የመንግሥት ተጨማሪ በጀት እና የዋጋ ግሽበት

0
1045

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ጥር 20/2014 ባደረገው ልዩ ስብሰባ ተጨማሪ በጀት ማጽደቁ ይታወሳል። በዕለቱ የፌዴራል መንግሥት የ2014 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ ዐዋጅን መርምሮ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

የጸደቀው ተጨማሪ በጀት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በጦርነት ክፉኛ መጎዳቱን ተከትሎ ተገቢ ነው ቢባልም፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ሐሳብ ከተለያዩ አካላት ቀርቦበታል። ከተሠነዘሩ አስተያየቶች ውስጥ ዋነኛው ከኢኮኖሚው ያልመነጨ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ሲደረግ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል ይችላል የሚለው ነው።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ትልቁ ችግር አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ስለሆነ፣ የአገሪቱ የማምረት አቅም ካልጨመረና በተለያዩ መንገዶች የአገሪቱ የውስጥ እና የውጭ የገቢ አቅም ካልጎለበተ ተጨማሪ በጀት በመያዝ የተጎዳውን ምጣኔ ሀብት ማከም እንደሚያስቸግር የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ።

መንግሥት ያለበትን ሠፊ የበጀት ጉድለት ለመሙላት አቅም ላይኖረው ስለሚችል ተጨማሪ በጀት መመደቡ አስፈላጊ የሚባል ቢሆንም፣ ትልቅ አደጋ ይፈጥራል የሚባለው ግን ይህ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት የሚመጣበት ምንጭ ነው።

በረቂቅ ዐዋጁ ላይ የተጨማሪ በጀት ብሩ ከአገር ውስጥ ብድር እንደሚገኝ ነው የተገለጸው። ገንዘብ ሚኒስቴርም በወቅቱ ለምክር ቤቱ በሠጠው ማብራሪያ አዳዲስ ገንዘብ እንደማይታተም ነው ያስረዳው። ተጨማሪ በጀቱ ከአገር ውስጥ እና ከቦንድ ሽያጭ ሊገኝ እንደሚችል ቢጠቆምም፣ ይህ ነገር በታማኝነት ስለመፈጸሙ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል እና እንደ አገርም ጤናማ የተጨማሪ በጀት ምንጭ አለ ብሎ ለመውሰድ እንደሚያስቸግር ነው ብዙዎች የሚናገሩት።

ይህም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የምትከፍለው ብድር ያለባት በመሆኑ ኢኮኖሚው ጫና ውስጥ እንዳለና አዳዲስ ብር መታተሙ አይቀሬ እንደሆነ የሚናገሩ አካላት አሉ።

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አጥላው አለሙ (ረ/ፕሮፌሰር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ተጨማሪ በጀት መያዙ ሳይሆን ገንዘቡ ከየት ነው የሚገኘው የሚለው ነው ወደ ዋጋ ግሽበት ሊመራን የሚችለው ይላሉ። በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ገንዘብ መኖሩ ይታወቃል፤ ይህን ገንዘብ ከአንዱ ወደ ሌላው በማዘዋወር ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ ግሽበት አይፈጠርም ባይ ናቸው።

መንግሥት ከግል የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ከባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ከጡረታ እንዲሁም ከባለሀብቶች በብድር መልክ ገንዘብ እየወሠደ የሚጠቀም ከሆነና ኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ ሳይጨመር ባለው መሥራት እስከተቻለ ድረስ የሚፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ማስቀረት ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም ውጭ ብዙ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች አሉ የሚሉት መምህሩ፣ ከእያንዳንዱ ሰውና ከትናንሽ የሀብት ምንጮችም ገንዘብ በመሰብሰብ ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል ብለዋል።

እንዲሁም፣ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመጠገን ተብሎ ከውጭ በዓይነት ተገዝተው የሚገቡ ዕቃዎችና ማሽነሪዎች የዋጋ ግሽበት ስለማያስከትሉ ይህንም እንደ አንድ የመፍትሔ አማራጭ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ መንግሥት ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ በሚሠራቸው አንዳንድ ነገሮች ስለማይስማሙ ገንዘብ አይሰጡም እንጂ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ውስጥ ሀብት ለማፍሰስ (ኢንቨስት ለማድረግ) የሚያስቡ ስላሉ ይህን ዕድል መጠቀም ይቻል ነበር በማለት ያስረዳሉ።

በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ደመላሽ ሀብቴ (ዶ/ር) ተጨማሪ በጀቱ የሚመጣበት ምንጭ ነው ለዋጋ ግሽበት የሚዳርገው ሲሉ ገልጸው፣ በአንድ አገር ውስጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ አለ የሚባለው ያለው ምርትና አገልግሎት ካለው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን ነው ብለዋል።

ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ኹኔታ በጦርነት፣ በድርቅና ኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርትና አገልግሎትን ለማሳደግ የሚቻልበት ምቹ መደላድል የለም። ይህ ችግር እያለ የገንዘብ መጠን ብቻ ሲጨመር ግሽበት ይፈጠራል ባይ ናቸው።
ብዙ ጊዜ በሌሎች አገሮችም እንደሚደረገው ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ገንዘብ ይታተማል። ይህም ለመንግሥት አንዱ የገቢ ማግኛ ዘዴ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ሚዛኑን በማዛባት የነበረውን ግሽበት እንደሚያባብስ አስረድተዋል።

መንግሥት ተጨማሪ በጀቱን ከአገር ውስጥ ብድር መሸፈን ከቻለ ግሽበት አይፈጠርም የሚሉ ምሁራን ቢኖሩም፣ ደመላሽ ግን ይህ በራሱ ሌላ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያስከትል ጠቁመዋል። እኛ ባንኮች ውስጥ የምንቆጥበው ገንዘብ ለግሉ አምራች ዘርፍ በብድር የሚቀርብ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥትም ተበዳሪ ከሆነ የግል አምራች ተቋማት በገንዘብ ዕጥረት ሊገፉና ምርት እንዳያድግ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ነው የገለጹት።

መንግሥት ተጨማሪ በጀቱንም ይሁን ሌላ ገቢ ለማግኘት፣ ቦንድ ለአገር ውስጥና ለ ውጭ አገር ገበያ ለሽያጭ በማቅረብ፣ ንብረት በመሸጥ፣ የልማት ተቋማትን ለግሉ ዘረፍ ክፍት በማድረግ ገንዘብ መሰብሰብ ይችላል ነው ያሉት መምህሩ።

ምክር ቤቱ ተጨማሪ በጀቱን ባጸደቀበት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሠጡት የገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ አሁን ካለው የባሰ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊያጋጥማት የሚችልበት ኹኔታ ውስጥ ገብታ እንደነበር ገልጸው፣ መንግሥት በወሰዳቸው የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ግሽበቱን መቆጣጠር በመቻሉ ኹኔታው ሳይከሠት መቅረቱን አስረድተዋል። በዚህም ተጀምረው ያሉና መዘግየት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን እንዲዘገዩ በማድረግ፣ ሊሠሩ የታቀዱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማቆየት እና የመንግሥት ወጪዎችን በመቀነስ ችግሩን ለመከላከል ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል።

ሆኖም ግን፣ ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩ መደረጉ የአገሪቱን የመልማት አቅም የሚጎዳና ገቢ የሚያሳጣ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ፕሮጀክቶቹን ከሆነ ጊዜ በኋላ እንደገና በማስቀጠል ለማጠናቀቅ በሚሞከርበት ጊዜ ተጨማሪ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ጫና የጎላ እንደሚሆንና ያለውን የኑሮ ውድነትም በዘላቂነት ለማስተካከል አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የምጣኔ ሀብት ባላሙያዎች ሳይገልጹ አያልፉም።

የበጀት ጉደለትና የዋጋ ግሽበት
ለ2014 የተመደበው በጀት 561 ቢሊዮን ብር (ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ) መሆኑ አይዘነጋም። ከተጨማሪው 122 ቢሊዮን ብር ጋር ደግሞ ከሰኔ 30 በፊት 683 ቢሊዮን ብር የዓመቱ በጀት መሆኑ ነው። ይህም ከሰኔ 30 በፊት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ካላስፈለገ ነው። ሆኖም መንግሥት ሠፊ የበጀት ጉድለት እንዳለበት ይነገራል።

የምጣኔ ሀብት መምህሩ የበጀት ጉድለት አንዱና ዋነኛው የዋጋ ግሽበት ገፊ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። መንግሥት ብዙ ፕሮጀክቶችን በየቦታው ይወጥንና የበጀት መስመሮችን በተለያዬ ቦታ በመክፈት ይህን ለማስፈጸም ገንዘብ ያሳትማል ወይም ከውጭ ገንዘብ ይበደራል። ይህ ላለፉት 27 ዓመታት በስፋት ይሠራበት የነበረና መዘዙም ሲንከባለል መጥቶ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት እንዳስከተለ አመላክተዋል።

አሁን ላይ በተፈጠረው የበጀት ክፍተትም በተለይ የአማራና አፋር ክልሎች ተጎጅ በመሆናቸው ከሌሎች ክልሎች ያለውን ገንዘብ በመዋዋስ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

አማራ ክልል የሕወሓትን ኃይል ሒሳባችሁን አዲስ አበባ ገብታችሁ አወራርዱ ብሎ ያለ ውጊያ ቢያሳልፋቸው ኖሮ፣ አፋርም የሚሌ መስመር እንዳይያዝ ያን ያህል ዋጋ ባይከፍል ኖሮ ችግሩ አገራዊ ሆኖ ኹሉም ክልሎች ተጎጅ ይሆኑ ነበር። ስለዚህም ሙሉ በጀታቸውን ለጦርነት አውለው በተጎዱት አፋርና አማራ ክልሎች ላይ ያለውን ሠፊ የበጀት ጉድለት በጋራ መሙላት እንደሚገባ አሳይተዋል።

ደመለሽ ሀብቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመንግሥት የበጀት ጉድለት የሚመጣው የሚሠራው ሥራና ያለው ገንዘብ ሳይመጣጠን ሲቀር ነው ብለዋል። የመንግሥት ገቢ ማግኛ መንገዶች በዋናነት ኹለት ሲሆኑ እነሱም፣ ከግብር የሚገኝ ገቢ እና ግብር ነክ ባልሆኑ መንገዶች የሚሰበሰስ ገቢ ማለትም፣ ከልማት ድርጅቶች፣ ከአገልግሎት አሠጣጥ፣ እንዲሁም ከቅጣት እና ሌሎች የገቢ መሰብሰቢያ መንገዶች የሚገኝን ገቢ ማለታቸው ነው።

ሆኖም መንግሥት በእነዚህ ኹለት ዋና ዋና መንገዶች የሰበሰበው ገቢ ለልማት ሥራው ሳይበቃው ሲቀር ጉድለት አጋጠመው እንደሚባል አውስተዋል። ይህም ከዋጋ ግሽበት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጠቁመው፣ ጉድለቱም መንግሥት የሚጠበቅበትን የልማት ሥራ በደንብ ሳይሠራ ሲቀርና ዋነኛ የገቢ ምንጩ የሆነውን ግብር ሳይሰበስብ ሲቀር መሆኑን አንስተዋል። በዚህ ጊዜ ብድርን እንደ ሠፊ አማራጭ ስለሚጠቀም ወደ ኢኮኖሚው ተጨማሪ ገንዘብ በማስገባት የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠርና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በር ይከፍታል ሲሉም አብራርተዋል።

በበጀት ጉድለት ኹሉም የአፍሪካ አገራት እንደሚሰቃዩ ያወሱት መምህሩ፣ በማጠቃለያቸው ደካማ የሆነው የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት በዓለም አቀፉ አበዳሪ ተቋም ( IMF) ተደግፎ እንደሚኖር አመላክተዋል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ምን ያህል በጀት ያስፈልጋል?
ተጨማሪ በጀቱ ያስፈለገበት ምክንያት በዋናነት ለአገር ደኅንነት ማስጠበቂያ ይሆን ዘንድ በዋናነት ለመከላከያ ሠራዊቱ ትጥቅና ስንቅ ለማሟላት፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ በተለይም ለዜጎች የዕለት ዕርዳታ የሚውል የስንዴና አልሚ ምግብ ግዥ ለማከናወን፣ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት መሆኑ በረቂቅ ዐዋጁ ላይ ተገልጿል።

ሆኖም፣ በጦርነቱ ምክንያት በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ መሠረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ለማድረግ እና ማኅበረሰቡም ወደ ቀድሞ አኗኗሩ እንዲመለስ ለማስቻል ከአጠቃላይ ተጨማሪ በጀቱ አምስት ቢሊዮን ብር ብቻ ነው የተያዘው።
ይህም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ ገንዘብ ጦርነቱ ውድመትና መፈናቀል ያስከተለበት የአንድን ቀበሌ ማኅበረሰብ እንኳን ወደ ቀድሞ አኗኗሩ መመለስ እንደማይቻል ነው የጥፋቱን ጥልቀትና አስከፊነት በሚያውቁ አካላት የሚነገረው።

ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች እንደሚያመላክቱትም፣ በአፋር እና በአማራ ክልል ሕወሓት በፈጸመው ወረራ የግብርና ተቋማት፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን፣ ለአብነትም በተለያዩ ቦታዎች በሦስት የተለያዩ መንግሥታት ዘመን በኖሩ የግብርና የምርምር ተቋማት ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወድሟል።

ከጦርነት ነጻ በወጡ እና መልሶ ግንባታ ይካሄድባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች የሚገኘው ማኅበረሰብም አሁን ያለበት ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የአማራ ክልል መንግሥትም በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት መውደሙን እና በሠላሳ ዓመት ወደ ኋላ እንደተመለሰ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በትክክል ቢጠና ከ500 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ሀብት ሳይወድም እንደማይቀር በምክር ቤቱ አባላት ተጠቁሟል።

ይህ ባለበት ኹኔታ በኹለቱ ክልሎች ለሚገኙ ለእነዚህ የወደሙ አካባቢዎች የተመደበው አምስት ቢሊዮን ብር ለምንም እንደማይሆን ነው የተገለጸው።

የምጣኔ ሀብት መምህሩ አጥላው በዚህም ላይ በሠጡት ሀሳብ፣ በመቶ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በወደመባቸው አካባቢዎች አምስት ቢሊዮን ብር መመደብ ለይምሰል ካልሆነ በስተቀር ከደረሰው ጉዳት አንጻር ገንዘቡ ምንም አያሠራም ነው ያሉት።
ሆኖም መንግሥት በራሴ አቅም የመልሶ ግንባታ ሥራውን እወጣዋለሁ ከማለት ይልቅ ሕዝቡንም ወደ ጥሩ መንፈስ አስገብቶ ተሳታፊ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል። በጋራ በመሆን የአክስዮን ተቋማት እንዲገነቡ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት መምህሩ፣ በውጭ የሚኖሩ

ኢትዮጵያውያንም አገሬ ብለው እንዲያስቡ ከተደረገ እና መንግሥት ታማኝ ከሆነ ለመልሶ ግንባታው ድጋፍ ያደርጋሉ። በተጎዱ አካባቢዎችም ሀብት እንዲያፈሱ (ኢንቨስትም) ማድረግ ይችላል ሲሉ አክለዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ታማኝ መሆን ስላልቻለና፣ ራሱም ወደ ጥሩ መንፈስ ስላልገባ ይህን ማድረግ ያዳግታል በማለት ይሞግታሉ። መንግሥት አንዴ ጦርነቱን ሳይጨርስ ጨርሻለሁ ይላል፤ አንዴ ድርድር ሊኖር ይችላል ይላል፤ በዚህም ጦርነቱ ሳያልቅ አልዋጋም ብሎ በማቆሙ ሕዝቡን በሥጋት ውስጥ እንዲኖር ከማድረጉም በላይ፣ ቀጣይ ወረራ እንደማይኖር አስተማማኝ ኹኔታ ሳይኖር ማን በእዚያ አካባቢ ኢንቨስት ያደርጋል? ማንስ ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል? የሚል ጥያቄ አላቸው።

ደመላሽ ሀብቴም በበኩላቸው፣ በኹለቱ ክልሎች የደረሰው ጠቅላላ ጉዳት በጥንቃቄ ተጠንቶ ሳይታወቅ፣ አምስት ቢሊዮን ብር መድቤያለሁ ማለት ተገቢነት እንደሌለው ሳይገልጹ አላለፉም። በዚህም የተመደበው ብር ከሚያስፈልገው ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ከመንግሥት በኩል በተሠጠ ምላሽ፣ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቱ ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት የሚፈጅ በመሆኑ፣ ከዘንድሮው ዓመት በጀት ላይ አምስት ቢሊዮን ብር ለሥራው ማስጀመሪያ ከመንግሰት ግምጃ ቤት እንደተመደበ ገልጿል።

እንዲሁም የተመደበው አምስት ቢሊዮን ብር በቂ ነው ባይባልም፣ ከግሉ ዘርፍ የተለያዩ አካላት እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም በመልሶ ግንባታ ሥራው በተናጠል ተሳትፎ ያደርጋሉ ሲል መንግሥት ተጨማሪ ማሳመኛ ያለውን ሐሳብ አቅርቧል።

ጦርነት ከተከሠተበት አካባቢ ውጪ ካለው ኢኮኖሚ ባሻገርም፣ በሱማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተከሠተው ድርቅ ምክንያት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ከተጨማሪ በጀቱ የተወሠነ ፈሰስ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው አልቀረም። ይህም ብቻ ሳይሆን በቤኒሻንጉል እና በኦሮሚያም በታጣቂዎች የወደሙ በርካታ መሠረተ ልማቶች እና የተጎዱ ማኅበረሰቦች በመኖራቸው ለእነሱም ከፌዴራል መንግሽት በቀጥታ ድጎማ ለማድረግ አለመታሰቡ ስህተት ነው የሚሉ አሉ።

ጦርነቱ አሁንም ቢሆን ያልተቋጨ በመሆኑም፣ የክልል የፀጥታ ኃይሎችም (በተለይም የአፋርና አማራ) የሚያደርጉት ተሳትፎ ጉልህ እና ወሳኝ መሆኑን ተከትሎ ለእነሱም ከተጨማሪ በጀቱ የተወሰነ የማጠናከሪያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተነሳው።
የፌዴራል መንግሥቱ በቀጥታ ለክልል የፀጥታ ኃይል ድጋፍ እንደማያደርግ በሕግ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ኹለቱ ክልሎች የተመደበው ዓመታዊ በጀት ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ እና የፀጥታ ኃይላቸውን ለማጠናከር በቂ እንደማይሆን ይነገራል።

በምክር ቤቱ ስበሰባ ላይ አፋር ክልል ቀደም ብሎ በጎርፍ እና በአምበጣ የተጎዳ ክልል ሆኖ ሳለ ከፌዴራል መንግሥቱ ድጎማ እንዳልተደረገለትና በሕወሓት ወረራም ሠፊ ጉዳት ማስተናገዱ ተገልጿል። በአማራ ክልልም በተመሳሳይ በአንዳንድ ቦታዎች ከሚከሠቱ ሠው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የላቀ በጦርነቱ ጥልቅ የሆነ የኢኮኖሚ ድቀት እንደደረሰበት የሚታወቅ ነው።

በአጠቃላይ፣ በኹለቱ ክልሎች የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ኢኮኖሚው እንዲቃና በማድረግ ማኅበረሰቡን ወደ ቀድሞ አኗኗሩ እንዲመለስ ከተፈለገ፣ አለባብሶ ከማለፍ እና ለምንም የማይሆን ገንዘብ መድቤያለሁ ከማለት ይልቅ፣ ከተለመደው ስሌትና ትኩረት ወጣ ብሎ ማየትና መሥራት እንደሚገባ የብዙዎች ምልከታ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here