በአዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪስት ፍሰቱ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

0
761

ከተቋቋመ ኹለት ወር የሆነው አዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ የቱሪስት መስኅቦች ያሉት ቢሆንም፣ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዕጥረት በመኖሩ የቱሪስት ፍሰቱ ከሚገባው በታች መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ ፋንታሁን ብላቴ እንደተናገሩት፣ ክልሉ በተለይ በተፈጥሮ ሀብቱ ከሌሎች ክልሎች ለየት ያለ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ለቦታው የተሠጠው ትኩረት አነስተኛ የነበረ በመሆኑ እና የመሠረተ ልማት ተደራሽነትም ስሌለለው የቱሪስት ፍሰቱ ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ ከፍተኛ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር አለ ያሉት ኃላፊው፣ ወደ ቦታው ቀርቦ የማልማት ዕሳቤ ችግር በመኖሩም በቂ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዳልተፈጠረ አመላክተዋል።

በዚህም፣ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ የቱሪስት መዳረሻዎች ቢኖሩም፣ መንገዶች እና ማረፊያ ሎጅዎች ባለመኖራቸው ቱሪስቶች እንደልባቸው ወደ ቦታዎቹ ማቅናትና እዚያም አርፈውና ተዝናንተው ለመመለስ የሚያስችላቸው ምቹ ኹኔታ የለም ሲሉ ገልጸዋል።

ኃላፊው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልል የተለያዩ ፓርኮች ያሉ ሲሆን፣ ለአብነትም ከኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በተጨማሪ፣ ተራማጅና ተሳቢ እንስሳት፣ ጉማሬዎች፣ አዞዎችና፣ ብርቅዬ አሳዎች በውስጣቸው የያዙ ከስድስት ያላነሱ የተፈጥሮ ሐይቆችን የያዘው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መኖሩን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም፣ አግራሞትን የሚቸር የደን ሽፋን መኖሩን አመላክተው፣ በሸካና በከፋ አካባቢዎች በዓለም አቀፉ የባህል ሳይንስና ትምህርት ተቋም (UNESCO) የተመዘገቡ ጥብቅ ደኖች በስፋት መኖራቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም፣ ነባር ቅርሶች፣ ፍል ውኃዎች፣ የተፈጥሮ ሐይቆች፣ በአንድ ሥፍራ ብቻ ከ4 ሺሕ እስከ 5 ሺሕ የሚደርሱ የዱር እንስሳት ያሉበት የጎሽ መንጋ እንዳለም ነው የተናገሩት።

በአፍሪካ ደረጃ በመጥፋት ላይ የሚገኘው የአፍሪካ ጥቁር ዝሆንም በዚሁ ክልል ከ700 በላይ እንደሚገኝ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በክልሉ ብዙ ቦታዎች ከዓመት እስከ ዓመት ዝናብ እንደሚጥልና፣ በተለይ ወደ ኮይሻ አካባቢ እጅግ ልዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በቤንች ሼኮና በምዕራብ ኦሞም እንዲሁ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
አክለውም፣ የጥንት አባቶቻችንን የሕንጻ ጥበብ የሚያሳይ ነው ያሉትን እና 25 ኪሎ ሜትር አካባቢ አግድም የሚረዝመው ‹ሐላል ኬላ› የተሰኘው በእጅ የተሠራ የድንጋይ ካብም፣ በአዲሱ ክልል የሚገኝ ድንቅ የቱሪስት መስህብ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ይህን ኹሉ የታደለው ክልል ትኩረት ተነፍጎት በመኖሩ ባክኖ እና መክኖ ነው የኖረው የሚሉት ኃላፊው፣ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ለማድረግ ቢሮው ልዩ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ክልሉም በቅርብ የተቋቋመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ የፋይናንስ፣ የሎጅስቲክስ እና የሰው ኃይል ዕጥረት እንዳለበት ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here