“አራጆች እየሸለሉ የሚኖሩባት አገር ሆናለች”

0
1225

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

ሚሚ ሽሽጉ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቤተክርስቲያንን በማገልገል የደብራቸው የወጣቶች ማኅበር አባል የነበሩት ሚሚ፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸውን በመወከል የማኅበራቱ ኅብረት ውስጥ ገብተው በማገልገል በርካታ የበጎ አድራጎትና መንፈሳዊ ተግባራትን ማከናወናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ወጣቶች በማስተባበርና ለአገልግሎት በማሠማራት የሚታወቀው ይህ ኅብረት፣ የቤተክርስቲያኒቱና የምዕመኖቿ ችግር እንዲታወቅና መፍትሔ እንዲበጅለት ሲጥር የኖረ ነው፡፡ ስለወቅታዊው የቤተክርስቲያኒቱ ችግር፣ እንዲሁም ወጣቱ ምን እንደሚጠበቅበት የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ከምክትል ሰብሳቢዋ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ስለማኅበራቱ ኅብረት ቢያስተዋውቁን?
ኅብረቱ ከየአጥቢያው የተሰባሰቡ ማኅበራት ጥምረት ሲሆን፣ ዓላማው ከሠንበት ት/ቤት አባልነትና አገልጋዮች እና ከማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት ውጪ የሚገኙትን ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችና ጎልማሶች ማሰባሰብና የተደራጀ ሁለገብ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሠጥ እንዲሆን መሥራት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት በመጠበቅና በማስጠበቅ የቤተክርስቲያን ጠላቶችን አፍራሽ ተግባር ከአባቶች ጎን በመቆም ወጣቱ እራሱን፣ አካባቢውንና ቤተክርስቲያኑን እንዲጠብቅ ማደራጀት ነው።

ኅብረቱ የበጎ አድራጎት ተግባራትንም የሚያከናውን ቢሆንም፣ በዋናነት የቤተክርስቲያን ሕግጋቶችን ባልጣሰ መልኩ መብቶቿን ለማስከበር በሠፊው ይሠራል። አባላቱ የቤተክርስቲያን ልጅ እንደመሆናቸው በሚፈለጉበት ቦታ ኹሉ ተወክለው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ይሠጣሉ።

ወቅታዊውን የቤተክርስቲያኒቱ ኹኔታን እንዴት ያዩታል?
ወቅታዊው የቤተክርስቲያናችን ኹኔታ እንደሚታወቀው ከተወሠኑ ዓመታት ወዲህ በተለይ ከባለፉት ሦስትና አራት አመታት ወዲህ እጅግ በጣም ሠፋ ያለ መከራ ነው እያየን ያለነው። የቤተክርስቲያናት መቃጠል፣ የንዋያተ ቅዱሳን መዘረፍና የተለያዩ ካሕናቶችና ምዕመናኗ መታረድና መሞት በጣም በስፋት እየታየ ነው። በተለይ ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት የሚደረጉ ተግባራት ተበራክተዋል። ከዕለት ዕለት ይሻሻላል ብለን ታግሰን ብንጠብቅም፣ በየጊዜው እየተባባሰ ነገሮች እየከፉ ነው። እስከዛሬ ድረስ የምንሠማው እንደቀጠለ ነው። የይዞታ መነጠቅን ጉዳይ፣ የካህናትና ምዕመናን መታረድን የምንሰማው ዳር አገር እንደሆነ ነበር። አሁን ግን የአገሪቱ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ጭምር እያየነው እንገኛለን። አሁን አሁን የመብት ነጠቃው እያደር እየሠፋ ነው የመጣው። የቤተክርስቲያንን ይዞታ ለማሳጣት በሥፋት እየተሠራ ነው።

የቤተክርስቲያኒቱ ፈተና እንዲበዛ የተደረገው ሆን ተብሎ በመዋቅር ደረጃ በተዘጋጀ ዕቅድ ነው መባሉን እንዴት ያዩታል?
እየሆነ ያለውን ስንመለከት እንደዛ እንድንል ነው የሚያደርገው። ምዕመናን ላይ የሚደርሰውን ሞትና እንግልት ተከትሎ ምንም አለመደረጉን ስንመለከት፣ የምናስበው በመዋቅር ደረጃ ታቅዶ እንደሚፈፀም ነው። ያረዱ፣ የገደሉ፣ ንብረት ያወደሙ፣ ሕግ ፊት መቅረብ ሲገባቸው በአደባባይ የሚፎክሩበት ኹኔታ ነው ያለው። ስንት ግፍ ሲፈፀም አንድ እንኳን ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድበት አልሰማንም። ወለጋ እንኳን ብዙ ምዕመናን ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ምንም የሠማነው መፍትሔ የለም። ለሚደርሰው በደል ምላሽ የሆነ አንዳችም ነገር የሰማነው የለም። ጥፋት ያጠፋ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዳኛ ፊት እንዲህ አደረገ ሲባልና ፍርዱን ሲቀበል እስካሁን አልተሰማም። መንግሥት እንዲህ ሲያስደርግ ቢታይ ኑሮ ምዕመኑም ሆነ አባቶች ተስፋ አይቆርጡም ነበር። ምንም ቢዘገይም መንግሥት ከጎናችን ነው ለማለት የሚያስችል ዕርምጃ ይሆን ነበር። እውነቱ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። አራጆች እየሸለሉ የሚኖሩባት አገር ሆናለች። የቤተክርስቲያን መከራዋ፣ እንግልትዋ፣ ስደቷም አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው። መከራዋ እየባሰ እንጂ እየቀለለ አይደለም።

አንዳንዶች ቤተክርስቲያኗ ላይ የሚፈፀመው በደል፣ “ትንኮሳ” ነው በማለት ተከታዮቿ የአፀፋ ዕርምጃ እንዲወስዱና ያን ተከትሎ መውሰድ የተፈለገ ዕርምጃ አለ የሚሉ አሉ። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የቤተክርስቲያናችን መምህር ሲገልጹ፣ “እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ጦርነት ያልተነሳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዝም ብላ ችላ ስለኖረች ነው” በማለት ነው። አንዳንዴ ሕዝብ የተሰበከውን ወይም የተነገረውን ነገር ተግባራዊ እያደረገ ሲመጣ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲያጋጥሙት እየቻላቸው ያልፋል። ለምሳሌ፣ በክርስትናው አስተምሮ “ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው” እየተባለ ሲሰበክ የኖረ ወጣትና ምዕመን መኖሩ ይመስለኛል የተማረው ውስጡ ተጽዕኖ እያሳደረበት ቁጣውን ሲገልጽ የማይታየው።

ምዕመኑ ሲበደል እስካሁን በጸጋ ሲቀበል ነው የኖረው። ለክርስቲያን መሞትም መታረድም መቃጠልም ብርቁ አይደለም። የክርስትና ታሪኩንና ክርስቲያናዊ ሕይወትን ብናየው እንኳን፣ አልጋ ባልጋ የሆነ ሳይሆን የፈተና ጉዞ ነው። ከበፊቱ ልዩ የሚያደርገው አሁን ላይ መዋቅራዊ መሆኑ ነው። ኹሉንም ምዕመናኑን እያስከፋ የመጣው አሁን ያለው የተደራጀ ዘመቻ በመሆኑ ነው የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች ዋጋ እንዲከፍሉ የሚያደርጋቸው። “ሕገ-መንግሥቱ የኃይማኖት እኩልነትን ያምናል፤ በውስጡም ኹሉም ኃይማኖቶች እኩል ናቸው” ቢባልም በተግባር ግን መሬት ወርዶ እያየነው አይደለም።

ቤተክርስቲያንን ከገጠማት ፈተና ለመገላገል ቁርጠኛ መሆን ይሻላል የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ከመንግስት ጋር ያለውን ጉዳይ እየተለሳለሱ መያዙ ያዋጣል የሚሉ እንዳሉ ይነገራል። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
በዚህ ጉዳይ ላይ እንደምሳሌ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ አለ። ከዚህ በፊት በዚሁ በመስቀል አደባባይ ጉዳይ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወንድሞቻችን የአፍጥርን በዓል እናከብራለን ብለው ወጥተው ነበር። በዛ ሰዓት አንዳንዶች ያሰሙትና ያንጸባረቁት የነበረውን ነገር ስንሰማው ነበር። በእነሱ የተደረገውን ኦርቶዶክሱ አድርጎት ቢሆን ኑሮ በእርግጠኝነት ብዙ ነገር ይደርስ ነበር። “ኢህአዴግ ይሻለናል” የሚል መፈክር ጭምር ይዘው ነበር የታዩት። ኦርቶዶክሱ ግን ጥያቄ አቅርቦ እምቢ ሲባል አክብሮ፣ “እሺ” ብሎ ነው ቤቱ ሲገባ የኖረው። መንግሥት የሽንገላ ቃል ሲያሠማ ምዕመኑ አምኖ ነበር እሺ ብሎ ሲጠብቅ የኖረው። እስካሁንም ለዚህ የዳረገን የሽንገላ ቃላታቸውን ማመናችን ይመስለኛል። በአፋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገር ናት፤ አገር ገንብታለች፤ የአገር ባለውለታ ነች ይሉናል፤ ተግባር ላይ ሲመጣ ግን እንደምናየው ዜሮ ነው።

አገርን ከነድንበሩ አቆይታ፣ ፊደል ቀርፃ ያስረከበች ቤተክርስቲያን በአግባቡ መስተናገድ ሲገባት ዛሬ እየተገፋችና ወደዳር እየተጣለች ነው ያለችው። እንደዚህ ነው ወይ ውለታ የሚመለሰው? ታቦት አዝምታ አገር ያስከበረች ቤተክርስቲያን ውለታ በዚህ ዘመን ይህ መሆኑ ነው የሚያሳዝነው። ኢትዮጵያ ብለን ስናነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታ ናቸው። ታሪካችንንም ከተመለከትን ቤተክርስቲያናችን ለአገሪቱ ያበረከተችው አስተዋፅኦ በርካታ ነው። የቀን መቁጠሪያዋን ከመቅረጽ ጀምሮ ፊደል አዘጋጅታ፣ ሥነምግባርን አስተምራ፣ ለዚህ ያበቃችን ናት። ለአገር ከሠራችው አንፃር እየተከፈላት ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ ጭራሽ ሚዛን ላይ የሚቀመጥ ክፍያን እያገኘች አይደለም። አሁን ደግሞ ጭራሽ የነበራትን ልዕልና ለመውሰድ መብቷን መንጠቅ ልማድ እያደረጉት ነው። ውለታዋን መክፈል ሲገባ የማይገባትን የመብት ገፈፋ ሲፈፅሙባት ነው ምዕመናኑን ያስቆጣው።

የምዕመናኑ ስሜት በሚነቃቃበት ወቅት፣ ወጣቱ ጉዳት እንዳደርስበት በሚል የጋለ ስሜቱ ላይ ውኃ ይቸልሳሉ የሚባሉም አሉ። በዚህ ላይ አቋማችሁ ምንድን ነው?
እንደቤተክርስቲያን ልጅነታችን ከአባቶቻችን ትዕዛዝ ውጭ አንወጣም። እነሱ የሚሉንን እናደርጋለን። ነገር ግን፣ አንዳንድ አባቶች አሉ ቤተክርስቲያኗን ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ። ይህን ስል ውስጥ ያሉ ትልልቅ ብጹዓን አባቶች መኖራቸው ሳይረሳ ነው። ለቤተክርስቲያኒቱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ፣ መደረግ ያለበትን ኹሉ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ የሚፈፅሙ እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን፣ አንድ እግራቸው ቤተ-መንግሥት ሌላኛውን ቤተ-ክህነት ያደረጉ ጥቂት አባቶች አሉ። ቤተክርስቲያንን እንደበሶ የሚበጠብጧት ለሆዳቸው ያደሩ በውስጧ አሉ። እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። መጸሐፉም እንዲህ ይላቸዋል፤ “ሆዳቸው አምላካቸው የሆነ” ነው የሚላቸው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው ቤተክርስቲያኒቱን የሚበጠብጧት እንጂ፣ እኛ ልጆቻቸው እንዳንጎዳባቸው የሚሳሱልን በርካታ ብጹዓን አባቶችም አሉ። እነዚህ አባቶች እኛ እንዳንጎዳባቸው ብለው የሚደርስባቸውን ችለው ቆይተዋል። እንደአባትነታቸው የቤተክርስቲያን ነገር ከኛ በላይ ያንገበግባቸዋል። ይህ ቢሆንም የሚደርስባቸውን ችለው እኛ እንድንረጋጋ የሚያደርጉ አባቶች አሉ። በአንጻሩ ደግሞ እኛን ያስጠቁን ያስደፈሩን አባቶች አሉ። የሚያስጠቁ አባቶችን ከእንግዲህ ወጣቱ ይታገሳል የሚል ዕምነት የለኝም። ሚናቸውን እስኪለዩ ድረስ አንታገሳቸውም። መጫወት ወደሚፈልጉበት ሜዳ ሔደው መጫወት ይችላሉ። ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆነው ግን አይበጥብጧት።

እኔ ኹልጊዜ የሚገርመኝ በታሪክ ስንሠማ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ጫና የሚፈጠረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ መሆኑ ነው። ይህ የሚሆነው ለምን እንደሆነ እስካሁን አይገባኝም። በአቶ መለስ ዘመን የነበሩ ብጹዓን አባቶች ተሰደው የራሳቸውን ጳጳስ ሹመው ነበር። አሁን ደግሞ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቀጥል እየፈለጉ ነው። ይህ ትውልድ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዲኖር አይፈልግም። እኛ አልፈን ቀጣዩ ትውልድ ቤተክርስቲያኒቱን በሠላም እንዲረከብ ነው የምንፈልገው።

ቤተክርስቲያኒቱ የሠላም አውድማና ከተማ እስከሆነች ድረስ የምትታወቅበትን ይዛ መቀጠል አለባት። በዚህ አጋጣሚ ብጹዓን አባቶች እባካችሁ ቤተ-ክህነትን ረግጣችሁ እያለፋችሁ ቤተክርስቲያኒቱን አታስደፍሯት ለማለት እፈልጋለሁ። እነሱ ተንቀው ቤተክርስቲያኒቱንና ምዕመኑን አስናቁ፤ አስደፈሩ፤ ኹላችንንም አዋረዱን። በተወሰኑ ሠዎች ምክንያት ነው ታላቋ ቤተክርስቲያን ከፈተናዋ መውጣት ያልቻለችው።

የቤተክርስቲያኒቱ የውስጥ ፈተናዎች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ማድረግ ይሻላል ወይስ የውጩን መቅረፍ ይቅደም በሚል የሚነሳውን ሐሳብ እንዴት ያዩታል?
ቤተክርስቲያን በውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች መወጠሯ ይታወቃል። ውስጣዊ ፈተናዎቻችንን አንድ ቀን ኹላችንንም ወደቤታችን መለስ ብለን በማየት እናፀዳዋለን፤ መጀመሪያ ግን የውጩን ተቋቁመን እንቅረፈው። ለውጩ ጠላት መጠንከር መንስዔዎቹ የውስጥ ጠላቶቻችን ናቸው። የውጮቹን ካፀዳን በኋላ ወደ ውስጣችን መመለሳችን አይቀርም። ቤተክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት መልኩ መቀጠል የለባትም።

ለኃይማኖታችሁ በመቆርቆራችሁ የኅብረታችሁ አመራሮችና ወጣቶች ላይ የሚፈጠር ጫና እንዳለ በተደጋጋሚ ይሰማል። ኹኔታው አሁንስ ምን ይመስላል?
ጫና እንዳለብን ይታወቃል። ፈተና፣ ፈተና መሆኑ የሚታወቀው ተቋቁመው ሲያልፉት ነው። ሙሉ አመራሩ ማለት ይቻላል የተለያየ ጫና ሲደርስበት ነበር። በሰኔ ሦስቱ፣ በግንቦት 17ቱ በቅድስት ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ወቅት ጭምር የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ይደርሱናል። ይህ ቢሆንም የማኅበራቱ ኅብረት ጫናውን ተቋቁሞ ወደፊትም ይቀጥላል። ጫናዎች ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጡብንም። እኛ እንደማኅበር እንደተቋም ነው የምንጓዘው።

ሠሞኑን ከጥምቀት በዓል ጋር በተገኛኘ በርካታ ወጣቶች ለዕሥር መብቃታቸው ይታወቃል። በነቀምትም ኃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙም ይፋ ሁኗል። ይህን ዓይነት ተግባራትን ለማስቀረት ኅብረቱ ምን እየሠራ ነው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአደባባይ በአላቶቿ ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ትልቁን ዋጋ እየከፈለ ያለው ወጣቱ ነው። ምንጣፍ በማንጠፍና ቱቦ በመጥረግ የሚታወቀው የእኛ ማኅበር በተለይ በእንዲህ ዓይነት ወቅት ግንባር ተሰላፊ ስለሆነ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ምዕመኑ በሠላም ወጥቶ በሠላም እንዲመለስ ከሕግ አካላት ጋር ግንኙነት የሚኖረው ወጣቱ ነው። ይህን ኃላፊነታችንን በምንወጣበት ወቅት አንዳንድ ትንኮሳዎችን እናስተናግዳለን። ለምሳሌ በዘንድሮው ዓመት በዓል የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች የሠሩት የእጅ ሥራ ነበር። ሥራቸው ከቤተክርስቲያናችን አኳያ ትርጉም ያለው ነው። የቤተክርስቲያን እጅ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ካህን ሲባርኩ የሚያሳይ ነው። አንዳንድ ፖለቲከኞች ትርጓሜውን እንደነሱ ይመነዝሩታል። አንድ አባባል አለ፣ “ሠው እግሩን የሚዘረጋው በአልጋው ልክ ነው” የሚል። ሠው በራሱ ባሰበበትና በሚያውቀው መንገድ ነው የሚሄደው። ስለቤተክርስቲያን ታስቦ ነው የተሠራው።

ኢትዮጵያ የቅዱሳን፣ የኃማኖትና ለዚህች አገር 24 ሰዓት የሚፀልዩ ፃድቃን የሞሉባት አገር ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት ስለመንግሥቱ፣ ስለወታደርና ስለአገር በየሠዓቱ የሚጸለይባት። ይህን በማስመልከት ነው ወንድሞቻችን ምሳሌውን የሠሩት። ባለሥልጣናቱ ግን ጭራሽ ያልታሰበን ነገር አምጥተው ነው ለራሳቸው ፖለቲካ እንዲመቻቸው አድርገው የሠሩትን ዕሥር ቤት ያወረዷቸው። ከጥር 10 ቀን ጀምሮ አስረዋቸው ፍርድ ቤት እንኳን አላቀረቧቸውም። ያልጠየቅነው አካል የለም። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት፣ ቤተክህነትም ሔደናል፣ ግን ማንም መልስ ሊሰጠን አልቻለም። በምን ጥፋታቸው እንደታሠሩ እንኳን ቤተሰቦቻቸው ማወቅ አልቻሉም። ምንም ባላጠፉበት ወንድሞቻችን ለዕሥር ተዳርገው እንዲፈቱ እየጮህን እንገኛለን።

የወይብላ ማርያም ታቦትን ወደመነበሯ ለማስገባት በነበረው ሒደትም የተፈጠረውና ኹለት ወጣቶች የተገደሉበት ኹኔታ የሚረሳ አይደለም። በእጁ ከበሮና ፅናፅንል ይዞ የወጣን ምዕመን በጥይት መምታትና መግደል ምን ማለት ነው? “ለሕዝቦች እኩልነት እንታገላለን” የሚል መንግሥት ባለበት አገር ይሄ ይሆናል? ታቦት አጅቦ የወጣን ምዕመን መቀጥቀጥ፣ ማንገላታት፣ መግደል፣ ምን ይባላል? የወይብላው ለየት ይላል። ገዳይ እየፎከረ ሟች የሚሸማቀቅበት ነው። ወይብላ ላይ ኹሌ ችግር አለ። ለምንድን ነው መንግሥት ቀድሞ ጥንቃቄ የማይወስደው? ይህንን ባደረጉትስ ላይ ለምን አፋጣኝ ዕርምጃን አይወሰድም? ለምን ገዳዮችስ ለፍርድ አይቀርቡም?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “እየሞትን እንበዛለን” በሚል ዓይነት ጥቅሶች ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። ዝም ብሎ መሞት አይገባም የሚሉ አስተሳሰቡን ይቃወሙታል። እዚህ ላይ ምን አቋም አሎት?
መጽሐፍ ቅዱስ “እንደእርግብ የዋሆች፣ እንደእባብ ልባሞች ሁኑ” ይላል። እኛ አካሄድ አለን፤ ያንን ይዘን እንሄዳለን። ለምሳሌ፣ በዝምታ መስበክ ያለበት ይሰብካል፤ መናገር ያለበትም ይናገራል። የሰናኦር ግንብ የፈረሰው በጩኸት መሆኑ ይታወቃል። እኛም መሄድ ባለብን መንገዶች ተጠቅመን እንጓዛለን። ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባራችንን ሳንጥስ የቤተክርስቲያኒቱን መብት ማስከበር ሥራችን ይሆናል። ኃይል የእግዚአብሔር ነው ብለን ስለምናምን መጠቀም ያለብንን ኃይል ኹሉ ተጠቅመን እንሠራለን። እስካሁን ዝም ማለታችን ዋጋ አስከፍሎናል። ስንበደል፣ ስንታረድ፣ ሲቃጠልብን በፀጋ መቀበላችን፣ ዛሬ ላይ ሲበዛብን ምንም እንዳይመስለን አድርጓል። አሁንም በጅምላ ስንፈጅ በዝምታ እንዳለን ነው። ከዚህ በኋላ ግን በዝምታ አይቀጥልም። የሚገድሉን እንድንበዛ ሳይሆን ጨርሰው ለማጥፋት ነው።

ቤተክርስቲያን ምዕመናኖቿንና ንብረቶቿን ለማስጠበቅ እስካሁን የምትጓዝበት መንገድ ከልመናና ከመማፀን አይተናነስም በሚል ሒደቱን የሚተቹ አሉ። የራሷን ኃይል አደራጅታ በመቅጠር ራሷን ማስከበር ይጠበቅባታል የሚሉም አሉ። በዚህ ጉዳይስ ምን ይላሉ?
በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተክርስቲያን አባቶች ጠንክረው ይሠራሉ የሚል ዕምነት አለኝ። አገሪቱ በቱሪዝም ከምታገኘው የውጭ ሀብት 80 በመቶ የሚሆነው በቤተክርስቲያኒቱ ምክንያት የሚገኝ ነው። ገዳማቷንና አድባሮቿን ለጎብኚዎች ዘግቻለሁ ብትል በመንግሥት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 90 በመቶ የምታንቀሳቅሰው ቤተክርስቲያኗ ናት ማለት ይቻላል። መብቷ ሊከበርላት ካልቻለ ያለውን አማራጭ በሙሉ መጠቀም ግድ ይላል። የራሷን ዕርምጃ መውሰድ ትጀምራለች። የራሷን ባንክ፣ የጥበቃ አገልግሎትን መሳሰሉትን ራሷ ለወደፊት ትሠራለች ብዬ እገምታለሁ። ከዚህ በኋላ አባቶች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በይበልጥ ያስቡበታል ብለን እንጠብቃለን። እንዲህ ለመሆናችንና ለማለቃችን ምንጭ የሆነው ምስጢር ምንድን ነው ቢባል ምድራዊ ኃይል ስለሌለን ነው። ከዚህ በኋላ ከአባቶች ጋር ምክክር እያደረግን ነገሮችን ለማስተካከል እንሠራለን። ይህን ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ በየአጥቢያው ንቁ ተሳትፎ እያደረገ የአባቶችን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ዝግጁ መሆን አለበት።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here