የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ማስጠንቀቂያ የሠጣቸው ሬዲዮ ብሮድካስት ባለፈቃዶች ሟርሴ መልቲሚዲያ ኃ.የተ.የግ.ማ (ጄ ሬዲዮ ጣቢያ 106.7)፣ አዲስ ኦንላይን የግንኙነትና የግብይት ሥራ ኃ.የተ.የግ.ማ (ሀበሻ ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ 98.7)፣ ትርታ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ (ትርታ ሬዲዮ 97.6) እና ኢትዮ ዋርካ መልቲ ሚዲያና ኮሚየኒኬሽን አ.ማ. (ዋርካ ሬዲዮ 104.1) ናቸው ተብሏል።
ሟርሴ መልቲሚዲያ ኃ.የተ.የግ.ማ (ጄ ሬዲዮ ጣቢያ 106.7) የተሠኘው ባለፈቃድ የሬዲዮ ፈቃዱን ካገኘ ጀምሮ ሙዚቃ ብቻ በማጫወት በውድድር ፈቃድ ከወሠደበት ውል ውጪ እየሠራና ውስን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለብክነት እየዳረገ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
በውድድር የሚገኝን ይህን ውድ የአገርና የሕዝብ ሀብት ለተፈቀደው እና ውል ለተገባበት ዓላማ እንዲውል በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ የተሠጠ ቢሆንም፣ በድርጅቱ በኩል የተለወጠ ነገር የለም ተብሏል። ስለዚህም ሬድዮ ጣቢያው እስከ መጋቢት 01/2014 ድረስ ውል በገባው መሠረት መደበኛ ሥርጭቱን ካልጀመረ ፈቃዱ በቀጥታ የሚሠረዝ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል፣ አዲስ ኦንላይን፣ ትርታ ትሬዲንግ እና ኢትዮ ዋርካ የተሰኙ ድርጅቶች በመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 80 መሠረት ከባለሥልጣን መ/ቤቱ የንግድ ሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ወስደው ከአንድ ዓመት በላይ ቢሞላቸውም፣ በሕጉ መሠረት መደበኛ ሥርጭት ባለመጀመራቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ድጋፍ፣ ማሳሰቢያ እና የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሲደርስ መቆየቱን ባለሥልጣኑ አስታውሷል፡፡
አሁንም መደበኛ ሥርጭት ያልጀመሩ በመሆኑ ለመጨረሻ ጊዜ እስከ መጋቢት 01/2014 ድረስ በገቡት ውል መሠረት መደበኛ ሥርጭት ካልጀመሩ በቀጥታ ፈቃዳቸው የሚሠርዝ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ድርጅቶቹ የተሠጣቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ አክብረው እስከ መጋቢት 01/2014 ድረስ መደበኛ ሥርጭት ካልጀመሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በዐዋጅ በተሠጠው ኃላፊነት መሠረት እጅግ ውሱን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ጨረታ አውጥቶ በማወዳደር ለአገርና ሕዝብ ጥቅም እንደሚያውል አሳውቋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014


