ለረጅም ዓመታት አትክልትንም ሆነ ፍራፍሬን አብዝቶ መመገብ ያለምንም እንከን ለጤና ተስማሚ ነው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ይህ ያለጥያቄ ለዘመናት የቆየ ዕምነት ግን ከሠሞኑ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ እውን አትክልትን አብዝቶ መመገብ ለጤና እክል አይዳርግም? በሚል ተመራማሪዎች ጥናት አድርገው ያገኙት ውጤት ውዝግብን አስነስቷል፡፡
አትክልትን አብዝቶ የበላ በልብ ሕመም የመጠቃት ዕድሉን እንደማይቀንስ በምርምር አረጋግጠናል ያሉት ተመራማሪዎች፣ በግኝታቸው መሠረት አትክልትን አብዝቶ መመገብ ጎጂ ነው ባይሉም ይገመት እንደነበረው ጠቃሚ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህንን የተመራማሪዎቹን ውጤት በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች የተቃወሙት ሲሆን፣ ከፍተኛ ክርክርንም እያስነሳ ይገኛል፡፡
አትክልትን አብዝቶ መመገቡ ከልብ ሕመም በመከላከል ጤናን ይጠብቃል የሚለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ ዕምነት የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ እንዳላገኙ ያሳወቁት ባለሙያዎቹ፣ አትክልት ጭራሽ አትመገቡ ሳይሆን ሌላ ነገር ትቶ ብቻውን መመገቡ አይጠቅምም ብለዋል፡፡ አትክልት ለጤና ተስማሚ ነው የሚባለው ብቻውን አከታትሎ በመመገብ ሳይሆን፣ ከሌሎች ዓይነት ምግቦች ጋር በማቀላቀል የተመጣጠነ ምግብን በመመገብ ነው ሲሉ ልዩነቱን አስረድተዋል፡፡
የጥናት ውጤቱ በርካታ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች እንዳሉት፣ ምርምሩ ምንም አይጠቅምም ብሎ የሚያረጋግጥ ሳይሆን ከልብ ሕመም ጋር በተገናኘ ስለመጥቀሙ ማረጋገጫ ማግኘት አለመቻሉን ነው ያሳያል ያልነው በማለት ግኝታቸውን ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ አትክልትን አብዝቶ መመገብ ተመጋቢው ከልብ በሽታ እንዲጠበቅ ያደርጋል የሚለው ዕምነት መሠረተ ቢስ ነው ያሉ ሲሆን፣ በዚህም አስተሳሰብ ሳቢያ ይከሠት የነበረን ሞት ለመቀነስ ምርምሩ ይጠቅማል ማለታቸው ተሠምቷል፡፡
የልብ ሕመም በዕድሜ የገፉ ሠዎችን ብቻ ሳይሆን ወጣቶችንም ለሞት የሚዳርግ የዓለማችን ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ልብ ድካምና የደም አስተላላፊ ትቦዎች ጋር በተገኛኙ የሚከሠቱ ሕመሞች በአጠቃላይ የልብ ሕመም ተብለው ሊገለፁ የሚችሉ ሲሆን፣ ከአመጋገብ ጋር በተገናኘ በሽታው እንዳይከሠት ማድረግ ይቻላል የሚል በሠፊው የተሠራጨ ዕምነት በዘርፉ ምሁራን ይቀርብ ነበር፡፡
በቻይናና በእንግሊዝ ተመራማሪዎች ጥምረት የተካሄደው የምርምር ሥራ በአብዛኛው አትክልት ላይ ያለ ንጥረ ነገር ለሰውነታችን አደጋ ያስከትላል ባይልም፣ ከልብ ጋር በተገናኘ የሚከሠት በሽታን ለማስቀረት ግን ምንም ፋይዳ እንደሌለው ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በ‹ፍሮንቲርስ ኢን ኒውትሪሽን› መጽሔት ላይ የወጣው ይህ ግኝት፣ አትክልትን አብዝቶ መመገቡ ልብ ሕመምን ከመከላከል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው የተረጋገጠበት ነው፡፡
‹ኔቸር ወርልድ ኒውስ› ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ፣ በምሁራኑ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና ክርክር ተመልክተው ብዙዎች አስተያየት እየሠጡ እንደሆነ ነው፡፡ የጥናት ውጤቱ ያልተጠበቀ እንደመሆኑ ክርክር ማስነሳቱ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ አትክልት መመገብ አይጠቅምም የሚል ባለመሆኑ ሕብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብን እንዲመገብ ተመክሯል፡፡
ጥናቱ የተካሄደው በእንግሊዝ አገር ሲሆን፣ የ400 ሺሕ ሰዎች የጤና መረጃ ግብዓት ተደርጎ የተመረመረበት ነው፡፡ የግማሽ ሚሊየን እንግሊዛውያን የጤናና አመጋገብ ባህሪን መዝግቦ ከያዘ የጤና ባንክ ተወስዶ የተደረገው ጥናት፣ ከ2006 እስከ 2010 ድረስ የተመዘገቡ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የተካሄደ ነው ተብሏል፡፡
በጥናቱ የበሠለ አትክልት የሚበሉ ሳያበሥሉ ከሚበሉ ጋር ተነጻጽሮ የተገመገመ ሲሆን፣ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ እንግሊዛውያን የአመጋገብ ስልትንም ከግምት ያስገባ ነው ብለዋል፡፡ በግኝቱ አትክልት አይጠቅምም ማለት እንዳልሆነ ደጋግመው ለማስረዳት የተሞከረ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረ በጣም ጠቃሚ ነው የሚልን ዕምነት ምንም ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ነው ማወቅ የቻልነው ሲሉ ግኝቱን አብራርተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ ይህንን ቢሉም፣ የአገሪቱም ሆኑ የአሜሪካ ተመራማሪዎች ተቃውሟቸውን አሠምተዋል፡፡ ‹ሲኤን ኤን› ላይ እንደተዘገበው፣ ምንም ይባል ምንም አትክልትን መመገብ ለጤና ተስማሚ እስከሆነ ድረስ ለልብ ሕመም እንዳንዳረግም ያግዛል ሲሉ ሳይንቲስቶች የነበረውን ዕምነት አስረግጠው ለማሳመን ሞክረዋል፡፡
የልብ ሕመም በዓለማችን በርካቶችን ለሞት የሚዳርግ ሚሊየኖችን የሚያጠቃ አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ከሌሎች ሕመሞች በተለየ ድንገት የሚከሠት በመሆኑ ለበርካቶች ሞት እንዲሁም ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ሕመም ነው፡፡ የበርካቶቸን ሕይወት እንደሚያናጋ የሚታወቀው ይህ በሽታ፣ እያንዳንዱን አገር በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብን በማስወጣት ይታወቃል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በሽታውን የሚያመጣውን ምክንያት በመመርኮዝ በአመጋገብ መንስኤውን ማስቀረት እንደሚቻል ሲነገር ተኑሯል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን አትክልትን ብቻ እየተመገቡ ከበሽታው መዳን ያልቻሉ እንዳሉም ይነገራል፡፡
ጡት ማጥባትና የልብ ሕመም
ለልብ ሕመም የሚዳርጉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ አብዛኞቹ ከአመጋገብና ከጭንቀት ጋር የተገናኙ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ መንስኤዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም እንደመፍትሔ የሚቀመጡም የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ አመጋገብን ማስተካከል፣ ጭንቀትን ማስወገድ ልብ ድካምን የመሳሰሉ ሕመሞች እንዳይከሠቱ ያግዛል የሚል የቆየ ዕምነት ቢኖርም፣ አሁን አሁን ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ከላይ አመላክተናል፡፡
በሌላ በኩል፣ አዳዲስ ለመከላከል ይጠቅማሉ የሚባሉ መንገዶችም ይፋ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እናቶች ጡት ማጥባታቸው በልብ በሽታ የመጠቃት ዕድላቸውን ይቀንስላቸዋል የሚል የጥናት ውጤት ሠሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡
በአሜሪካ የልብ ማኅበር መጽሔት ላይ የወጣው ይህ ግኝት፣ በሕይወታቸው ለአንድ ጊዜም ቢሆን ልጃቸውን ያጠቡ ሴቶች በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ምንም አጥብተው ከማያውቁት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡ የሚያጠቡ እናቶች በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸውን በ11 በመቶ የሚቀንሱ ሲሆን፣ በልብ ድካም የመጠቃታቸው አዝማሚያም በ12 በመቶ ይቀንሳል፡፡ ከደም ማስተላለፊያ ትቦዎች ጋር በተገናኘ የሚያጋጥማቸው የጤና እክልም በ14 በመቶ ይቀንሳል ያሉት ተመራማሪዎቹ፣ አጠቃላይ ከልብ ሕመም ጋር በተገናኘ ለሞት የሚዳረጉትንም በ17 በመቶ እንዲቀንሱ ያደርጋል ሲሉ ግኝታቸውን አሳውቀዋል፡፡
ይህ የሠሞኑ ግኝት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ጡት ማጥባት ለሚጠባው ልጅ ብቻ ነው ጥቅም ያለው የሚለውን አስተሳሰብ የሚያስተካክልና እናትም ልጅም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያሳውቅ ነው ተብሏል፡፡ የሚያጠቡ ሴቶች በሚያጠቡበት ወቅት ደስታ ስለሚሰማቸው ይህ ስሜት ከልብ ጋር በተገናኘ እክል እንዳይፈጠር የማድረግ ብቃት አለው፡፡ ደስታ የደም ማስተላለፊያ መስመሮችን በዕጥፍ ሊያሠፋ የሚችል የተፈጥሮ ብቃት ስላለው እናቶች በማጥባት ራሳቸውን ከልብ ሕመም መጠበቅ ይቻላቸዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አንዲት እናት ልጅ ከወለደች አንስቶ ቢያንስ እስከስድስት ወሩ ጡት እንድታጠባ ትመከራለች፡፡ ይህ የሚባለው ለልጁ ጤናማነትና ጥንካሬ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ለእናትየውም ይጠቅማል መባሉ ይበልጥ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ያደርጋቸዋል ተብሏል፡፡ ጡት ማጥባት ለልብ በሽታ ብቻ ሳይሆን ደም ግፊትን (ሐይፐርቴንሽን)፣ እንዲሁም ‹ታይፕ2› የሚባለውን የስኳር ሕመም ለመከላከል ያግዛቸዋል፡፡
የልብ በሽታ አሜሪካንን በመሳሰሉ አደጉ በሚባሉ አገሮች የሴቶች ትልቁ ገዳይ በሽታ ነው፡፡ ኮሮና ከተከሠተ ወዲህም አድማሱ ሠፍቶ ብዙዎችን እንደገደለ እየተነገረ ነው፡፡ ‹ኖርዝ ኬንተኪ ትሪቢውን› ላይ እንደተጠቀሰው፣ በወረርሽኙ ሳቢያ ሠዎች አስፈላጊ ስፖርታዊ እንቅስቃሴያቸውንም ሆነ መደበኛ የጤና ክትትላቸውን ማድረግ ባለመቻላቸው የተጎጂዎቹ ቁጥር እንዲበራከት ምክንያት ሁኗል፡፡
ከአንድ ሚሊየን በላይ በሚሆኑ ሴቶች ላይ ከተካሄደ ጥናታዊ መረጃ ላይ በመነሳት እናቶች ተፈጥሯዊ የማጥባት ሒደቱን መጠቀማቸው ጤናቸው ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋል፡፡ ከበሽታ መጠበቅም ብቻ ሳይሆን ከሕመምም ያድናቸዋል፡፡ በማሽን ወተቱን አስመጥጠው በጡጦ ስለሚያጠቡ እናቶች ጥናቱ ያለው ነገር ስለመኖሩ ባይጠቀስም፣ ከበቂ በላይ ወተት አምርተው ልጃቸውንም እስከኹለት ዓመት ያጠቡ እናቶች፣ ለወተት ባንክ በመለገስ ወተት ማመንጨት የቸገራቸውን እናቶች እንዲያግዙ ተመክሯል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



