በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ተሻሽሎ የነበረው የጸጥታ ችግር ዳግም ማገርሸቱ ተገለጸ

0
444

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ለወራት ያህል ሠፍኖ የነበረው አንጻራዊ ሠላም ጠፍቶ፣ በድጋሚ ንጹኃን ሰዎች በታጠቁ ኃይሎች እየተገደሉ መሆኑ ተገለጸ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ታጣቂዎች በንጹኃን ላይ ጥቃት እያደረሱ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸው፣ መፈናቀላቸው እና ንብረት መውደሙ አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ፣ በ2014 ጥቃቱ ለወራት ያህል ቁሞ አካባቢው ላይ አንጻራዊ ሠላም ሠፍኖ እና የአካባቢው ማኅበረሠብ ተረጋግቶ እንደነበረ ተገልጿል።

አንጻራዊ ሠላሙ ሠፍኖ የነበረው ወደ መተከል ዞን ያቀናው የጥምር ኃይሉ ሲያካሂደው በነበረው የተጠናከረ ኦፕሬሽን ሲሆን፣ ሠሞኑን ግን ችግሩ በድጋሚ ማገርሸቱን ነው ማወቅ የተቻለው።

ከነዋሪዎቹ መካካል መስፍን መለሰ የተባሉት ግለሰብ፣ ባሳለፍነው ሳምንት የጉምዝ ታጣቂ ኃይሎች በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት ሦስት ንጹኃን ሰዎች እንደሞቱ ማረጋገጣቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የሠነዘሩት ባሳለፍነው የካቲት 1/2014 ማክሰኞ ለዕሮብ ከንጋቱ 10 ገደማ መሆኑን ዳዊት አያሌው የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ አክለው ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ በሠነዘሩት ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ያሉት ዳዊት፣ ቁጥራቸውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም በርካታ ቤቶችም እንደተቃጠሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ከሟቾቹ በተጨማሪም፣ ኹለት ንጹኃን ሰዎች በተሠነዘረባቸው ጥቃት ጉዳት እንደደረሰባቸው ዳዊት አያይዘው አብራርተዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት የጉምዝ ታጣቂዎች፣ ከኦነግ ሸኔና ከሱዳን ከመጡ አሸባሪዎች ጋር በመተባባር ነው የተባለ ሲሆን፣ ሽፍታዎቹ ‹‹ኩኪ›› ተብሎ በሚጠራው ቦታ እንደሚገኙም ዳዊት አመላክተዋል።

አዲስ ማለዳ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው ስትል ጥያቄ ያቀረበችላቸው የቤኒሻጉል ጉምዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ መለስ በየነ፣ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አለም ቀበሌ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት በሽምቅ ገብተው መሆኑን የገለጹት መለስ፣ የሟቾቹ ብዛት በትክክል አይታወቅም ብለዋል። ሽምቅ ተዋጊያ በባህሪው በአንድ በኩል ኦፕሬሽን እየተሠራ በአንድ በኩል ገብቶ ጥቃት ማድረሱ አይቀሬ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ ሠሞኑን ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ የጸጥታ ኃይሉ ታጣቂ ቡድኑን የማጽዳት ሥራ እየሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“እኛ የጀመርነው ሥራ የኦፕሬሽን ሥራ ነው እንጂ ከእነርሱ ጋር ድርድርና ውይይት አይደለም” የሚሉት ኃላፊው፣ በዚህ ኦፕሬሽንም የመከላከያ ኃይል፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የሲዳማ፣ እንዲሁም የጋምቤላ ልዩ ኃይሎች አሰሳ እያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተያያዘም፣ ከዚህ በፊት ቁጥራቸው ወደ 250 ሺሕ ይሆናል የተባሉት ተፈናቃዮች ድጋፍ አግኝተዋል? አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ መለስም በበኩላቸው በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካይነት ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት።

ኃላፊው አክለውም፣ “አሁን ባለው ኹኔታ ምናልባት መንገዶች ሲዘጉ ባሉ የመቆራረጥ ኹኔታዎች ካልሆነ በስተቀር በአቅርቦት ደረጃ በእኛ በኩል ችግር የለም” ብለዋል።
አያይዘውም፣ የተፈናቃዮች ቁጥር እንደየጊዜው እንደሚጨምርና እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

የጉምዝ ሕዝብ ነጻ አውጭ ተብሎ የተደራጀው የጉምዝ ታጣቂ ለዓመታት በተከታታይ በሠዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመና ንብረት እያወደመ መሆኑን ገልጸው፣ ከ2014 ጀምሮ ቡድኑ እጅ መስጠት ካለበት እንዲሠጥ፣ ካልሆነ ደግሞ መመታት እንዳለበት ተወስኖ እየተሠራ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here