራጅቶ ድጋፍ በማድረግ በቋሚነት ሕዝቡን ለማቋቋም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሠሞኑን ተጨማሪ በጀት መጽደቁን ተከትሎ በአማራና አፋር ክልል ለወደመው 5 ቢሊየን ብር መመደቡን በማንሳት፣ ከዚህ ቀደም ለትግራይ ከተመደበው በ100 ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ጋር በማነጻጸር ትችት የሠነዘሩ አሉ። እርሶ ይህን እንዴት ያዩታል?
ይህ ነገር ለእኔ በጣም አስቂኝ ነው ብዬ ነው የማልፈው። በጣም ቀልድ የሆነ ድርጊት ነው። የተለየ የበጀት ድጎማ አደረግን ባይሉ ነው የሚሻለው። ይህች የተባለችው ገንዘብ ለአንድ ተቋም መልሶ መገንቢያ አትሆንም። የወሎና ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ለወደመባቸው እንኳን የማትመጥን ናት። በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው። በጦርነቱ አንድ አገር ነው የወደመው ማለት ይቻላል። አፋርና አማራ ክልል የሆነው ሲታይ ከኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው አካሏ ተጎድቷል። ለጉዳቱ 5 ቢሊየን ብር መደብኩ ማለት “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” እንደሚባለው ነው የሆነው።

እንደግለሰብ ሳስበው ኹለቱ ክልሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ለቀጣይ ዓመታት ከግብር ነፃ ሁነው የሚያገኙትን ገቢ በሙሉ ለመልሶ ግንባታ እንዲያውሉት ማድረግ ያስፈልጋል። ከተፈጥሮ ሀብት፣ ከቱሪዝምና ከገበሬውም የሚሰበሰብ ግብር ለራሱ ለክልሉ መልሶ መገንቢያ መሆን ይገባዋል። በዚህ ደረጃ ነው ሠፋ ተደርጎ ለችግሩ መፍትሔው መታየት ያለበት። ተመደበች የተባለችው ገንዘብ እንኳን ለመልሶ መገንቢያ በግንባር ላይ ለወደቁት ሰማዕታት ቤተሰብ መደጎሚያም አትበቃም። የወደሙ ቤቶችንም ሆኑ የፈረሱ ድልድዮችን ማስጠገን የማይችል ገንዘብ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲሰሙ ምን ሊሉ ነው፣ በጣም ያሳፍራል።

የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ጦርነቱ እንዳላለቀ እነሱም ያውቁታል። በተለይ የአፋርና አማራ ሕዝብን ለመጨረስ አሁንም ድረስ ባለህበት ዕርጋ ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቶ ከማየትና ከእነዚህ ሰዎች ጋር እንዲህ እንደሠሞኑ ዓይነት ነገር ተፈጥሮ ሠላም ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ፣ እስከመጨረሻው ጠፍተው ከሕዝቡ ጋር ሠላም የሚወርድበት ኹኔታን መንግሥት ለራሱ ሲል ቢሠራበት ይሻላል። በኹለተኛ ደረጃ፣ እዚህ መከራ ላይ የተጣደ ሕዝብ አሁንም መልሶ የማቋቋም ሒደት ላይ ተመልሶ የሞራል ሥብራት እንዳይገጥመው መጠንቀቅ ይገባል። ከቀልድና ፌዝ ወጥቶ ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተገብቶ ሕዝብን መታደግ ይገባል እላለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here