ልመና በሕፃናት ላይ የሚያሳርፈው ጠባሳ

0
1273

ህይወት ንጋቱ የአንድ ልጅ እናት ሲሆኑ፣ ልጃቸውን የሚያሳድጉት ጎዳና ላይ ላስቲክ ዘርግተው በሚያገኙት ሳንቲም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸውን አስከትለው በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ ጎዳናዎች የዕለት ምግብ ፍለጋ ሲባዝኑ የሚውሉት ህይወትን አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ ቤት ብለው የሚያድሩት ከመንገድ ዳር ጠጋ ብላ በምትገኝና ጠጋግነው በሠሯት የላስቲክና የካርቶን ደሳሳ ጎጆ ውስጥ መሆኑን አዲስ ማለዳ አይታለች፡፡

ባለቤታቸው በሞት ስለተለዩዋቸው ህይወት ልጃቸውን የሚያሳድጉት ብቻቸውን ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ ድሮውንም ከባለቤታቸው ጋር ሲጋቡ ደሳሳ ጎጇቸውና ኪሳቸው በፍቅር እንጂ በዕቃና በገንዘብ የተሞላ አልነበረም፡፡ ለሠው ፍቅር በቂ ነው፤ ኹሉም ነገር በጊዜው ይደርሳል ብለው የሚያምኑት ጥንዶቹ፣ ባልተንዛዛ ድግስ አነስተኛ ምሳ አዘጋጅተው አንዳንድ የቅርብ ሰዎችን በመጥራት ነበር ትዳራቸውን የመሠረቱት፡፡

ህይወት ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ ምግብ ኖረም አልኖረም፣ ራባቸውም ጠማቸውም፣ ተመገቡም አልተመገቡም፣ ቤታቸው በፍቅር የተሞላ ነበር፡፡ በተሟላ ቤት ከተጀመረ ትዳር ይልቅ ከባዶው ተጀምሮ ችግርን አብሮ በመጋፈጥ የሚመሰረተው ትዳር፣ የትኛውም ፈተና ቢመጣ ሊሸረሽረው አይችልም ብለው ስለሚያምኑ፣ ማጣታቸው ይበልጥ ያጠነከራቸው ልብ ለልብ የሚተዋወቁ ጥንዶች እንደነበሩ ህይወት ይናገራሉ፡፡

የሚተዳደሩት ባለቤታቸው ይገረም ኃይሉ የቀን ሥራ ሠርተው ይዘውት በሚገቡት ብር ነበር፡፡ ባለቤታቸው በተደጋጋሚ የቀን ሥራ ማግኘት ባለመቻላቸውና ተቀማጭ ብር ስላልነበራቸው የሚበሉት ያጣሉ፡፡ ከቀናት በፊት ከሥራ ውለው ሲገቡ ይዘውት የመጡትን የበቆሎ እሸት ሲጠግቡ በአልጋ ሥር አስቀምጠውት የነበረ ሲሆን፣ ከቀናት በኋላ የሚበሉት ሲያጡ ፈለጉትና ግማሽ በቆሎውን አግኝተው በብረት ምጣድ ሞቅ አድርገው በልተው እየተሳሳቁ ማደራቸውን ኹሌም የማይረሱት ትውስታችው መሆኑን ህይወት ይገልጻሉ፡፡
ከምግብ በላይ ፍቅር ያጠግባል የሚለውን ቃል በተዳጋጋሚ የሚያነሱት ህይወት፣ ምግብ ሆድን ሲሞላ ፍቅር ግን ሐሴትን ይሞላል ሲሉ ማነጻጸሪያ ያስቀምጣሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ፣ ባለቤታቸው በጠና ታመው ለትንሽ ጊዜ አልጋ ላይ ከዋሉ በኋላ እስከወዳኛው እንደተለዩዋቸው ህይወት ይናገራሉ፡፡
የትዳር አጋራቸውን ያጡት የጎዳና ተዳዳሪዋ ህይወት፣ እናትና አባታቸውን በሞት ያጡት ገና በሕፃንነታቸው ስለነበር ባለቤታቸውን እንደ አባትና እናት ጭምር የሚያዩዋ ነበሩ፡፡
ታዲያ ባለቤታቸውን በሞት ማጣታቸው የኑሮ ሸክሙን እያከበዳቸው ሲመጣ ወደ ጎዳና ህይወት ለመሔድ እንደተገደዱ ያወሳሉ፡፡

ህይወት እንደሚሉት ከሆነ፣ በርካታ ሰዎች በልመናው ተግባር መሠማራታቸውን ተከትሎ አሁን አሁን ለምነው የዕለት ምግብ የማግኘት ዕድላቸው እየቀዘቀዘ መጥቷል፡፡ በዚህም አሁን ላይ ከሚያልፉና ከሚያገድሙ መንገደኞች ብር ወይም ምግብ ለማግኘት የሚጠቀሙት ስልት “ሒድ ዳቦ ግዙልኝ በላቸው” ብለው ልጃቸውን በልመና በማሠማራት እንደሆነም አልደበቁም፡፡

ይህም ሆኖ፣ ልጆችን እንደ ብር መሠብሰቢያ ያደረጉ ሌሎች ሠዎች ከችግረኞች ጋር በተመሳሳይ ልጆቻቸውን ለልመና መላክ በመጀመራቸው ለምነው እንኳን ለመብላት እንደተቸገሩ ነው የገለጹት፡፡
አዲስ ማለዳ ህይወት ልጃቸውን ለልመና ሲልኩ በተመለከተችበት ወቅት፣ ልጁን ለልመና የላኩት እሱ ከእርስዎ የተሻለ ሆኖ ነው ወይ ስትል ላቀረበችው ጥያቄ፣ “ለተጨማሪ ገቢ የሚለምኑ ሠዎች በመበራከታቸው ሠጪዎች በመማረራቸው ብንለምንም ማጣትችንን የሚረዳን የለም፡፡ ስለዚህ ምናልባት ሕፃናቱ አሳዝነዋቸው ቢራሩላቸው ብለን ነው የምንልካቸው” ሲሉ ነው በዝርዝር ምላሽ የሠጡት፡፡

በአገራችን በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች፣ በተለይም በመዲናዋ ውስጥ፣ ልመናን እንደ ሥራ ያደረጉ የሚመስሉ በርካታ ሠዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

በርካታ ሠዎች፣ ቡትቶ ልብስ ለብሰው፣ አኮፌዳ አንጠልጥለው፣ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ሲለምኑ ይስተዋላሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መኪና ተከራይተው በድምፅ ማጉሊያ (ሞንታርቦ) እየለፈፉ ዕርዳታን የሚጠይቁም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ በመዲናዋ ዋና ዋና አደባባዮች ተዘዋውሮ ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት፣ በሆቴልና ሬስቶራንቶች፣ ብዙ ሕዝብ በሚራወጥባው እንደ መገናኛ፣ መርካቶና መሠል ቦታዎች፣ ተሸከርካሪዎች በሚቆሙባቸው የተለያዩ የትራፊክ መብራቶች፣ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ተቀምጠውና እየተዘዋወሩ የሚለምኑትን ሠዎች አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ተመልክታለች፡፡

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በተመለከተችው መሠረት፣ በልመናው ዓለም የተሠማሩት የዕለት ጉርስ ያጡ ሠዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ልመናን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ የሚቆጥሩና እንደ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ የሚጠቀሙትም ጭምር መሆናቸውን ሠምታለች፡፡
ከፊሎቹ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ብር የሚጠይቁት ማኅተም ያለው ወረቀት በመያዝ፣ ለልመና የተዘጋጀ ባነር በመለጠፍና መኪና ተኮናትረው በሞንታርቦ በመለፈፉ ሲሆን፣ ከፊሎቹ ደግሞ ሕፃናትን አሠማርተው እንደ መለመኛ በመጠቀም ነው፡፡

የመኪና ላይ ለማኞቹ፣ ከመኪናው ላይ ባለው ሞንታርቦ የዕርዳታ ጥሪ እያቀረቡ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ አነስተኛ ቀዳዳ የተበጀለት ካርቶን በመያዝ እግረኞችን እያገዱ፣ መብራትና አደባባይ ላይ ወደቆሙ ተሸከርካሪዎችም እየተጠጉ ብር ያሰባስባሉ፡፡
ብዙዎች በጉዳዩ ላይ የሚሠጡት አስተያየት፣ ምንም እንኳ በአገር ውስጥ ሕክምና የመዳን ዕድላቸው ከሽፎ ወደ ውጭ አገር ሔደው በመታከም ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሚለምኑ እውነተኛ ሠዎች ቢኖሩም፣ ለማጭበርበር የሚለምኑም እንዳሉ ነው፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ካነጋገረቻቸው ሰዎች መካከል ፍቅሩ ሞገስ የተባሉ ግለሰብ፣ “በመኪና ተዘዋውረው በመለመን ሕንጻ የሠሩ ሠዎችን አውቃለሁ” ሲሉ ነው ገጠመኛቸውን የተናገሩት፡፡
ፍቅሩ አክለውም፣ ልመናን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ አድርገው ተሠማርተዋል የተባሉት ሠዎች፣ “ሳይታመሙ የታመሙ አስመስለው የሐሰት ደብዳቤ በማጻፍና ማኅተም በማስመታት” ገንዘብ እንደሚያሰባስቡ ነው የተናገሩት፡፡

ገንዘብ ሠጭው ምንም ላይጎዳ ይችላል፣ ምክንያቱም ለተቸገረ ሠው መመጽወት እንዳለበት አምኖ እየመጸወተ ስለሆነ የሚሉት ፍቅሩ፣ ተቀባዩ ግን የነፍስም ሆነ የሥጋ ዕረፍት ማግኘት አቀበት ስለሚሆንበት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበረታበታል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል፣ በዚህ ወቅት ቸገረኝ ላለ ኹሉ ሳይገመግሙ መስጠትም ሠርቶ የሚበላ ሠውን ለስንፍና የሚያነሳሳ ድርጊት በመሆኑ፣ ሠጭዎችን ከተጠያቂነት አያድንምና ማስተዋል ያስፈልጋል ሲሉ ከገጠመኛቸው ተነስተው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ ማለዳ፣ ታመው ለመታከም የሚያስችል ገንዘብ የሌላቸው፣ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው ሠርተው መብላት ያልቻሉ እና የዕለት ጉርስ ለምነው የሚያገኙ የማኅበረሠብ ክፍሎች በተለመደው መንገድ ገንዘብ ለምነው ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ሕፃናትን ለልመና ማሠማራትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን ነው ማወቅ የቻለችው፡፡

አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ጎዳናዎች የሚጓዙ መንገደኞችን በመከተል እና የትራፊክ መብራት ላይ ያስቆማቸውን መኪናዎች በመጠጋት የሚለምኑ በርካታ ሕፃናት አሉ፡፡
ታዲያ ሕፃናቱን ለልመና የሚያሠማሩት ረዳት የሌላቸው ችግረኞች ብቻ ሳይሆኑ አቅም ያላቸውም ጭምር መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች፡፡ አዲስ ማለዳ የጉዳዩን እርግጠኝነት ካረጋገጠችበት መንገድ መካከል አንዱና የመጀመሪያው መንገደኞችን ተከትለው የሚለምኑ ሕፃናትን ማን ልኮህ/ሽ ነው የሚል ጥያቄን በማንሳት ነው፡፡

አዲስ ማለዳ ስድስት ኪሎ ጎዳና ላይ አንድን መንገደኛ እየተከተለ (እስከሚሰጠው ድረስ ተስፋ ሳይቆርጥ) “ዳቦ ግዛልኝ” ሲል ያገኘችው አፅናፉ ስዩም የተባለ ታዳጊ፣ “እማዬ እታች አለች፤ ሒድ ብር ጠይቀው ላንተ ይሠጥሃል ብላኝ ነው” በማለት ምላሽ ሠጥቷል፡፡
“ብዙ ጊዜ ለእማዬ ብር የምወስድላት እኔ ነኝ” የሚለው የአምስት ዓመት ታዳጊው፣ ለምንድን ነው ራሷ የማትጠይቀው ለሚለው ጥያቄም፣ “እኔ እንጃ፣ ለአንተ ይሰጡሃል ትለኛለች” ሲል ተናግሯል፡፡

ሕፃናትን ለልመና የሚያሠማሩት ከቸገራቸው ይልቅ፣ ብር አሰባስበው የቅንጦት ተግባራትን ለማከናወን ያቀዱ ሠዎችም ጭምር መሆናቸውን በርካቶች ያወሳሉ፡፡
አዲስ ማለዳም ጉዳዩን ይበልጥ ለማጣራት በመዲናዋ ስትዘዋወር መገናኛ አካባቢ ላገኘችው አንድ የስድስት ዓመትን ልጅ፣ “ቤተሰብ የለህም? ለምንድን ነው የምትለምነው?” ስትል ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ “ብር ይዤ ካልሔድኩ አባቴ ጎበዝ አይለኝም እኮ” ሲል ነው የመለሠው፡፡
ታዳጊው አክሎም፣ ቤተሰቦቹ ቤት እንዳላቸውና አከራይተውም ጭምር እንደሚኖሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የክልል ከተሞች በርካታ በልመና ሥራ የሚተዳደሩ ሠዎች እንዳሉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ መኪና ተከራይተው ከሚለምኑት ጀምሮ ሕፃናትን ለልመና ያሠማሩ በርካታ ሠዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች፡፡
ምንም እንኳ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውን ተመልክቶ ኹሉም ሳይቸግራቸው የሚለምኑ ናቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ ከመካከላቸው ግን ሳይቸግራቸው የሚለምኑም መኖራቸውን መዲናዋን በጥልቀት ለሚታዘብ ሰው የተደበቀ አይደለም፡፡

ልመና በሕፃናት ላይ የሚፈጥረው ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ
ልመና በሕፃናት ሥነ ልቦና፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሥነ ልቦና ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ድርጊቱ በሕፃናቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚሉት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ቴዎድሮስ ድልነሳው ናቸው፡፡

ጎዳና ላይ ባሉት መፍረድ ባይቻልም፣ ቤት አከራይተው የሚኖሩ ሠዎች ኹሉ ልጆችን እንደ ገቢ ምንጭ ይጠቀሙባቸዋል ሲሉ የተመለከቱትን የጠቆሙት ቴዎድሮስ፣ ይህ ድርጊት ሕፃናቱን ያለ ዕድሜያቸው ወደ ሥራ በማስገባት መብታቸውን የመጣስ ሕገ-ወጥ አሠራር ከመሆኑም ባሻገር፣ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ሕይወታቸው ላይ ጉዳት እንደሚያስከትልባቸው ነው ያብራሩት፡፡

እያንዳንዱ ሠው ወደ ሥራ የሚገባበት የራሱ የሆነ የዕድሜ ክልል እንዳለው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም፣ ሕፃናትን ያለ ዕድሜያቸው የወደፊት ሕይወታቸው ላይ ጥላሸት የሚሆን ሥራ ላይ ማሠማራት አግባብነት የሌለው ድርጊት መሆኑን የሥነ ልቦና ምሁራን ይስማሙበታል፡፡
“እናት አባቶቻቸው ቤት ኑሯቸው የሚለምኑ ሕፃናት አሉ” የሚሉት ቴዎድሮስ፣ አንዳንዶቹ ለምኑ ተብለው ተልከው ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከትምህርት ቤት ሲወጡ ሳንቲም እየለቀሙ ጣፋጭ ለመግዛት መሆኑን ከገጠመኛቸው በማንሳት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ሕፃናት ከሚያዩት ነገር ስለሚማሩ ትላልቆች የምናደርገው ድርጊት የተመረጠና አስተማሪ መሆን እንዳለበት የሚያሳስቡት ቴዎድሮስ፤ እንኳን መጥፎውን አስተምረናቸው ይቅርና የተመረጠና አስተማሪ አርአያ አሳይተናቸው እንኳ በተቃራኒው ሊረዱት እንደሚችሉ ምሳሌ በመስጠት አብራርተዋል፡፡

አንድ አባት ከዕለታት በአንደኛው ቀን ከልጃቸው ጋር አስቀድሰው ሲመለሱ ልጃቸውን ሲያድግ እንዲመጸውት ሊያሥተምሩት ፈልገው እጃቸው የነበረውን ሳንቲም ለየኔ ቢጤ እየሠጡ፣ “እየውልህ እንደዚህ ነው መስጠት ያለብህ” እያሉ የተግባር ትምህርት አስተምረውት ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ በሌላኛው ቀን አባትዮው ወደ ቅዳሴ ጎራ ብለው ስለነበር ቅዳሴው ተጠናቆ ሲወጡ እንደተለመደው በረድፍ ለተሰለፉት ሰዎች ምጽዋት ለመስጠት ሲዞሩ ልጃቸውን ስለማርያም፣ ስለጊዮርጊስ እያለ እንዳገኙት ነው ቴዎድሮስ ያጫዎቱን፡፡

የጎዳናው ሻወር የሚባለወን በመመስረትና በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት፣ ምግባቸውን በመስጠትና ንጽሕናቸውን በመጠበቅ 17 ዓመት ሆኖኛል ያሉት አስመሮም አስናቀ በበኩላቸው፣ ሰዎች ምጽዋት ሲሠጡ ለማን መስጠት እንዳለባቸው ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው በማለት ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስተያየታቸውን የሠጡት፡፡

በቀን 150፣ በሳምንት 800 የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንደሚንከባከቡ የገለጹት አስመሮም፣ ሠዎችን ለመርዳት ከጎዳና ላይ አንስተው ሲወስዱ የራሳቸው መስፈርት እንዳለቸውና ዝም ብለው “ቸገረን” የሚለውን ኹሉ እንደማይቀበሉ ነው የተናገሩት፡፡
ትክክለኛ ችግር የገጠመው ሠው ዐይነ ውኃው ያስታውቃል የሚሉት አስመሮም፣ በዚህ ወቅት ብርን ለመሰብስብ ሠርተው መተዳዳር የሚችሉት ኹሉ በልመና ስለተሠማሩ የዕለት ምግብ ያጡትን ለይቶ መመጽወት የኹሉም ማኅበረሠብ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡
ሠሞኑን በልመና የተሠማሩ በርካታ ሕፃናትን እየተመለከትኩ ነው የሚሉት አስመሮም፣ ፖሊስም ቢሆን ይህን ጉዳይ ዝም ብሎ ማየት የለበትም ብለዋል፡፡

ቴወድሮስ በበኩላቸው፣ በጨቅላነት ዕድሜያቸው ሕፃናትን ብር እንዲለምኑ ማድረግ በወደፊት ሕይወታቸው ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ሦስት አንኳር ነጥቦችን በማንሳት አስረድተዋል፡፡

የሥነ ልቦና ምሁሩ በመጀመሪያ ደረጃ ያነሱት ነጥብ፣ አዕምሯችን በተፈጥሮው የማስታወስና የአንድን ነገር መነሻ ከሌላኛው ጋር የማነጻጸር ባህሪ ስላለው፣ በልመና ሕይወት የቆዩ ሕፃናት፣ ትልቅ ሲሆኑ ምጽዋት ተቀባይና ከሌሎች ዕጅ ጠባቂ የመሆን ዕድላቸው የሠፋ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡

ቴዎድሮስ በኹለተኛ ደረጃ ያነሱት ጉዳይ፣ ልመና የሥራ ፍቅር አለመኖር ሊያመጣ እንደሚችልና ምጽዋትን በአጭር መንገድ ብር የማግኛ ዘዴ አድርጎ የማሳብ አዝማሚያ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ነው ለአዲስ ማለዳ ያብራሩት፡፡
በሦስተኛነትም፣ ልመና በሕፃናት ላይ የሚያሳድረው ጠባሳ የቤተሠብ ፍቅርን ከገንዘብ ጋር የማያያዝ የተሳሳተ አመለካከትን እንዲያዳብሩ ማድረግ እንደሆነ ቴወድሮስ አክለው ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ የቤተሠብ ፍቅርን ሕፃኑ ሲያስብ ቤተሠቦቹ የሚደሰቱት ብር ይዞ ሲመጣ መሆኑን ይረዳና ብር ከሌለው እንደማይወዱት ዓይነት ስሜት ሊሠማው እንደሚችል ነው ያብራሩት፡፡
ሌላውና የመጨረሻው ቴዎድሮስ ሊሰመርበት ይገባል ያሉት ፍሬ ሐሳብ፣ በተለይም ተሸከርካሪዎችን በመጠጋት የሚለምኑ ሕፃናት አደጋ እንዳይደርስባቸው በቅድሚያ ወላጆች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውና ሌሎች አካላትም እንደ ዜጋ ትብብር ቢያደርጉ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ነው፡፡

ቴዎድሮስ አያይዘውም፣ ይህ ስሜት የሚያድርባቸው ሕፃናት አጭበርባሪ፣ ሌባ፣ ከመሥራት ይልቅ ገንዘብን በአቋራጭ መንገድ በልመና ለማግኘት የሚቃትቱ የመሆን ዕድላቸው የሠፋ እንደሚሆን ነው የጠቆሙት፡፡

መፍትሔው ምንድን ነው?
ለተዘረዘረው ችግር መፍትሔው ምንድነው የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ አዲስ ማለዳ ከምሁራኑ ያገኘችው ምላሽ መጽዋቾች የሚሠጡት ሰው ችግረኛ መሆን አለመሆኑን አጢነው መስጠቱ ተመራጭ መሆኑን ነው፡፡
ተቸግረው ሕፃናትን ለልመና የሚያሠማሩ ሰዎች ደግሞ ሕፃናቱ የመኪና አደጋ እንዳይደርስባቸው በቅርብ ርቀት መከታታል፣ እንዲሁም ልመናን ጊዜያዊ ተግባር እንጅ ዘላለማዊ አድርገው እንዳይለማመዱት ማስተማር እንደሚገባም ቴዎድሮስ አብራርተዋል፡፡
የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን ከጎዳና አንስተው በመንከባከብ 17 ዓመት ያስቆጠሩት የጎዳናው ሻወር መሥራች አስምሮም በበኩላቸው፣ በተለይም መብራት ላይ የሚቆሙ መኪናዎችን ተጠግተው የሚለምኑ ሕፃናት ለአደጋ ስለሚጋለጡ ቤተሰቦቻቸው ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ምጽዋት ሲሠጡ ካገኘቻቸው ሰዎች መካከል እመቤት ካሳው የተባለችው ወጣት ለምንድነው የምትመጸውችው ብላ ጥያቄ አቅርባለች፣ “ምንም ይሁን የእመቤቴን ሥም ከጠራ እሰጠዋለሁ” ያለች ሲሆን፣ ሌላኛዋ ጓደኞዋ ደግሞ “አሳዘነኝ፤ ርቦኛል ሲል ርሃብን ስለማውቀው እንዳይርበው ፈለኩ” የሚል ምላሽ ሰጥታለች፡፡

ራሱ ይጠየቅበት እንጅ፣ የተራበንና ያልተራበን፣ ትክክለኛውን ከችግረኛው፣ እውነተኛውን ከአስመሳዩ እንዴት መለየት ይቻላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄና አቋም ነው፡፡
በጉዳዩ ልምድ ያላቸው አስምሮም በበኩላቸው፣ ሲሰጡ የተለያየ ሰው የሚሰጥበትን ዐላማና ለማን መስጠት እንዳለበት ማወቅ እንጅ፣ መስጠት ብቻ እንደሌለበት ነው ምክራቸውን የለገሱን፡፡
ሌሎች ተመሳስለው በልመና የተሠማሩት ሰዎችን ቁጥር የሚያመላክት ጥናት ባለመኖሩ፣ በኢትዮጵያ በጠቅላላ 88ሺሕ 960 የሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡

ከእነዚህም መካከል 3ሺሕ የሚሆኑት ሰዎች ድጋፍ ባደረጉላቸው የመንግሥትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከጎዳና ሕይወት መገላግል የቻሉ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 85ሺሕ 960 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ደግሞ፣ የጎዳና ሕይወትን በመምራት ላይ መሆናቸውን በተለያየ ወቅት የወጡ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here