የዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጁ ብልሹ አሠራር ለጉዳት ተዳርገናል አሉ

0
461

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ሥር እንደሆነ የሚነገርለት የዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2013 ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጁ የአመራር ድክመት እና ብልሹ አሠራር የተነሳ ለጉዳት ተዳርገናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ተመራቂ ተማሪዎች ይህን ያሉት በዋናነት ኮሌጁ ተማሪዎቹን ባለማስመረቁ ነው። ተማሪዎቹ እንደሚናገሩት፣ ኅዳር 4/2014 እንዲመረቁ የጊዜ ሠሌዳ ውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ መጨረሻ ላይ ግልጽ ባልሆነ መንገድ የምርቃ ቀኑ መሠረዙን አንስተዋል።

ኮሌጁ ከእኛ በፊት የነበሩ ተመራቂ ተማሪዎችን ሳያስመርቅ እንዲሁ ነው የበተናቸው የሚለው ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የተመራቂ ተማሪዎች ተወካይ፣ ኮሌጁ ተማሪ ካለማስመረቁም በላይ እንደማንመረቅ የሚነገረን መጨረሻ ላይ በመሆኑ፣ በወቅቱ የማሳወቅ ኃላፊነት የሚሰማው አካል የለም እንድትል ያደርገሃል ሲል ተናግሯል።

የትምህርት ማስረጃችንም በመመረቂያ ቀናችን ሠሞን ሊሠጡን ሲገባ ያለምክንያት ከሦስት ወር በኋላ ስለሰጡን ብዙ የሥራ ማስታወቂያዎች አልፈውናል ሲል አመላክቷል።

ከዚህ ባለፈም፣ ከመጋቢት 2012 ጀምሮ እስከ ጥር 2013 ባለው ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ስለተቋረጠ ወርሀዊ ክፍያ አትከፍሉም ተብለን የነበረ ቢሆንም፣ የመመረቂያ ወረቀታችንን ልናወጣ ስንሄድ ግዴታ መክፈል አለባችሁ ተብለናል በማለት አብራርቷል።

በወቅቱ ትምህርት ለተዘጋባቸው ወራት ክፍያ እንደማይከፍሉ በኮሌጁ የፋይናንስ ተጠሪ በኩል ተነግሯቸው እንደነበርና በኋላ ግን አላልንም ብለው እንደካዱ ነው ተመራቂው የገለጸው።

ኮሌጁ ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመስማትና ምላሽ ለመስጠትም ፍቃደኛ እንዳልሆነ እና የሚመለከታቸውን ተወካዮች ሲጠይቁም ከአንዱ ወደ ሌላው በማመላለስ አንደማያነጋግሯቸው የተማሪዎቹ ተወካይ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት የተመራቂ ተማሪ ወላጅ እንዲሁ፣ አራት ዓመት አስተምረን እና ይመረቃሉ ብለን ብዙ ወጪና ጊዜ አጥፍተን መጨረሻ ላይ የምርቃ ሥነ- ሥርዓት የለም በመባሉ በጣም አዝነናል ነው ያሉት። ይህ የሆነውም ጤና ሳይንስ ኮሌጁ እና ዩኒቨርስቲው ውስጥ ያሉ አመራሮች ስለማይናበቡ እንደሆነ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

ሌላም ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ የተመራቂ ተማሪ ወላጅ እንዲሁ፣ ኮሌጁ የመንግሥት ይሁን የግል ማወቅ ያዳግታል ነው ያሉት። በዚህም ለልጃቸው 500 ብር በየወሩ ይከፍሉ እንደነበር ገልጸው፣ ኮሌጁ የመንግሥት ከሆነ ለምን እንደሚያስከፍል ግልጽ አይደለም ብለዋል። ለአብነትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚተዳደረውን እና ያለክፍያ ነው ተማሪዎችን የሚያስተምረው ያሉትን ጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅን አንስተዋል።

አክለውም፣ በወረርሽኙ ምክንያት ያልተማሩባቸውን ወራት ክፍያ ጠቅላላ ብር 5500 መጨረሻ ላይ ክፈሉ በመባላቸው ብዙ ልጆች ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። በኮሮና ወረርሽን ምክንያት መደበኛ ትምህርት አላገኙም የሚሉት ወላጅ፣ በአንድ ቀን አንድ የትምህርት ዓይነትም ያስተምሯቸው ነበር ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም በሕክምና ትምህርት ውስጥ በአንድ ቀን አንድ የትምህርት ዓይነት መጨረስ ተስፋ ያስቆርጣል ብለዋል።

አክለውም፣ ተመራቂዎቹ የቀራቸው ክፍያ ሳይኖር እየተሠጣቸው ያለው የትምህርት ማስረጃ ዋናው ሳይሆን ኮፒው እንደሆነም በቅሬታቸው አንስተዋል። ይህም ተመራቂዎች ዋናውን ማስረጃ በሚወስዱበት ጊዜ ሌላ ክፍያ ለማስከፈል ነው ብለዋል።

በተበላሸ የትምህርት አሰጣጥ የተነሳ ብዙ የድሃ ልጆች ያለውጤት ቀርተዋል የሚሉት ወላጅ፣ አመራሮቹም ለሕዝብና ለመንግሥት ያልቆሙ፣ በጥቅምና በወገን የተሰገሰጉ ናቸው የሚል ቅሬታም አንስተዋል። አሁንም ኮሌጁ የመንግሥት ነው ስለሚባል ብቻ ብዙ ተማሪዎች ሲመዘገቡ ይታያል፣ ግን የመንግሥት ነኝ በሚል የሚሠራውን ብልሹ አሠራር ሕዝቡ ቅድሚያ አውቆ ኮሌጁ ሲስተካከል ነው ልጆቹን መላክ ያለበት በማለት ገልጸዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችና ወላጆችም ይህ ኹሉ ችግር የሚፈጠረው በዩኒቨርስቲውና በኮሌጁ አመራሮች ድክመት እና ብልሹ አሠራር መሆኑን ያምናሉ።

የኮሌጁ ዲን ኩማ ጌታሁን፣ የተማሪና የወላጆቹን ቅሬታ አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮሌጁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቸኛው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንደነበር አንስተው፣ አሁን ላይ ኮሌጁ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ጋር በመዋሀድ ከከተማ አስተዳደሩ በሚያገኘው በጀት ለከተማው ማኅበረሠብ አገልግሎት የሚሰጥ የመንግሥት ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግሥት ኮሌጅ ሆኖ ለምን ያስከፍላል ለሚባለው ጥያቄም በሠጡት ምላሽ፣ የቀድሞ ተመራቂዎችን የከተማው ጤና ቢሮ ይቀጥራቸው እንደነበር አንስተው፣ ከጊዜ በኋላ ቢሮው በቂ የሰው ኃይል አለኝ በማለቱ ማኅበረሠቡ በክፍያ ልጆቹን እንዲያስተምር ተገልጾለት አውቆት ነው ልጆቹን ያስመዘገበው ብለዋል።

እንዲሁም፣ የጤና ትምህርት በአብዛኛው ተግባራዊ በመሆኑ ለተግባር ትምህርት 68 ብር ከ33 ሳንቲም፣ ለጹሑፍ ትምህርት ደግሞ 95 ብር ለአንድ ክሬዲት እንዲከፍሉ የከተማ አስተዳደሩ ለዩኒቨርስቲው የወከለው ቦርድ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

የክፍያ ወረቀት ተጠይቀው የጠፋባቸው ተማሪዎችም የእነሱን መረጃ ወደ ኋላ ሔዶ ማገላበጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን መረጃቸውን መጣል እንደሌለባቸው አስገንዝበው፣ ዋናው የትምህርት ማስረጃቸው የማይሰጣቸውም ድጋሜ ለማስከፈል ሳይሆን ታትሞ ስላልደረሰ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ተማራቂዎች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመመረቃቸው ያቀረቡት ቅሬታ አግባብ ነው ያሉት ዲኑ፣ ችግሩ የተፈጠረው በወረርሽኙና አገሪቱ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ኹኔታ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ሰኔ ወር አካባቢም የ2013 እና 2014 ተመራቂዎችን በጋራ ለማስመረቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም ተማሪዎች በትግዕስት እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here