በአማራ ክልል የወሊድ መቆጣጠሪያ ዕጥረት አጋጠመ

0
970

በአማራ ብሔራዊ ክልል የወሊድ መቆጣጠሪያ ዕጥረት ማጋጠሙን አዲስ ማለዳ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እረጋግጣለች፡፡

ዕጥረቱ በዋናነት ያጋጠመው ለሦስት ወራት በሚያገለግለውና በመርፌ በሚሠጠው የወሊድ መቆጣጠሪያ ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ዕጥረቱ ያጋጠመው በዋናነት በመንግሥት የጤና ተቋማት ሲሆን፣ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ኹሉም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያዎች እንደማይገኙ ተጠቁሟል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ባለሙያ ሲስተር ንብረት እያሱ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዕጥረቱ ያጋጠመው በኹሉም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ሳይሆን በዋናነት በመርፌ በሚሠጠው ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አማራ ክልል ያሉ እናቶች ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት መርፌ ተጠቃሚ ናቸው ያሉት ባለሙያዋ፣ ሌሎች ክልሎች ግን ወደ ሌሎች የወሊድ መቆጣጠሪያ አማራጮች ስለተሸጋገሩ ዕጥረቱ ጎልቶ አይታይባቸውም ብለዋል፡፡

አክለውም፣ ድሮ ይቀርብ የነበረው በዕርዳታ ነው፡፡ አሁን ግን በጤና ሚኒስቴር በኩል በግዥ የሚቀርብ በመሆኑ ከዶላር ጋር በተያያዘ መጓተቶች ይከሰታሉ፡፡ የግዥ ሒደቱና ገዝቶ ለማጓጓዝም ከሦስት እስክ ስድስት ወር ስለሚፈጅ ለዕጥረቱ መከሠት ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ዕጥረቱ የተከሠተው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መሆኑን ያነሱት ባለሙያዋ፣ አያይዘውም ችግሩ ከጦርነቱ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም፤ ሠላም በሆኑ አካባቢዎችም ዕጥረት ይስተዋላል ብለዋል፡፡

ኾኖም እናቶች ሌሎች የወሊድ መቆጣጠሪያ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡ ከዋጋ፣ የጎንዮሽ ጉዳትን ከመቀነስ፣ እንዲሁም የአገልጋይ ተገልጋይ ጊዜን ከመቆጠብ አንጻር ወደ ሌሎች አማራጮች መሸጋገር ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ እናቶች ሌሎች አማራጮቸን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ይሠራል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠርና ስብጥሩን በማብዛት ችግሩን ለመቅረፍ ሙከራ ይደረጋል እንጂ የተጠቃሚዎቹን ምርጫ ግን መገድብ እንደማይቻል ነው ያመላከቱት፡፡ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በመውሰድ የጤና ተቋማቱ ተዋውሰው እንዲጠቀሙ ይደረጋል የሚሉት ኃላፊዋ፣ የአማራ ክልል መርፌ ተጠቃሚ በመሆኑም የተሻለ ኮታ እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

የወሊድ መቆጣጠሪያ ዕጥረቱ አማራ ክልል ውስጥ የጎላ ይሁን እንጂ፣ ምርቱ ውጭ አገር ተመርቶ የሚመጣ በመሆኑ ዕጥረቱ አገራዊ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የዲኬቲ ኢትዮጵያ የሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ማኔጀር ሙሐመድ አሕመድ በበኩላቸው፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዕጥረቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኾኖም በሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች በተለይ ጦርነት ከተከሠተ በኋላ ዕጥረቱ ጎልቶ መከሠቱን አመላክተዋል፡፡

ድንገተኛ የሚወሰድና መርፌ እንጂ የረዥም ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዕጥረት የለም ያሉት ኃላፊው፣ ኾኖም ከተጠቃሚዎች ፍላጎት አንጻር ያለን በቂ አይደለም፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮም በቂ መጠን እየቀረበልን አይደለም ነው ያሉት፡፡

ዲኬቲ ኢትዮጵያ የወሊድ መቆጣጠሪያዎችን በቅናሽ ዋጋም ቢሆን የሚያቀርበው በዋናነት ለግል የጤና ተቋማት በመሆኑ እነሱ ጋር ዕጥረት የለም ማለት ይቻላል ነው ያሉት፡፡ አያይዘውም፣ የለጋሾች ቁጥር በመቀነሱ ባለፈው ዓመት 10 ብር ይሸጥ የነበረ የመርፌ ወሊድ መቆጣጠሪያ በዚህ ዓመት 30 ብር መግባቱን ጠቁመዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here