የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ማን ናቸው?

0
1465

የካቲት 14/2014 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ለተቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ11 ኮሚሽነሮችን ሹመት አጽድቋል። የኮሚሽነሮቹ ማንነት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

መስፍን አርአያ(ፕ/ር)
መስፍን አርአያ(ፕ/ር) በቅርቡ የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ መስፍን ውልደትና ዕድገታቸው አዲስ አበባ ሲሆን፣ በተለይ በሕክምና ዘርፍ የዳበረ ልምድ ባለቤት ናቸው፡፡
የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ ሆነው ሕወሓት እና የፌዴራል መንግሥት ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት በሽምግልና እንዲፈቱ ለማድረግ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡
ሰብሳቢው በሕክምና ዘርፍ ካጠኗቸው ትምህርቶች መካከል፣ ከሩሲያው ፓቭሎቭ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና የዶክተሬት ዲግሪ፣ ከስዊድኑ ኦማያ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮቴራፒ ፍልስፍና የፒኤች ዲ ዲግሪ እና ስፔሻላይዝድ ዲፕሎማ፣ በሳይኮሎጂካል ሜድስን እና ሳይካትሪ ከግሮኒንገን ዩኒቨርስቲ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

መስፍን ለ12 ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት፣ የዲፓርመንት ኃላፊ እና ሌክቸረር ሆነው ካገለገሉ በኋላ፣ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል። ለ11 ዓመት የፌዴራል ሆስፒታሎች አመራር ቦርድ አባል ሁነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ከሙያዊ አገልግሎት በተጨማሪ የማንነትና የአስተዳር ወሰን ኮሚሽን አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

በሥራ ልምዳቸው ደግሞ ለስድስት ዓመት በዓዲግራት፣ በደሴ እና በአማኑኤል ሆስፒታሎች ሜዲካል ኦፊሰርና ዳይሬክተር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይካትሪ ዲፓርትመንት ለስድስት ዓመታት ዲን፣ በአማኑኤል ሆስፒታል ሳይካትሪስት ለ10 ዓመት እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡

ሒሩት ገብረ ስላሴ
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ ለ14 ዓመት በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል፡፡ ሒሩት ለምዕራብ አፍሪካ እና ሳህል የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ምክትል ወኪል ሆነው አግልግለዋል፡፡ ለስድስት ዓመት የአፍሪካ የሴቶች የሠላምና ልማት ኮሚቴ ከፍተኛ ኦፊሰር፣ ለሦስት ዓመት በኦክስፋም አኅጉራዊ የሠላም ግንባታ እና የግጭት አመራር አማካሪ ሆነው አግልግለዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢዋ ከፈረንሳዩ ሰርቦን ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሩቅ ሲሆኑ፣ ለኹለት ዓመት በሕግ እና ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ተንታኝ ባለሙያ፣ ለኹለት ዓመት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የአፍሪካ ኅብረት የሕግ ጥናት ኦፊሰር፣ ለኹለት ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ሌክቸረር፣ ለስምንት ዓመት በግል የንግድ ድርጅት ከፍተኛ የሕግ አማካሪ፣ ለአራት ዓመት ዓለም አቀፍ የንግድ አማካሪ በመሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለዓለም ባንክ እንዲሁም በተለያዩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሠርተዋል፡፡

ተገኘወርቅ ጌጡ(ዶ/ር)
ተገኘወርቅ ጌጡ(ዶ/ር) የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ ትምህርታቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እስከ አሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ተከታትለዋል፡፡ ተገኘወርቅ ከአሜሪካው ኮሎምቢያ ዩኒቨርስሰቲ ፒኤችዲ በኢኮኖሚክስ እና ኹለት ማስተርስ ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡

ከ30 ዓመት በላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠሩት ተገኘወርቅ፣ በአሁኑ ጊዜ ከተባበሩት መንግሥታት ጡረታ ወጥተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልማት ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ፣ በአገራት የልማት ፕሮግራሞችን የመሩ፣ በርካታ ጽሑፎችን ያበረከቱ፣ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ፣ የልማት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙ እና ግጭቶችን ለመፍታት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያካበቱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እና በጃፓን መካከል የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር ላበረከቱት አስተዋጽዖ በኢትዮጵያ የጃፕን ኢምባሲ የክብር ኒሻን ሸልሟቸዋል፡፡

ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)
ዩናስ አዳዬ አዲስ የተቋቋመው አገራዊ ኮሚሽን አባል ሲሆኑ፣ በሙያቸው የሠላምና ደኅንነት ተመራማሪ እና መምህር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሠላምና ደኅንነት ጥናት ተቋምን በዳይሬክተርነት የመሩ ሲሆን፣ ትኩረታቸውን በሠላም ግንባታ፣ እንዲሁም በግጭት አፈታትና በድኅነት ላይ ያደረጉ ጥናቶችን አሳትመዋል፡፡

የሠላምና ደኅንነት ተመራማሪው ዮናስ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጥናት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጀምረው፣ ከብራንድ ፎርድ ዩኒቨርስቲ በሠላም ጥናት የፒኤችዲ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡

የኮሚሽኑ አባሉ ካሳተሟቸው የሠላምና ደኅንነት ጥናቶች መካከል በኢትዮጵያ እና በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ትኩረታቸውን ካደረጉ ጥናቶቻቸው መካከል Peacebuilding Through Peace Education in the Horn of Africa, The impact of local conflict on regional stability, Africa in the Global Security Governance: A Critical Analysis of Ethiopia’s Role in the UN Peacekeeping Operations, State fragility and conflict nexus: Contemporary security issues in the Horn of Africa ይገኙበታል፡፡

አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር)
አምባዩ የኮሚሽኑ አባል ሆነው ከተመረጡት ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ከዚሁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በሶሻል አንትሮፖሎጂ አግኝተዋል፡፡ በዚሁ በሶሻል አንትሮፖሎጂ ከጀርመኑ ማርቲን ሉተር ዊተርን በርግ ዩኒቨርስቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን(ፒኤችዲ) አግኝተዋል፡፡

የኮሚሽን አባሉ አምባዬ ለአምስት ዓመት በሠላምና ግጭት አማካሪነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በመምህርነትና በተመራማሪነት የሥራ ልምድ አካብተዋል፡፡ በግጭት አፈታት ላይ ልምድ ያካበቱት አምባዬ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረጉ የተለያዩ ጽሑፎችንና ጥናቶችን ከሌሎች አጋር ጸሐፊዎች ጋር እና በግላቸውም አሳትመዋል፡፡ ካሳተሟቸው ጽሑፎችና ጥናቶች መካከል Synergy of descent, history and tradition : Sidama ethnic identification , The revival and reconstruction of tradition and ethnic politics in Sidama , tradition as an arsenal of contest and negotiation ፣ Seeking out wise old men : six decades of Ethiopian studies at the Frobenius Institute revisited, Dynamic synergy of descent, history and tradition in the process of Sidama ethnic identification in Southern Ethiopia ይገኙበታል፡፡

መላኩ ወልደማሪያም
መላኩ ወልደማሪያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ የሦስት ዓመት የሕግ አማካሪነት፣ አራት ዓመት በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ዋና ጽሐፊነት፣ ለሰባት ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትርፍ ሰዓት መምህርነት፣ እንዲሁም አሁን ላይ በሕግ አማካሪነትና ጠበቃነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በልማት ማኅበራት አመራርነትና በሕዝባዊ ተቋማት አገልግሎት የሠጡ እና በሕግ አማካሪነት የሥራ ልምድ ያካበቱ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡

 

 

አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ(ዶ/ር)
አምባሳደር አይሮሪት የኮሚሽኑ አባል ሲሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም ከኔዘርላንዱ አሚስተርዳም ዩኒቨርስቲ በሕግ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከዚሁ ከአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን(ፒኤችዲ) በፍልስፍና አግኝተዋል፡፡

አምባሳደሯ በሥራ ዘመናቸው ከዳኝነት እስከ መምህርነት እና ሕግ አማካሪነት አግልግለዋል፡፡ ለ11 ዓመት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት፣ በአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት፣ እንዲሁም ለሦስት ዓመት በአምባሳደርነት አገልግለዋል፡፡

ብሌን ገብረመድህን
ብሌን የኮሚሽኑ አባል ሆነው ከተመረጡት ሰዎች መከከል አንዷ ሲሆኑ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በዓለም ዓቀፍ ሕግና ሰብዓዊ መብት ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከጀኔቯ አካዳሚ ኦፍ ሂዩማኒታሪያን ሎው ኤንድ ሂዩማን ራይትስ አግኘተዋል፡፡
በመምህርነት፣ በቀይ መስቀል ማኅበር ውስጥ በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሆነው የሠሩ እና በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን እያገለገሉ ያሉ ናቸው::

 

ዘገየ አስፋው
ዘገየ አስፋው የኮሚሽኑ አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከዊስኮንሰን ማዲስን ዩኒቨርስቲ በሕግ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከ1975-1976 የመሬት ይዞታ ሚኒስትር፣ ከ1977-1978 የግብርና ሚኒስትር፣ ከ1991-1992 የፍትሕ ሚኒስትር፣ ለኹለት ዓመት በምግብና ግብርና ድርጅት(ፋኦ) ከፍተኛ አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡

 

 

አምባሳደር መሐመድ ዲሪር
አምባሳደር መሐመድ በትምህርት ዝግጅታቸው ከኔዘርላንዱ አምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ሕግ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ ልምዳቸው በዚምባብዌና በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በሱማሌና ደቡብ ሱዳን የሠላም ሒደት የተሳተፉ፣ በሱዳን የሽግግር መንግሥት የሠላም ሒደት ላበረከቱት አሰትዋጽዖ ሽልማት ያገኙና በቀድሞው ባህልና ቱሪዝም በሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡

 

 

ሙሉጌታ አጎ
ሙሉጌታ አዲስ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በሕግ የመጀመሪያና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ በደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነትና ምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ እንዲሁም በዳኝነት ያገለገሉ፣ በከፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ዳኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ይህን ጽሑፍ ስናጠናቅር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከተለያዩ ድረ ገጾችና ኮሚሽነሮቹን በቅርበት ከሚያውቋቸው ሠዎች ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች ተጠቅመናል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here