ከልክ በላይ የተዝረከረኩት የአዲስ አበባ ማስታወቂያዎች

0
1026

በአዲስ አበባ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ወይም ባነሮች ከመጠን በላይ እየተበራከቱ መሆኑ ይስተዋላል። የመንግሥትም ሆኑ የግል ተቋማት ለማስተዋወቅ የሚፈልጉትን ጉዳይ በባነር አሠርተው በማስታወቂያ ሠሌዳዎች ላይ መለጠፋቸው የተለመደ ቢሆንም፣ አሁን እየተስተዋለ ያለው ግን በተቃራኒው ነው።

በአሁኑ ወቅቱ ሚለጠፉት ባነሮች ከመጠን በላይ እየተበራከቱ ከመምጣታቸው በተጨማሪ፣ በበርካቶች በኩል አነጋጋሪ የሆነው ባነሮቹ መለጠፍ ካለባቸው ቦታ አልፈው በግለሰቦች አጥር ላይ ሁሉ መለጠፋቸው ነው።
በዚህም፣ ከተማዋ በየቦታው የተዝረከረኩ ማስታወቂያዎች ወይም ባነሮች መናኸሪያ ከመሆኗ በዘለለ፣ ማስታወቂያዎች ከተፈቀደ ቦታ አልፈው በግለሰቦች አጥር ላይ ሳይቀር መለጠፋቸው የመብት ጥሰት እንደሆነ ብዙዎቹ ያነሳሉ።

ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል ጉዳዩን በጥልቀት ተመልክቸዋለሁ የሚሉት እያሱ አራጋው ናቸው። እያሱ ያነሱት፣ በግለሰብም ሆነ በመንግሥት ለሚዘጋጁ ማስታወቂያዎች የራሳቸው የሆነና የተዋበ ቦታ እንደሚያስፈልግ ነው።

ማንም ሰው ባለቤቱን ሳያስፈቅድ መብትን በሚጥስ መልኩ ከመሬት ተነስቶ ከፈለገው ቦታ ባነር ሊለጥፍ ይችላል ወይ? ሲሉ የሚጠይቁት እያሱ፣ ብዙዎች ለመናገር እየፈሩ ነው እንጅ ከፈቃዳቸው ውጭ ከሕንጻቸውና ከአጥራቸው ላይ ሳይቀር የሚለጠፉ ማስታዎቂያዎች ተመልክቻለሁ በማለት መስከረዋል።

አያይዘውም፣ በወረቀት ለሚጻፉ የሥራ ቅጥር ማስታዎቂያዎች የታወቀና በሥርዓት የተተከለ የመለጠፊያ ሠሌዳ እንደተዘጋጀው ሁሉ፣ በኅትመት የሚሠሩ ባነሮችም በተመሳሳይ ጊዜ የተወሰነ ቦታ ሊወሰንላቸው ይገባል ሲሉ ነው የመፍትሔ ሐሳብ የሚሉትን የሠጡት።

እያሱ አክለውም፣ የሥራ ማስታወቂያዎችም ቢሆኑ ከተተከለላቸው የማስታወቂያ ሠሌዳ ውጭ እየተለጠፉ ለከተማዋ ውበት መበላሸት ምክንያት ሆነዋል ያሉ ሲሆን፣ በተለይም በሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች የሚለጠፉት በየቦታው በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሠጠው ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መሰረት ብርሃኑ የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው፣ “ምነው ከተማዋ የማስታወቂያ መለጠፊያ ቦታ የላትም እንዴ? በተለይም ባነሮች ቁጥራቸው እንደ ምድር አሸዋ ሆኗል፤ ከተማዋም በተንጠለጠሉና በተዝረከረኩ ማስታዎቂያዎች ድንብርብሯ ወጥቷል” ይላሉ።

መሰረት አክለውም፣ ዜጎች በጦርነት ችግር ላይ በመሆናቸው የመሠረታዊ ፍላጎት ዕርዳታ በሚያስፈልግበት ወቅት፣ ተመሳሳይ መልዕክት የሚያሥተላልፉ ትላልቅ ማስታወቂያዎች በአንድ አካባቢ ተጨምቀው መቀመጣቸው ከወጪ የዘለለ ምን ፋይዳ አለው? ሲሉ ጠይቀዋል።
ግለሰቧ እንደሚሉት ማስታወቂያዎቹ መለጠፋቸው አስፈላጊ ቢሆንም፣ የሚለጠፉበት ኹኔታ ግን አካባቢን በማያጎድፍ መልኩ ሊሆን ግድ ይላል ባይ ናቸው።

የማስታወቂያ ዓይነቶች
የተለያየ መልዕክትንና ማሳሰቢያዎችን ለማስተላለፍ ሰዎች በግልጽ ሊመለከቷቸው በሚችሉ ቦታዎች ወይም በማስታወቂያ ሠሌዳዎች ላይ የሚለጠፉ ባነሮች ከሚለጠፉበት ኹኔታ አንጻር በኹለት እንደሚከፈሉ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
ባነሮችን ወይም የአደባባይ ላይ መልዕክቶችን በዋናነት በኹለት መንገዶች እንከፍለቸዋለን የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ- ሕንጻና የከተማ ዕቅድ መምህሩ ዮሐንስ መኮንን ናቸው።

አንደኛው ዓይነት ማስታወቂያ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ማስታወቂያ ነው የሚሉት ዮሐንስ፣ ይህም የአካባቢ መረጃዎች፣ የቦታ መልዕክቶች፣ የተቋማት ሥያሜዎች እና የመሳሰሉትን ያካትታል ይላሉ።

በኹለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት የባነር ዓይነቶች፣ ከወቅታዊ አገራዊ ወይም ማኅበረሠባዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚለጠፉ ናቸው። የዘርፉ ምሁር እንዳስረዱትም በወቅታዊ ጉዳዮች ማለትም እንደ ዘመን መለወጫ፣ የኃይማኖት በዓላት፣ የገናን በዓል በማስመልከት መንግሥት ጥሪ ያደረገላቸውን ዳያስፖራዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮች በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት አማካይነት የሚለጠፉ ናቸው።

መዲናዋን አጥለቅልቀዋት የሚገኙት ባነሮች ግን ከፊሎቹ የተተከሉበትን ዓላማ ካስፈጸሙ በኋላ ወቅቱን ጠብቀው መነሳት ሲገባቸው በተቃሪኒው በስብሰው የተቀመጡ ናቸው።

ጉዳዩን በተመለከተም በርካታ ሰዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱ ይስተዋላል። የቅሬታቸው ምንጭ የባነሮቹ መለጠፍ ሳይሆን ሥርዓታቸውን ጠብቀው አለመዘጋጀታቸው፣ መቀመጥ ከሚገባቸው ቦታ ውጭ ሕግን በጣሰ ቦታ ተበራክተው መታየታቸው እና በዚህም የከተማዋን ውበት በመጨመር ፈንታ ገጽታዋን ማደብዘዛቸው ነው።

ማንኛውም ነገር ሲዘጋጅ ልክና ሥርዓት እንዳለው ኹሉ፣ ባነሮች በሚዘጋጁበት ወቅትና መልዕክትን ለማስተላለፍ የሚተከሉበት ቦታን በተመለከተ የራሳቸው የሆነ ቋሚ ሥርዓት እንዳላቸው ምሁራን ይገልጻሉ።
ከምሁራኑ ገለጻ መረዳት የተቻለው፣ በአገራችን አልተተገበረም እንጅ ሌሎች አገራት የባነር መለጠፊያ ቦታዎችን በተመለከተ የራሳቸው የሆነ ሕግና ሥርዓት ያላቸው መሆኑን ነው።

በሌሎች አገሮች ባነሮች የሚዘጋጁበትና የሚተዳደሩበት ቋሚ ሥርዓት አላቸው የሚሉት የኪነ ሕንጻ ባለሙያው ዮሐንስ፣ ሥርዓቱ በተግባር ላይ እንዲውል ያስፈለጉባቸው ኹለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
አንደኛውና የመጀመሪያው መሠረታዊ ጉዳይ ፕሮቶኮል (Branding) ሲሆን፣ ይህም አካባቢው በተለየ መልክና መታወቂያ እንዲጎናጸፍ ያደርገዋል ሲሉ ነው ዮሐንስ ጠቀሜታውን ያስረዱት።

አንድ ባለ ሦስት ወይም ባለ አምስት ኮከብ የሚባል ሆቴል መታጠቢያ ቤት ይኖረዋል። የሻወር፣ የባኞ ቤት፣ የሶፋ፣ እንዲሁም የክፍሉ ስፋትና ጥበት የሚወስን ደረጃ (ስታንዳርድ) ይኖረዋል የሚሉት ዮሐንስ፣ ለአንድ ሆቴል ይህን ያህል የምንጨነቅ ከሆነ አገር ደግሞ ከሆቴል ትሰፋለችና መርህ (ፕሮቶኮል) ያስፈልጋታል ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን የማስታወቂያ መርህ (ብራንዲንግ) ሊኖራት ሲገባ፣ ከማስታወቂያ አጻጻፍ ጀምሮ እስከ መለጠፊያ ሠሌዳ ድረስ የሚታየው ነባራዊ ዕውነታ ዲዛይኑን ያልጠበቀ ነው።
“እንዳለመታደል ሆኖ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ያን አይነት ‹ብራንዲንግ› የላትም” በማለት ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የኪነ- ሕንጻ ባለሙያው ዮሐንስ፣ ‹‹ብራንዲንጉ›› መከናወን ያለበት በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሚለጠፉ መልዕክት ያነገቡ ባነሮች፣ በምን ዓይነት ቋንቋ፣ ቀለም፣ ምን ላይ ይጻፋሉ በሚለው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ነው የመከሩት።

ማንኛውም ነገር ከሥርዓት ውጭ ከሆነ፣ ነገሮች መስመራቸውን ስለሚስቱ የታለመላቸውን ዓላማ ከግብ በማድረስ ፈንታ ያልታሰበ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸው የማይካድ ሐቅ ነው።

ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
ጽሑፎችን በተለያየ ቅርጽና መሣሪያ መጻፍ ከተማዋን ኮተታምና ዝብርቅርቅ እንድትሆን አድርጓል የሚሉት የሐንስ፣ ይህ የሆነው አንዳንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚያብረቀርቅ ማይካ ላይ፣ አንዳንዶቹ በላሜራ ላይ፣ ሌሎቹ ደግሞ በድንጋይ ላይ ስማቸውን ስለሚጽፉ ነው ብለዋል።

ባለሙያው ስለሚታየው ችግር ትችት ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ሐሳብም አካፍለውናል። ዮሐንስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ ባነሮችን በተመለከተ ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ መፍሔው፣ የተቋማት መለያ፣ ጊዜያዊና ቋሚ የሆኑ የከተማ ምልክቶች የሚጻፉበት ማስታወቂያ ወጥና ቋሚ የሆነ ደረጃ ሲወጣለት ነው ብለዋል።

ዮሐንስ ችግሩን ለመቅረፍ ያሥችላል ያሉትን መፍትሔ በኹለት መንገድ የገለጹ ሲሆን፣ አንደኛውና ግንባር ቀደም ነው ያሉት መፍትሔ የአንድን ከተማ መልክ የሚመጥን የማስታወቂያ አጻጻፍ ዲዛይናና መለጠፊያ ቦታ ማዘጋጀት ነው።
ኹለተኛውና ትኩረት ሊቸረው የሚገባው ያሉት ደግሞ፣ ማስታወቂያዎች ማስተማሪያዎች፣ የአንድ አገር እና ማኅበረሠብን ማንነት ማንጸባረቂያዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ ከፊደላት አጠቃቀም ጀምሮ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ነው።
በመዲናዋ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ከፊደል አጠቃቀምና ዲዛይን ጀምሮ ትክክል ስላለመሆናቸው አስተያየት ሲሰጥ ይስተዋላል።
“በአንድ ውቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተጠና ጥናት መሠረት፣ በከተማዋ ካሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መካከል በትክክለኛው መንገድ ሥማቸውን የጻፉት ከግማሽ በታች የሆኑት ነበሩ” ሲሉ ዮሐንስ ያስታውሳሉ።

አዲስ ማለዳ ማስታወቂያዎች እንዲለጠፉ የሚፈቀድበትና የማይፈቀድበት ቦታ ይኖራል ወይ ስትል ለባለሙያው ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ዮሐንስም በዕምነት ተቋማት፣ በአገሪቱ የመከላከያ ተቋማት፣ እንዲሁም በሌሎች ያልተጠቀሱ ቦታዎች ማስታወቂዎችን መለጠፍ እንደማይቻል አብራርተዋል።

አክለውም፣ “በመዲናዋ የሚለጠፉ ማስታወቂዎች የተቋማትንና የግለሰቦችን መብት የሚጥሱ ሆነዋል ያሉ ሲሆን፣ ጠዋት ስትነሳ የአንድ ተቋም ማስታወቂያ ተለጥፎበት አድሮ ይገኛል፤ እንዳታነሳው ትፈራለህ። ይህ ችግርም እየተለመደ በመምጣቱ ትክክል የሆነ ኹሉ ይመስላል” ነው ያሉት።

በግለሰብ ሱቅና አጥር ላይ መለጠፍ የመብት ጥሰት ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ከተማ አስተዳደሩም ቢሆን ይህን ችግር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል። አርከበ ዕቁባይ የከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት ዝም ብሎ ማስታወቂያ መለጠፍ ያስቀጣ እንደነበር ያሚያስታወሱት ዮሐንስ፣ ተግባሩን መከተል እንደሚገባ መክረዋል።

ምን እየተሠራ ነው?
የከተማዋን ውበት ካበላሹት ነገሮች መካከል ሥርዓቱን ባልተጠበቀ መልኩ በዘፈቀደ የሚለጠፉ፣ የሚንጠለጠሉ፣ እንዲሁም የሚተከሉ ማስታዎቂያዎች እና ባነሮች ስለመሆናችው በርካቶች ቅሬታ ማሰማታቸውን በመጀመሪያ ማብራራታችን ይታወሳል።
አዲስ ማለዳ ሕገ-ወጥ የሆኑና በጎዳና ላይ በዘፈቀደ በመቀመጥ የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ አላስፈላጊ ነገሮችን የማስነሳት ኃላፊነት የተሰጣችውን የደንብ ማስከበር ሠራተኞች ለተነሳው ቅሬታ ያላቸውን ምላሽ የጠየቀች ሲሆን፣ ቅሬታው ተገቢ መሆኑን መስክረው በጉዳዩ ዙሪያ ያደረጉትንና ለማድረግ ያሰቡትን ተግባር ጠቁመዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ለመሥራት ካሰቧቸው ተግባራት መካከል በጎዳናዋ ላይ ያሉና የከተማዋን ውበት የሚያደበዝዙ ማስታወቂያዎችን፣ ባነሮችን፣ እንዲሁም መንገድ በማጣበብ በመንገድ ላይ የተወጠሩ ኬንዳዎችን ማስነሳት መሆኑን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ኃላፊ ሻምበል ኑርልኝ ገብረኪዳን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከተማዋን ገጽታ ካበላሹት ነገሮች መካከል ማስታወቂያዎችና ባነሮች በሕገ ወጥ መንገድ መለጠፋቸው፣ መንጠልጠላችው እና መተከላቸው ነው የሚሉት ሻምበል ኑርልኝ፣ ችግር መኖሩን አምነው በዕቅዳቸው መሠረት እየሠሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በከተማዋ ተዝረክረከው የተቀመጡ አላስፈላጊ ማስታዎቂያዎችን፣ እንዲሁም ባነሮችን የማንሳት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያልደበቁት ሻምበል ኑርልኝ፣ የዳያስፖራውን መምጣት እና የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ተከትሎ በዚህ ኹለት ወር ውስጥ ብቻ ወደ 15 ሺሕ የሚሆኑ ማስታወቂያዎችን የማንሳት ተግባር እንዳከናወኑ አብራርተዋል።

በደንብ ማስከበር ሕግና መመሪያ መሠረት ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ የማስታወቂያ ወረቀቶችን እንዲሁም ባነሮችን ሲለጥፍ የተገኘ ሰው ወይም ገንዘብ በመክፈል እንዲለጠፉ ያደረገ ድርጅት፣ የ500 ብር የቅጣት ዕርምጃ ይወሰድበታል የሚሉት ኃላፊው፣ በኹለት ወራት ውስጥ እንኳ ከ30 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የቅጣት ዕርምጃ እንደወሰዱ ነው የተናገሩት።

ምንም እንኳ ኃላፊው የተዋቀረው የደንብ ማስከበር ኮሚቴ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ቢናገሩም፣ ችግሩ በተደጋጋሚ መከሰቱ ስላላቆመ ሠርተው እንዳልሠሩ እየሆኑ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እጃችን አመድ አፋሽ እንዲሆን የሚያደርጉት የተለያዩ ድርጅቶች በየቦታው የሚለጥፏቸው ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎች ናቸው የሚሉት ኃላፊው፣ በተለይም ተለጣፊና ተንጠልጣይ ማስታወቂያዎችና ባነሮች እየተበራከቱ የመጡት ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎች ገንዘብ እየተከፈላቸው ጨለማን ተገን አድርገው ስለሚለጥፏቸው ነው ሲሉ ጥቆማ ሠጥተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍና ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ የሚገኘው የደንብ ማስከበር ኮሚቴ ምሽት ላይም እየተዘዋወረ ዕርምጃ የመውሰድ ድርጊቱን መቀጠሉን አብራርተዋል።
ባነሮችና የወረቀት ማስታወቂያች አንዲለጠፉበት ከተፈቀደ ቦታ አልፈው ተርፈው የአካባቢ ገጽታን በሚያበላሽ መልኩ በመብራት ፖሎች፣ በመንገድ ግርግዳዎች፣ እንዲሁም በግለሰብ አጥር ላይ ሳይቀር የተንጠለጠሉ ፖስተሮች መበራከታቸውን አዲስ ማለዳ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውራ ተመልክታለች።

በተለይም ፖስተሮቹ እየተበራከቱ የመጡት የዳስፖራውን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እና የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ተከትሎ ነው። የዳያስፖራው መምጣትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ድርጊት ቢሆንም፣ አገሪቱ በጦርነቱ ምክንያት ኢኮኖሚዋ በደቀቀበት፣ ዜጎቿ የምግብ ዕርዳታን በሚሹበት፣ እንዲሁም ገና ያልተቋጨ ጦርነት በተደቀነበት ወቅት መንግሥትም ቢሆን በአንድ ቦታ እንኳ በተደጋጋሚ ለሚለጠፉ በርካታ ባነሮች አላስፈላጊ ወጭ ማውጣቱ በብዙኅኑ ዘንድ ቅሬን ሲያስነሳ ተስተውሏል።
ታዲያ በብዙኅኑ በኩል የሚሠነዘረው አስተያየት ለምን የማስታወቂያ ባነር ተሠራ ሳይሆን፣ ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ አንገብጋቢ ችግሮች እያሉ ለባነሮች ከልክ ያለፈ ወጪ መውጣቱ ላይ እና ባነሮቹ በዘፈቀደና በተዝረከረከ መልኩ ስለተለጠፉ የከተማዋን ውበት ከመጨመር ይልቅ ለማደብዘዝ ምክንያት ስለመሆናቸው ነው።

ትችቶች እየተሠነዘሩ ያሉት አላስፈላጊ ወጪ እየወጣባቸው እንኳ ለከተማዋ ፕሮቶኮል የማይመቹና ዲዛይናቸው የተበላሸ ነው በተባሉት ባነሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከሳምንታት በፊት በተመረቀውና ለዕድሳቱ 2.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል በተባለው የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤትም ጭምር ነው።

አንዳንዶቹ የሕንጻው ዕድሳት የተጠናቀቀው በዚህ ዓመት ቢሆንም የተጀመረው ከዓመታት በፊት በመሆኑ፣ እንዲሁም መንግሥት ዕድሳቱን ያካሄደው በጀቱን ታሳቢ አድርጎ ከካዝናው አውጥቶ ስለሆነ ብዙም አያስነቅፍም ቢሉም፣ አንዳንዶች ደግሞ መንግሥት ከካዝናው የሚያወጣው ብር የሕዝብ እንጅ የእርሱ ስላልሆነ ሕዝቡ ችግር ሲገጥመው ሊጠቀምበት ይገባል እንጅ ለቅንጦት መዋሉ አግባብ አይደለም ባይ ናቸው።

በተያያዘም መዘጋጃ ቤቱ እድሳት ተደረገለት እንጅ መሰረት ተጥሎ የተገነባ አዲስ ሕንጻ ስላልሆነ ይህን የተጋነነ በጀት ስለመጨረሱ ለማመን እንደሚከብድ ነው ትችቱ ሲነሳ የሰነበተው። ይህን በተመለከተም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አባሎች ወደሚመለከተው አካል ገብተው 2.2 ቢሊዮን የሕዝብ ብር የት ደረሰ ብለው ጥያቄ ለማቅረብ ቢሞክሩም ወደ ቢሮ እንዳይገቡ መደረጋቸውን በተለያዩ መልዕከት ማስተላለፊያ መንገዶች ሲገልጹ ሠንብተዋል። (ባለፈው ሳምንት የተባለ እና በዚህ ሀተታ ውስጥ መግባቱ ጥቅሙ አምብዛም ነው)
ታዲያ ለመዘጋጃ ቤቱ ዕድሳት እንዲሁም የዳያስፖራውን መምጣት ተከትሎ ለባነሮች የወጣው አላግባብ ወጪ ቅሬታ እያስነሳ ባለበት ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ መከናወኑን ምክንያት በማድረግ ለተሠሩና በቁጥር በርከት ላሉ ባነሮች እየወጣ ያለው አላስፈላጊ ወጪ መቆሚያው መቼ ነው በሚል ብዙዎች ይጠይቃሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here