በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ የኢትዮጵያ ባንኮች እንዳይንቀሳቀሱ ዘግተዋቸው ከነበሩትና በመጨረሻ እንዲከፈቱ ካደረጓቸው በክልሉ ከተከፈቱት አካውንቶች መካካል፣ የሕብረት ባንክ አካውንቶች እስካሁን ባለመከፈታቸው ደንበኞቹ ብራቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የኢንተርኔት ግንኙነት አገልግሎት በመቋረጡ ኹሉም በክልሉ የተከፈቱ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን፣ ደንበኞች በተደጋጋሚ ባነሱት ቅሬታ መሠረት በትግራይ ክልል የተከፈቱ የብዙዎቹ ባንኮች አካውንቶች እንዲከፈቱ ተወስኖ ደንበኞች አገልግሎት እያገኙ ቢሆንም፣ የሕብረት ባንክ ግን እንደተዘጋ ስለቆየ ብራቸውን ማግኘት አለመቻላቸውን ነው አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ያረጋገጠችው።
በትግራይ ክልል የተከፈቱ የኹሉም ባንኮች የደንበኞች አካውንቶች በክልሉ ውስጥ በተፈጠረው የግንኙነት መቋረጡ ምክንያት በባንኮቹ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ተዘግተው ቢቆዩም፣ ከሐምሌ 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ ባንኮች አግደዋቸው የነበሩ አካውንቶችን ከፍተው (ለአብነትም የንግድ ባንክ ደንበኞች አዲስ አበባ በሚገኘው ጎተራ ቅርንጫፍ) ደንበኞች አገልግሎት ማግኘት እንደጀመሩ አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ አይዘነጋም።
በወቅቱ በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ተዘግተው የነበሩ አካውንቶች እንዲከፈቱ ተደርገው ደንበኞች አገልግሎት እያገኙ ቢሆንም፣ ሕብረት ባንክ ግን ትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶችን እስካሁን እንዳልከፈተላቸው እና ከአምስት ወር በላይ ብራቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የተከፈቱ የንግድ፣ የአዋሽ እና ወጋገን ባንክ አካውንቶች ማጣራት እየተደረገ እገዳቸው ተነስቷል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የሕብረት ባንክ አካውንቶች ግን እስካሁን እንዳልተከፈቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ቅሬታቸውን ወደ ተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት ሔደው ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ እንዳልተሰጣቸውና መቼ አካውንታቸው ሊከፈት እንደሚችል እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል።
ከንግድና ወጋገን ባንክ በተጨማሪ፣ ተዘግተው የቆዩ የአዋሽ እና አቢሲኒያ ባንክ አካውንቶች ተከፍተው የደንበኞችን ብር ከመመለሱም ባሻገር፣ ደንበኞች የተቋረጠባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን፣ ሕብረት ባንክ ግን መፍትሔ ለመስጠት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ እንዳልሆነ ወደ ዋና መሥሪያ ቤቱ አቅንተው ያረጋገጡ ቅሬታ አቅራቢዎች አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል የተከፈተ አካውታቸው ተዘግቶባቸው ከነበሩት የንግድ ባንክ ደንበኞች መካከልም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩ አካውንታቸው ተከፍቶላቸው እስከዚህ ሰዓት ድረስ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ግለሰቡ አክለውም፣ ባለቤታቸው በትግራይ ክልል የከፈቱት የሕብረት ባንክ አካውንታቸው እስካሁን እንዳልተከፈተላቸው እና ማንቀሳቀስ እንዳልተፈቀደላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሌላኛው በትግራይ ክልል መቀሌ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ ኤፍሬም አስፋው የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ የራሳቸውን ጨምሮ የበርካታ ተማሪዎች ብር እንዳልተመለሰላቸው ገልጸዋል።
ሕብረት ባንክ ከሌሎች ባንኮች ተለይቶ ገንዘባችንን የማይመልስበት ምን ምክንያት አለ ሲሉ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ብራቸው እንዲመለስላቸውና በከፈቱት አካውንት እንዲጠቀሙ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።
አዲስ ማለዳ ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ወደ ሕብረት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በአካል ያቀናች ሲሆን፣ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በባንኩ ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ ሠራተኛ ጉዳዩ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌሎች ባንኮች የተዘጉትን አካውንቶች ከፍተው ለደንበኞቻቸው አገልግሎት መስጠት ሲችሉ ሕብረት ባንክ ለምንድን ነው እስካሁን የዘገየው? ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄም፣ በክልሉ አለመረጋጋት ስላለ የደንበኞችን ብር ማረጋገጡ ጊዜ እንደወሰደ ነው የባንኩ ሠራተኛ ያስረዱት።
አክለውም ሕብረት ባንክ በትግራይ ክልል ከ20 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት ገልጸው፣ ብራቸው ያልተመለሰላቸው ደንበኞችን ቁጥር ማስታወስ እንዳልቻሉ እና በቅርቡ ብራቸው እንዲመለስላቸው በማኔጅመንቱ በኩል ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ገንዘባቸው አይቀርባቸውም የሚሉት የባንኩ ባልደረባ፣ በከፍተኛ ማኔጅመንቱ የተያዘው ውይይት እንዳለቀ በቅርቡ ጉዳዩን እናሳውቃለንም ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014



