ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ ከፍተኛነት የምትሞገሰውን ያህል ዜጎቿ ንፁህ ውኃ እንደማይጠጡ ይታወቃል፡፡ ከከተማ ራቅ ብሎ የሚኖረው፣ እንኳን ንፁህ ውኃ ሊጠጣ የሚጠጣ ውኃ በአቅራቢያው ለማግኘትም ፍዳውን እንደሚያይ ግልጽ ነው፡፡ ይህ በአቅራቢያ ውኃ የማግኘት ችግር ሴቶችን ለድካምና እንግልት አልፎ አልፎም ለጥቃት ይዳርጋል፡፡
በኢትዮጵያ ንፁህ ውኃ የሚያገኘው ዜጋ ቁጥር ጥናቱን እንዳደረጉት አገራትና እንደዓለም አቀፍ ተቋማቱ መረጃ ይለያያል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በ2020 ባወጣው ሪፖርት 57 በመቶው ኢትዮጵያዊ ንፁህ ውኃ ያገኛል ሲል፣ ከ30 ዓመት በፊት ከነበረው ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል ይላል፡፡ መፀዳጃ ቤትን ከመጠቀም አኳያ ግን 3 በመቶ የነበረው ወደ 28 በመቶ ብቻ ነው ያደገው በማለት ብዙ እንደሚቀር ይናገራል፡፡
ሌሎች ደግሞ የውኃ አቅርቦቱን ከ25 በመቶ አያስበልጡትም፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሠቱ በሽታዎች በንፁህ ውኃ ዕጥረት የሚከሠቱት ውኃ ወለዶቹ ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሸፍኑ መሆናቸውን የዩኒሴፍ መረጃ ያሳያል፡፡ ‹ዋተር ዶት ኦርግ› ባካሄደው ጥናት መሠረት ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሠት የውኃ ዕጥረት ዋና ዋና ምክንያቶቹ ድርቅና ፖለቲካ ግንባር ቀደም ናቸው ይላል፡፡ 42 በመቶ ኢትዮጵያውያን ብቻ ንፁህ ውኃ ያገኛሉ የሚል ሲሆን፣ 11 በመቶዎቹ ብቻ ደግሞ በተገቢው የመጸዳጃ መንገድ ይጠቀማሉ ብሏል፡፡
የውኃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከተወሠኑ ዓመታት በፊት በዘመቻ መልክ ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡ በተለይ የገጠሩ ማኅበረሠብ ውኃ እንዲያገኝ በሚል በግብረ ሠናይ ተቋማትና በየአካባቢው ማኅበረሠብ ሲደረግ የነበረው የጉድጓድ ቁፋሮ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባይታወቅም፣ አሁንም ድረስ ንፁህ ውኃ የማያገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር እንደአጀማመሩ አለመሠራቱን መናገር ይቻላል፡፡
የገጠሩ ማኅበረሠብ የውኃ ችግር ትኩረት አጥቶ፣ ትልቅ በጀትና ቅድሚያ የሚሠጠው ለከተማው ነዋሪ እንደሆነ ከሚያዘው በጀት መረዳት ይቻላል፡፡ ለማከሚያ ኬሚካል ከሚወጣ ወጪ ጀምሮ ለማሠራጨትና የአረጁ ማስተላለፊያዎችን ለማደስ የውኃ ፍሳሽ ባለሥልጣን የሚባለው የመንግሥት ተቋም ለዓመታት ሲሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን፣ ተቋሙ እንደሚያቀርበው ውኃ በአገልግሎቱ ሕብረተሠቡን ማርካት ሳይቻለው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፍጆታ ዋጋውን ጨምሮ ብቅ ቢልም፣ አገልግሎቱ እንደገቢው በመሻሻል ፈንታ ማሽቆልቆሉን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡
እንደኤሌክትሪክ ኃይል ውኃን በፈረቃ የሚያገኘው ከተሜ ከመብዛቱ አንፃር፣ ስለውኃ ችግር ማውራት የሚሰለችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ዳገት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ውኃ እየገዙ በማመላለስ የሚያዩት ፍዳ ምንም መሻሻል አለማሳየቱን አሁንም በምሬት ይናገራሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ቀን ውኃ ማግኘት እንደሎተሪ ዕድለኛ ማስባል ብቻ ሳይሆን፣ ምን ታያቸው እንስኪያስብል ድረስ ነዋሪውን የሚያጠራጥር ሆኗል፡፡
ውኃውን ለማዳረስ ያን ያህል አስቸጋሪ ናቸው በማይባሉ ዳገት በሌለባቸው አካባቢዎች ጭምር ውኃን እንደፈለጉ ማግኘት ቅንጦት እንደሆነ የሚነገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ሌሊት ሌሊት የተወሠነ ሰዓት ጭል ጭል እያለች የምትመጣን ውኃ እንቅልፍ አጥቶ የሚጠብቀውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ችግሩ ሌሊት ተነስቶ በዕቃ መሙላቱ ብቻ ሳይሆን፣ ኃይልም ስለማይኖራት በብርድ ለሰዓታት ቆሞ መጠበቅም የብዙዎች ምሬት ከሆነ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡
በፊት በፊት በእነዚህ አካባቢዎች በዚህ በዚህ ቀን ተብሎ ተዘርዝሮ ውኃ የሚጠፋበት ቀን አስቀድሞ ይታወቅና ዝግጅት እንዲደረግ ይነገር ነበር፡፡ አሁን ግን ብዙዎች ለቀናት፣ ጭራሹንም ለወራትም ሊሆን ይችላል፣ ውኃ ጠፍቶባቸው ሊያሳውቁ ሲሄዱ እንደማይታወቅ ጭምር መርዶውን እዛው ማሳወቅ ከነበረበት አካል ሲጠይቁ የሚረዱም አሉ፡፡
ውኃ ማግኘት የዜጎች መብት ቢሆንም፣ በተፈለገበት ጊዜና መጠን ለማግኘት እንደማይቻል አብዛኛው ያውቀዋል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ለሳምንታት ብቅ የማትል ሲሆን፣ ሕብረተሠቡ ተስፋ ቆርጦ እንደዱሮም በሬዲዮ ማስነገሩንም ትቷል፡፡ በፊት በፊት ድንገት ውኃ ሔደች ይባልና፣ “ይዟቸው ይሒድ” የሚል የእናቶችን እርግማን ያሠማን ነበር፡፡ የእርግማኑ ብዛት ተጠራቅሞ ነው መሰል፣ አሁን አሁን ውኃዋ የምትቀርበት ጊዜ እንደሚበልጥ ጥናት ቢደረግ ማረጋገጥ የሚቻል ጉዳይ ነው፡፡ ውኃ መጣች ብለው የሚደሠቱ መብራት ሲመጣ እንደሚጮኽው ለመሆን የቀራቸው ነገር እንደሌለ የሚቀልዱም አሉ፡፡
የዕጥረቱ መንስኤ
ኢትዮጵያ የውኃ ማማ እየተባለች፣ “የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው” እየተባለ እንደሚተረተው ብዙኅኑ ንፁህ ውኃ የማያገኝበት ኹኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ በረሃማና ድርቅ በሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በመደበኛነት ከሚያጋጥማቸው ዕጥረት በተጨማሪ፣ አሁን በደቡብ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ግዛቶች የተከሠተው ድርቅ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሠቱ ዕጥረት እንደሚኖር ግልፅ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ክስተት በሚስተዋልበት ኹኔታ ከአንድ ቦታ ወደተጎዱት አካባቢዎች በቦቴ ውኃ በማመላለስ ችግሩን ለመቀነስ ቢሞከርም፣ ከስፋቱ አኳያ መንስኤው ተፈጥሯዊ በመሆኑ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ኹኔታዎች በቀጣይ ቢከሠቱ፣ ለመቋቋም የሚያስችሉ (መጠባበቂያ እህል እንደሚባለው) ጉድጓዶችና ማጠራቀሚያዎች አስቀድሞ ለወደፊቱ እንዲያገለግሉ መቆፈርና መገንባት እንዳለባቸው አመላካች ነው፡፡
የተፈጥሮ አደጋ ባልተከሠተባቸው የከተማ አካባቢዎች የሚስተዋለው የውኃ ዕጥረት ደግሞ በሠው ሰራሽ ምክንያት የሚከሠት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፣ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በብዙ ከተሞች የተለመደው የውኃ ሥርጭት በመቋረጡ፣ ሕብረተሠቡ ለከብቶቹ እንኳን የማያቀምሳቸውን የተበከሉ ጅረቶችን ከብዙ ዐሥርት ዓመታት በኋላ ለመጠጣት ተገዶ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም በርካቶች ለጤና እክል ተዳርገው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ለወደፊቱም ሊከሠቱ እንደመቻላቸው መጠባበቂያ ዝግጅት መንግሥት ባያደርግ እንኳን ሕብረተሠቡ በራሱ መዘጋጀት እንዳለበት የተማረበት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ከጥንት የነበረ የምንጭ ጉድጓድን፣ የቧንቧ ውኃ አለ ብለው ለቤት መሥሪያ ብለው የደፈኑና ከጥቅም ውጭ ያደረጉ በእንዲህ አይነት ወቅት ምን ያህል እንደሚቆጩና ከክሠተቱ እንደሚማሩ ለማንም ግልፅ ነው፡፡
ማኅበረሠብን በጅምላ ውኃ ሊያሳጡ ከሚችሉ የተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ምክንያቶች በተጨማሪ፣ የዝናብ ዕጥረት ሌላው ውኃ በፈረቃ እንዲዳረስ የሚያደርግ ምክንያት ነው፡፡ በቂ የውኃ ክምችት አለመኖር ብቻ ሳይሆን ውኃን ሽቅብ ለማስፈንጠርና በየአካባቢው ለማዳረስ የሚያስፈልግ የኃይል ዕጥረት ሲኖርም ውኃውን ለማዳረስም አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነገራል፡፡ ውኃ ማከሚያ ንጥረ ነገሮች ከሌሉ አሊያም ማጣሪያው ዕድሳትና ማሻሻያ የሚደረግለት ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎቱ እንደሚቋረጥም ግልፅ ነው፡፡
ሌላው በአገልግሎት ሠጪው አካል ለዕጥረቱ በምክንያትነት የሚጠቀሰው የከተማ ፍልሰት ነው፡፡ ከገጠርም ሆነ ከከተማ ወደ ዋና ከተማ መኖሪያውን የሚቀይረው ሕብረተሠብ ወደ አንድ ቦታ ሲከማች የመሠረተ ልማት ፍላጎትን ይጨምራል፡፡ ይህም በዘርፉ ከሚደረግ መሻሻል ጋር ስለማይመጣጠን ለችግሩ መንስዔ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡
አብዛኛው ሕብረተሠብ የሚያበስልበትና የሚጠጣው ውኃ በጊዜ ሒደት ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንድ ድርጊቶቹ ግን ከዘመናዊነት ጋር በተገናኘ መቀየራቸው ለዕጥረቱ በምክንያትነት ይነሳል፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ በፊት አንድ ሰው መፀዳጃ ቤት ሲጠቀም የሚጠቀመው ውኃ እጁን የሚታጠብ ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን አሁን ግን የከተማ ነዋሪው ሽንት ቤት ተጠቅሞ በአንድ ጊዜ የሚለቀው ውኃ በትንሹ ከአምስት ሊትር እንደማያንስ ባለሙያዎቹ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህም ለመታጠቢያ የሚጠቀመውን ሳይጨምር ነው፡፡
በሌላ በኩል ገላውን ወንዝ ወርዶ ከመታጠብ የተገላገለው ማኅበረሠብ፣ ቤቱ አሊያም ባገኘበት “እናሸንፋለን” እንደሚባለው በጆግ እየቀዳ ሲታጠብ የሚጠቀመው፣ ሻወርም ሆነ በገንዳ ሲሞላ ከሚጠቀመው አይነጻጸርም፡፡ በየቦታው በተከፈቱ ሻውር ቤቶች ጥቅም የሚሠጠው ውኃ ከመብዛቱ ባሻገር፣ ልብስን በማሽን የሚያጥበው ቁጥርም በመጨመሩ ፍጆታው እያደር እንደሚጨምር ዕሙን ነው፡፡
ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውኃ ዕጥረት እንዲባባስ ያደረገው የውኃ አጠቃቀማችን እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዩኒቨርስቲዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በመሳሰሉ ተቋማት በየቀኑ ሳይጠቅም የሚባክነው ውኃ እያንገበገባቸው የሚናገሩ ቢኖሩም፣ ጥቆማቸውን ሠምቶ በአግባቡ እንዲውል የሚያደርግ ተቆርቋሪ አልተገኘም፡፡ ሌላው አትክልት ለማጠጣትና በየመንገዱ ያሉአበቦችን ለማጠጣት የሚውለው የውኃ መጠን ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ከወንዝ የሚቀዳ ነው ቢሉም፣ የወንዙ ውኃ የሚሞላውን መቀነስ በተዘዋዋሪ የውኃ ዕጥረት የሚከሥት ነው ይላሉ፡፡ በየቤቱ ለማይበላ ለዓይን ምግብ ብቻ ተብሎ በበጋ ሳርን ጭምር ለማጠጣት የሚፈሰው ውኃ የትየለሌ እንደሆነ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡
በኤንባሲዎች፣ በባለሃብቶች መኖሪያና በተለያዩ ተቋማት ግቢ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የሚባክን ውኃ አቅም ባላቸው ባለሀብቶች የሚከፈልበት ቢሆንም፣ ድሃውና ዳገት ያለው መክፈል የሚችልበትን ውኃ እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ ለውበት ተብሎ ለፏፏቴና ለፋውንቴን የሚውለውም ውኃ ተመላላሽ ቢሆንም፣ እንደመዋኛ ገንዳ ውኃው መቀየሩ ስለማይቀር አሳሳቢ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ከሁሉም ይልቅ የውኃ ብክነት የሚያስከትለው በየቦታው በግንባታም ሆነ በተለያየ ምክንያት ቧንቧ እየፈነዳና እያፈሰሰ ዝም የሚባለው ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ ቦታ ምንጭ ነው በሚል ለዓመታት ሲፈስ የነበረ ትቦ በአጋጣሚ ለሌላ ሥራ ሲቆፈር ታውቆ ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነት ኹኔታ የሚባክነው የውኃ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ አገልግሎቱን የሚሠጠው ተቋም ጭምር ስለሚያምንበት በሚያወጣው ሪፖርት ግምቱን ያስቀምጣል፡፡
ሕብረተሠቡን ያማረሩ ጉዳዮች
ውኃ እንዲያጥር የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ሕብረተሠቡን የሚያማርረው ማጠሩ ሳይሆን በፍትሐዊነት ባለመከፋፈሉ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የአንድ ሠፈር ነዋሪዎች ለሳምንታት ተበደልን ብለው ቅሬታ ለማሰማት አገልግሎት የሚሠጠው ተቋም ጋር ተገኝተው ነበር፡፡ የተመለሰላቸው መልስ፣ “በሠፈሩ ሀብታም ስለሚበዛ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር ይኖራችኋል ተብሎ ነው” የሚል አሳፋሪ ምላሽ ከአንድ ሠራተኛ ተነግሯቸው ነበር፡፡ በዚህ ስሌት ሌሊት ሌሊት ለጥቂት ጊዜ የሚለቀቅላቸው ቢሆንም፣ ማጠራቀሚያዎቹ ከፍታ ቦታ ላይ ስለሚኖሩ ውኃው ኃይል ስለማይኖረው ጭራሹኑ ማግኘት እንደማይችሉ ተናግረው ነበር፡፡ ማጠራቀሚያ የሌላቸው ሌሊት ሰዓቱ እንዳያልፋቸው በመጠበቅ ስለተሰቃዩ እንዲሻሻል ተደርጎላቸው ነበር፡፡
በሌላ በኩል፣ “ለባለሥልጣናት ሠፈር ቅድሚያ ይድረስ” በሚል የመቆጣጠሪያ ቫልቭ መግቢያቸው ላይ ተደርጎባቸው፣ እንዲሁም የሚያልፍላቸው የውኃ መጠን እንዲገደብ ትቦው ውስጥ ቡሽ ተወትፎባቸው በውኃ ዕጥረት እንዲማረሩ የተደረጉም ነበሩ፡፡ ይህ ዓይነት መድሎ እንደሚፈፀም የሚታወቅ ቢሆንም ምንም ማድረግ ሳይቻል አሁንም ቀጥሏል፡፡
ሌላው አሳፋሪ ነገር ደግሞ ከሙስና ጋር በተገናኘ የሚደረገው አሻጥር ነው፡፡ አንዳንዶች ሲናገሩ እንደሚሠማው፣ ብር የሚሠጡ አካባቢዎች ውኃ እንዳይቋረጥባቸው የሚያደርጉ ሠራተኞች መኖራቸው ሲሆን፣ የምስጉኖቹን ጭቃና አቧራ ሳይሉ የሚያገለግሉትን ሥም የሚያጎድፉ መሆናቸው በሥሞታ መልክ ይቀርባል፡፡ አሁን አሁን ለቀናት ውኃ የሚጠፋባቸው አካባቢዎች በአይሱዚ ጭነት መኪና ሮቶ በመባል የሚታወቀውን ውኃ ማጠራቀሚያ ጭነው የከርሰ ምድር ውኃ ነው እያሉ ለሽያጭ የሚያጓጉዙ በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ ነው፡፡ በመደበኝነት እንዲህ ዓይነት ሥራን ለመሥራት ትልቅ ወጪ የሚያወጡ ግለሰቦች፣ ገቢያቸው ከውኃ ዕጥረት ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው አላግባብ ይበለፅጋሉ ለሚለው ሥሞታ ማስረጃ ሲሆኑም ይሠማል፡፡
እንዲህ ዓይነት የሕብረተሠቡ ቅሬታ እንዳለ ሁኖ፣ ነዋሪው ተደራጅቶ ለማመልከት ሲሔድ ሆን ተብሎ ለቀናት የተዘጋ ይመስል ይከፈትላችኋል እየተባለ እንዲመለስ መደረጉ ጥርጣሬውን እንደሚያጠናክር ይናገራሉ፡፡ ይህን ዓይነት መልስ ካገኙ በኋላ ለትንሽ ጊዜ ይለቀቅና ወዲያው ወደ ነበረበት መመለሱ ይበልጥ እያጠራጠራቸው እንዲጣራላቸው ቢወተውቱም ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ የውኃ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባለመሆኑ ዕጥረት የሚፈጥሩ ምክንያችም ሆኑ ሠበቦች ተስተካክለው ሕብረተሠቡ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኝበት ጊዜ እንዲመጣ በርብርብ ሊሠራበት ይገባል፡፡
ለውኃ ዕጥረቱ መንስዔ ከሆኑ በርካታ ምክንያቶች መካከል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና እርጅናም ይጠቀሳል፡፡ የቀደሙ ዝርጋታዎችን በፕላስቲክ እንዳዲስ የመተካቱ ሥራ ከዚህ ቀደም በዘመቻ መልክ ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም እንዳላለቀ የሚናገሩ አሉ፡፡ ሌላው አዳዲስ ሠፈሮች ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ካርታ ስለሌላችሁ ግቢያችሁ ውስጥ አናስገባም የሚባለው አሠራር ነው፡፡ መስመሩ በደጃፋቸው እንዲያልፍ እየተደረገ ቆጣሪውም ሆነ ተከፋቹ ቧንቧ መንገድ ዳር ተደርጎ ለቁጥጥር ስለሚያስቸግር ለብክነት ያጋልጠዋል፡፡ ይህ ዓይነት አሠራር እንዲቀር በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየተናበቡ የመሥራቱ ነገር አሁንም ምንም መሻሻል ስላልታየበት ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በ2019 ባካሄደው የውኃ ብክነትን ለመቀነስ በሚረዳ ሥልጠና ላይ ኹለት ዓይነት ብክነቶች እንዳሉ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ የከተማ ውኃ አገልግሎቶች የውኃና ፋይናንስ ውጤታማነት ማሻሻያ ሥልጠና መመሪያው ላይ እንደሚለው ‹ፊዚካልና ኮሜርሻል› የተባሉ የብክንት ዓይነቶችን ለመቀነስ የሚታወቅበትን፣ እንዲሁም ጥቆማ ሲደርስ መደረግ ያለበትን አሠራር ባለሙያው እንዲያውቀው ይዘረዝራል፡፡ ይህ የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ አብዛኛው አባካኝ ተጠቃሚው እንደመሆኑ ተመሳሳይ የግንዛቤ መስጫ አሠራሮች በማስታወቂያ መንገድም ሆነ በተለያየ መልኩ ሲቀርቡ አይታዩም፡፡
በተቋሙ ሠራተኞችም ሆነ በአሠራሩ ላይ የሚቀርቡ ሥሞታዎችን በተመለከተ ተቋሙ ምላሽ እንዲሠጥ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሠርካለም ጋር በተደጋጋሚ በመደወል ሞክረን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
62 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ንፁህ ውኃ እንደማያገኙ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ በዓለም ደረጃ ካለው ዕጥረት አኳያ የኢትዮጵያውያን ችግር 7.5 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በዓመት ወደ 76 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃን ይጠቀማሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



