የአድዋ ጦርነትና ድል የሴቶች ጀግንነት እጅግ ከፍ ብሎ የታየበት ታሪካዊ ክስተት ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ የሴት ጀግኒቶችን አፍርታ አሳልፋለች፤ በተለያየ አገርን ለማዳን በተደረጉ ውጊያዎች ወቅትም የኢትዮጵያ ሴቶች ትልቅ ጀብድ ሠርተዋል። ‹ሴት የላከው ሞት አይፈራም!› እንዲሉ ጦረኞችን በማበረታታትና ስንቅ በማቀበል ከማገዝ ጎን ለጎን፣ የአድዋ ዘመን ሴቶች በጥንካሬአቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዛው በኢትዮጵያና ጣልያን መካከል በነበረ ጦርነት ጊዜ፣ ሕዝቡ ለአገሩ እንዲዋጋ ወረኢሉ እንዲከት የተደረገለትን ጥሪ ተከትሎ የዘመቱ ሴቶች ቁጥር እጅግ ብዙ ነበር።
በዚህ መሠረት ታዲያ በአድዋ ዘመቻ ከኻያ ሺሕ እስከ ሠላሳ ሺሕ የሚገመት ቁጥር ያላቸው ሴቶች እንደዘመቱ በምናለ አዱኛ የተሠራና በኢትዮጵያ ሴቶችና የጦርነት ክስተቶችን በተመለከተ በ2001 ይፋ የሆነ ጥናታዊ ሥራ ያመላክታል። በአገራችን ወግ እና ባህል መሠረት ጦር ሜዳ ሲባል የወንዶች ብቻ እንደሆነ ቢታሰብም፣ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ትግሎች ጀርባ እጅግ ጠንካራ ሴቶች ነበሩ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሴቶች በጦርነት ወቅት መሣሪያ በማቅረብ፣ ምግብ በማብሰል፣ ወኔን በመቀስቀስ እንዲሁም የጀግንነት ፉከራን በማቅረብ ከማበረታታት ባለፈ በውጊያው መካከል እየተሽሎከሎኩ ጥይት በማቀበልም ተሳትፎ አድርገዋል።
የቆሰለውን ከማከምም በተጓዳኝ የተሰዋውን ተዋጊ በክብር አፈር እንዲለብስም በማድረግ የሴቶች ሚና ትልቅ ነበር። ከዚህም ባለፈ በአድዋ ጦርነት በሴቶች ተሳትፎ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው እቴጌ ጣይቱ ናት። እቴጌ ጣይቱ መላ አዋቂ ጠንካራ እና በራስ መተማመን ያላት ሴት ስለነበረች። ሠራዊቱ ሲደክም አይዞን በማለት ብርታት ከመስጠት አንስቶ ቁልፍ የሆኑ ስልቶችን በመጠቆም ኢትዮጵያ ጦርነቱን እንድታሸንፍ አስችለዋል።
የዘመቱት ሴቶች ሥራቸው ብዙ ነበር። በጠጅ ቤት፣ በእንጀራ ቤት እና በጠላ ቤት ተከፋፍለው ያገለግሉ ነበር። ዳገት ቁልቁለቱን በመውጣት፣ እሾህ ጋሬጣ የሞላውን መንገድ በባዶ እግራቸው እየተጓዙ እህል ፈጭተው ውሀ ቀድተው እንጀራ ጋግረው ወጥ ሠርተው ያን ሁሉ ዘማች በመመገብ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት መስዋእትነት ከፍለዋል።
አደዋ ክስተት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድልና አረአያ ነው። በዚህ ዓለምን ያስደመመ፣ አውሮፓን አስደንግጦ አፍሪካን ባነቃ ታላቅ ድል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ዋነኛ ለውጦችንም አምጥቷል። አሁንም ታድያ ኢትዮጵያ እንደ አድዋ ዘመን ያሉ ሴቶችን የምትሻበት አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ትገኛለች። እንደ አድዋ ዘመን ጀግኒቶችን ትሻለች። እነዚህም ለሰላሟ፣ ለደኅንነት እና ለክብሯ የሚታገሉላት ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014


