የ“ሰካራም ስንኞች” ግጥም መጽሐፍ ዳሰሳ

0
1667

በአንድ የሥነ-ጽሑፍ ሠው ጥቆማ ሠጭነት በ 2012 የታተመውን የሣራ ሞገስን “ ሰካራም ስንኞች” የተሰኘ ግሩም የግጥም መድብል አነበብኩ። ማንበቤ ባልቀረ፣ ነገር ግን እጅግ ከመመሰጤ የተነሳ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ ደገምኩት። ከዚያም ለምን የበኩሌን አልልም በማለት ይህቺን ዳሰሳ ጻፍኩ። እነሆ ፡-

በአንድ የሥነ-ጽሑፍ ሠው ጥቆማ ሠጭነት በ 2012 የታተመውን የሣራ ሞገስን “ ሰካራም ስንኞች” የተሰኘ ግሩም የግጥም መድብል አነበብኩ። ማንበቤ ባልቀረ፣ ነገር ግን እጅግ ከመመሰጤ የተነሳ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ ደገምኩት። ከዚያም ለምን የበኩሌን አልልም በማለት ይህቺን ዳሰሳ ጻፍኩ። እነሆ ፡-

ሣራ አንድ ተጨማሪ የሥነ-ጽሑፍ እናት ሆና ተከስታለች። ሣራ ሕይወትን በየዘረፉ በራሷ ዕይታ ተመልክታ አጋርታናለች። ዘመንን፣ አገርን፣ እናትነትን፣ ወጣትነትን፣ ሴትነትን፣ ጽናትን፣ ፍቅርን፣ ትዝታን፣ የፍቅርን ንረት፣ መጣላትን፣ መለያየትን፣ ናፍቆትን፣ ተስፋንና ቀቢጸ ተስፋን በራሷ መንገድ ዐይታ፣ ይሄው እናንተ ደግሞ የምትሉትን በሉ ብላናለች።…ይሄው!

እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ ማራኪ ግጥሞችን የሠጠችንን ያህል፣ ቢታረሙ የምንላቸውንም አንዳንድ ሥራዎች ደርሳለች። ወጣትነትን ከዘመን መንፈስ ጋራ አጋምዳለች። ወጣትነትን ከመዝናናት ባለፈ ሕይወት ተቀኝታለች። አንድ ተጨማሪ ዕይታ፤ አንድ ተጨማሪ መንገድ፤ አንድ ተጨማሪ ሥራ በማበርከት አንድ ተጨማሪ የሥነ-ጽሑፍ እናት ሆና ተከስታለች።

የሚነበብ ገጸ ሽፋን
የፊት ገጽ የሽፋን ሥዕልን እንደ ድንቅ መግባቢያ በአንድ ግጥም ገልጻዋለች። የመጽሐፉን ሙሉ ይዘት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሊገልጥ በሚችል ማራኪና ዐይነ ግቡ የሆነ የሽፋን ሥዕልን መርጣለች። ስድሳ ስምንት (68) ግጥሞችን በ69 ገጾች ቀንብባ አቅርባልናለች። ሰዓሊ ወንድወሰን ከበደና የግራፊክስና ዲዛይነር ባለሙያው ግዛው ለገሰ ሳቢ በሆነ መንገድ መርጠው፣ ሥለው፣ አቀናብረው ለኛ ዕይታ አቅርበዋል። የሽፋን ሥዕሉ “ወይን ጠጅና እኔ” የተሰኘውን ግጥም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲገልጥ ሆኗል። የተሳካለት ምጥን፣ ገላጭ፣ የሽፋን ገጽ ሥራ ነው። እነሆ ግጥሙ፡-
“ ንፋስ የሚተፋ ትልቅ ሰፊ ባህር
ግማሸ የጠለቀች የቪርጎ ፀሃይ ስር
ለብ ያለ አሸዋ ላይ ሁሉ ተሰናድቶ
በረጨሁት ሽቶ አየሩ ተሞልቶ…” (ገፅ 3)

አንዲት አፍቃሪ አንስት፣ አንዲት አፍቃሪ አገር፣ ራሰዋን በከፊል የተገላለጠች፣ በውስጥ ልብስ ብቻ፣ ከፊል የደበዘዘ አረንጓዴ ውስጥ ሱሪዋ በስሱ የሚታይ፤ ባዘቀዘቀች ጀንበር፤ ለብ ባለ አሸዋ ፤ ከፊቷ በሰፊው የተዘረጋ ባህር፤ ብቻዋን ፤ በቀኝ እጇ መሃል የተቀጣጠለ ነገር ግን ጎደለ የማይባል ሲጋራ (ለምን በቀኝ ዕጅ ?)፤ በቀኝ በኩል ስድስት የተጨሱ ቁርጥራጭ ሲጋራዎች በሲጋራ ማጨሻ ራሶች ካልተጨሱት ተለይተው ይታያሉ። ተጠቅማ የጣለቻቸው የተበታተኑ ጥቅም አልባ ሲጋራዎች፤ … እሷ በግጥሟ አሸዋ ላይ ነው ያለሁት ትበለን እንጂ፤ ባንኮኒም ላይ ወይም ቤት ውስጥ የመሆን ዕድል አላት፤ የት እንደሆነች ልንገምት እንችላለን። የምትሻው ይሁን የምትጠብቀው አንድ ነገር ያላት ይመስላል። ከወገቧ በላይ ይበልጥ ጠቆር ያለ፣ ከወገቧ በታች የበለጠ የፈካ ራቁት ገላዋ ይታያል። ይሄ ምንን ሊያመለክት ይችላል? የሰራ አካላቷ ከወገቧ በላይ መሆኑ ነው ወይስ ዓይን ራሮት፤ በወንድ ልጅ ምኞት የጠቆረ የሴት ገላ ? እንቀጥል፡-
“…ትንሽ የጎደለ ውድ የጠርሙስ ወይን
ጋማ የለበሰ ከፊል ራቁት ጭን
ትኩስ ስሜት እና ወይን ያራሰው ከንፈር
የስቲቭ ዎንደር ዘፈን ከቀሉ ጉንጮች ጋር
በሽቶ የራሰ ጠረኔን አሽጌ
የቀይ ከንፈር ማተም አኑሬ ከግርጌ
ከኔ ወደ ባህሩ በሚነፍሰው ንፋስ
ያው ልኬልሃለሁ ናሌቱ ላይ ንገስ
ምሽቱ ሲጀመር በአዲሱ ጨረቃ
ናፍቆትህ ሳይገድለኝ ቶሎ ናልኝ በቃ” (ገፅ 3)

የተመሳቀለ ግራ እግር ጣቶቿ ጎን የጎደለ ውድ ወይንና ያልሞላ ብርጭቆን ጋርደዋል። ባለማስተዋል ለመነሳት ብትሞክር ብርጭቆው ይደፋል። የተጓጓለት ጥበቃ፤ የተጓጓለት ፍቅር፤ የተጓጓለት ተመስጦ አፈር ይበላል። በራሱ የሚቆም፤ ግን የሚሞላው (አጋር) የሚሻ የጎደለ ሕይወት፤ አጋር ሽቶ አልያም አጋሩ የበደለውን በደል ለመርሳት ብቸኝነትን የመረጠ …። ከውድ ወይንና ካልሞላ ብርጭቆዋ ግርጌ ሦስት አበቦች ወድቀዋል። ኹለቱ ቀይ ጽጌረዳ ፍቅርን የሚገልጡ/ለርሷ የተሰጡ?/ልትሰጥ ይዛው የወጣች፤ ትዝታዋን ልታድስ? ከስካር በኋላ የምትወረውረው? አንዱ ለወዳጅ ወይም ለራስ ሊሰጡ/ለርሷ የተሰጡ። ሦስትነትን በኹለትነት፤ ሦሰተንትን በአንድነት፤ አንድነት በኹለትነት፤ አንድነትን በሦሰትነት። አበቦቹ ደማቅ ቀለም አላቸው። ገና ትኩስ ናችው፤ ያልደበዘዘ ፍቅር፤….ትኩስ ፍቅርን በወይንና በሲጋራ ለአፍቃሪ ሊሰጥ የነበረ ወይም በፍቀር ተሰጥቷት ያልተቀበለችው። ስለዚህ ለሚመጣው ለተቀጠረ አልያም ለሰጠ፤ …ያለ የተለየ….ተስፋ…ጥበቃ…ጸጸት…፡ –
“…አንተ የምወድህ ልጅ አካል ሰውነቴ፤
ህይወት ትጣፍጥልኝ ቶሎና በሞቴ።” (ገፅ 5) ያለች፤
ወይም
“በስልክ አነጋግረኝ የኔ እና አንተ ድግስ፤
ና የልባችንን እንደልብ እናድርስ…” (ገፅ 2) ጆሮዋን እየቀሰረች፤
ወይም
“…የልጅነት ፍቅሬ ምጣልኝ ግድ የለም፤
የጀመርነው ጉዳይ ፖለተካ አይደለም።” (ገፅ 25) በሚል አምሮት፤
ወይም
“…የማይድን በሽታ የማልጠየቀው፤
ምን ያደርጋል ያልከኝ ናፍቆትህ ሕማም ነው !!!” (ገፅ 19) ዓይነት ጽኑ ሕመም፤
ወይም
“ አንተ የኔ ድክምት፤
አንተ የኔ ብርታት፤…”
በሚል የደጀንነት፣ የናፍቆት ዜማና ተማጽኖ በምትጠብቅ አንስት አይነት።

“አትቀርም አውቃለሁ” ፤ “ፍቀር እኔና አንተ”ና “ልንገርህ” እያለች፤ “ለምን ይመስልሃል?” ፤ ”ውዳሴ ለክብርህ”ና ”አንተኑ ለመርሳት” እያለች። እንዲሁም አንድ የነፍስ ጥያቄ፣ አንድ የነፍስ ናፍቆት፣ አፍቅሮ ላለማፍቀር፣ አስቦ ላለማሰብ፣ ረስቶ ላለመርሳት የተሰናዳችን ሴት ትመስላለች። ተሳክቶላት ይሆን? መጽሐፉን ወደ ውስጥ በዘለቅን መጠን ግጥሞቹ እያደጉ፤ ፍቅር እየጎመራ…. ይሄዳል…ዝለት ይከተላል። …ነፋሱ የሲጋራውን ጭስ ወደ ግራ ይመራዋል፤ በቀኝ የጀመርነው ልጅነት፤ በገርነት የተጀመረ ፍቅር… ወደ ግራ ባዘመመ፤ ባልተፈለገ መንገድ የነጎደ፤ የዘመመ፤ ለአፍታም ቢሆን ለቅጽበታት የወደቀ፤ …ዕደሜ ያጎበጠው… ሊነሳ የሚችል …እያለችን ይሆን? የቀጣዩ ሲጋራ ጭሰ ወዴት ይሆን የሚነፍሰው? ይህንንም “በፍቅራችን እድሜ“ በሚለው ግጥሟ በዕድሜዋ ርዝማኔ ለኮነናት አፍቃሪ ( ያው ሴት አፍቃሪ ስታረጅ ወንድ አፍቃሪ አያረጅም አይደል?) በሰጠችው መልስ እንዲህ ትላለች፡ –

“….በፍቅራችን ዕድሜ፤
አንተም እያወኩህ አንተም እያወከኝ፤
አረጀሽ አረጀሽ አረጀሽ እያልከኝ፤
ፍቅሬ በፍቅራችን እባክህ አታሳቀኝ።” (ገፅ 23)
ነው ወይስ ለ/እኔ ወጣት ልጅሽ “እናቴ አርጅተሻል እያለችን ነው ?” እኔ በርግጥ ይሄ ግጥም ከዚህ በተለየ መንገድ እነዲህ ቢጠናቀቅ እመርጣለሁ፡-
“….በፍቅራችን ዕድሜ፤
አንተም እያወኩህ አንተም እያወከኝ፤
“አረጀሁ አረጀሽ አረጀን“ እየተባባልን፤
ፍቅሬ በፍቅራችን አብረን እንዘልቃለን:: (ገፅ 23)

በግራዋ በኩል በግራ ትክሻዋ ትይዩ የፈኩ የመስከረም ዓደይ አበባዎች፤ መሃል መሃል ላይ ዕንቁ የመሰሉ ጠቃጠቆዎች ይታያሉ። ይህም የመስከረም ስካር? መቼ ነው የጀመረችው? መስከረም መስከር የጀመረ ማብቂያው የት ይሆን?። መስከረም ጸደይ ነው። መስከረም እሸት ነው። መስከረም ርጥብ ነው። መስከረም አበባ ነው። መስከረም አዲስ ነው። መስከረም ተስፋ ነው። መስከረም መታደስ ነው። መስከረም ብራ ነው። መስከረሟን ወይም በአደይ አበባዋ ግዜ ጀምራ በወይንና በሲጋራ የምትናውዝ አንስት። ቀሪውን ዓመት እንዴት ትገፋዋለች? ከሰው የተነጠለች፤ ባይተዋርነት የተሰማት ብቻዋን …። አገሬ ስካር ነው፤ ስካር አገሬ ነው፤ የሴት ሰካር!…አገር ስተሰክር…እናት ስትሰክር…ከልጆቿ ተነጥላ…ብቻዋን….እንቡጥ ልጆች ምን ይሉ ይሆን? ላለመናገር የተገዘተች…ብትናገር ሰሚ የሌላት….ምን ምርጫ ይኖራታል…ለብቻ መተከዝ…

በመድብሉ ወጣትነት ፈክቶ፤ ፍቅር ተወድሷል። ተስፋ ተዘርቷል። ከነፍስ ያፈቀረች ፍቅረኛ፤ የሔደበትን መንገድ አፈር ያስቅማታል። ከፈጣሪ እኩል ትሰግድልለታለች/ይመለካል፤በርሱ ሥም ይማላል፤ ፍቅር መለኪያ አልባ ይሆናል፤ ልበ ቢስነትን ያጋልጣል፤ የገባን እውነት ሲያሸሽ ያኖራል፤ በንጋት ከቤት ያስወጣል፤ ለነገው ያሳሳል፤ በልብ ይሰውራል፤ ድካምም ብርታታም ይሆናል፤ ሌሊቱ ይጎተታል፤ ጨረቃ ትስቃለች፤ ኮከብ እንደ እህል ከሰማይ ላይ ይሰጣል፤ ለዛ ባለው ዜማ ንፋሱ ያፏጫል። ከአፍቃሪዋ ውጪ ሌላ ድምጽ አትሰማም፤ ቆሳይ ምርኮኛ ካለሱ የማትነቃ ትሆናለች፤ መሸሽ የማትችል የሱ ሱሰኛ ትሆናለች፤ እህል የማትበላ እንቅልፍ የማትተኛ፤ ከደረቱ ማደር ተኝታም ማለም ማንጋት ትመኛለች፤ ማስመሰልን ትታ የምር ራሷን (እሷነቷን) ትገልጣለች። ተፈቃሪው በአንጻሩ አስማት ዓይነት ጥበብ ያለውና ምንም እንዳልሆነ ይቆጥራታል።

በጊዜ ሒደት፣ በቸልተችነት፣ በኑሮና በዕደሜ ዝለት ፍቅር ይሻክራል። ያን ግዜ መኮራረፍ ይነግሳል። ያኔ ሲያኮርፋት፡- በጸሐይ ዶፍ ይዘንባል፤ ጀንበር ታኮረፋለች፤ በክረምት ሐሩር ይሆናል፤ በጋ ዝናብ ይጥላል፤ዓለም ይሰፋታል፤ ተፈጥሮ ይዛባል። ለነገሩ አፍቃሪ ሲያኮረፈን ዓለም ትሰፋናለች ወይስ ትጠበናለች?

ይሔም፡- ቶሎና በሞቴ ተብሎ የተናፈቀ አፍቃሪ በ “የመጣነው መንገድ ያሳዝናል“ ዓይነት ትካዜ “ላልሄድንነበት መንገድ ሙሉ ከፍያለሁ“ በሚባል እኛ ምን አጠፋን፤ ለምን እንከፍላለን? ዘመነኞቹን ጠይቁ እንጂ በሚል ጸጸትና የፖለቲካ ሥንክሳር ይጠናቀቃል። ከነ ኪሳራዬ እንዳለሁ አለሁኝ በሚል የልብ ትካዜ እንደ እናት፣ እንደ ወጥቶ አደሩ ሚስት፣ እንደ አፍቃሪ ጥበቃ፣ በእልህና ናፍቆት፣ በእቀናለሁ ስብከት፣ በ “መጨረሻ” ያልከኝ መጨረሻ “ይሔኔ እኔም ገባኝ” በሚል ሙሾ ይጠናቀቃል።
ይቀጥላል…

የጽሑፉን አዘጋጅ በድሉ አበበን በ [email protected]
ኢሜል አድራሻ ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here