ሕወሓት ዳግም በተቆጣጠራቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች ከአንድ ግለሰብ ከአምስት እስከ 10 ሺሕ ብር በማስገደድ እየሰበሰበ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ከነዋሪዎቹ አስገድደው የሚሰበስቡት ብር ብቻ ሳይሆን አንድ ኩንታል ጤፍና ማሽላ ጭምር ነው ተብሏል፡፡
ሕወሓት ወደ ትግራይ ከተመለሰ በኋላ በአዋሳኝ አካባቢዎች ዳግም በጀመረው ጥቃት ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ለአብነትም ከራያ አላማጣ ወደ ቆቦ ከተማ 15 ሺሕ ሰዎች፣ ከዋግኽምራ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ወደ ፅፅቃ እና ሰቆጣ ከተማ ከ30 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
የሕወሓትን ጥቃት ተከትሎ የአላማጣ የተለያዩ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁን ድረስ ወደ ቆቦ ከተማ እየተፈናቀሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሠምታለች፡፡ የሕውሓት ቡድን ከየካቲት ስድስት 2014 ጀምሮ ከአንድ ሰው እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ብር እና አንድ ኩንታል እህል አስገድዶ የመሠብሰብ መመሪያ አውጥቶ ዘረፋ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከአዲስ ማለዳ የመረጃ ምንጮች መካከል ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉና ሰሞኑን ከአላማጣ ወደ ቆቦ ከተማ የገቡ አንድ ግለሰብ፣ ታጣቂ ቡድኑ በአላማጣ ዙሪያ በሚገኙ ቀበሌዎች በመዘዋወር ከአንድ ሠው እስከ 10 ሺሕ የሚደርስ ብርና መቶ ጣሳ እህል በግዴታ እየሠበሰበ ነው ብለዋል፡፡
ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው በዋጃ፣ ጥሙጋ፣ ሰሌን ውኃ፣ አቦ ኩርማ እና በሌሎችም ቦታዎች ነው ያሉት የአዲስ ማለዳ የመረጃ ምንጮች፣ እያንዳንዱ ግለሰብ “መቶ ጣሳ ማሽላ ወይም ጤፍ፣ ከአምስት ሺሕ እስከ ሰባት ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ከብቶች ጭምር በግዴታ አምጣ እየተባለ ነው” ሲሉ የተመለከቱትን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮች የሠማችው፣ ምንም እንኳ ታጣቂ ቡድኑ አካባቢዎቹን በተቆጣጠረባቸው ጊዜያት የንብረት ዘረፋ ሲያደርግ ቢቆይም፣ ከየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ እያንዳንዱን ሠው ብር አዋጣ በማለት በቀበሌ እስከ 70 ሺሕ ብር ድረስ እየሰበሰበ መሆኑን ነው፡፡
ነዋሪዎቹ አክለውም፣ ልዩልዩ መድኃኒቶች በታጣቂ ቡድኑ እጅ በመሆናቸው ቤታቸውን ለቀው ወደ ቆቦ ከተማ እስኪያልፉ ድረስ የስኳር እና የደም ግፊት ታማሚዎች የመድኃኒት አቅርቦት ዕጥረት እንደገጠማቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም፣ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በቆቦ ከተማ የሚገኙ ግለሰብ “እኔ የስኳር ታማሚ ነኝ፡፡ ወደዚህ እስከምመጣ ድረስ መድኃኒት ስላልነበረኝ ሕመሙ ተባብሶብኛል” ሲሉ ነው የደረሰባቸውን ያብራሩት፡፡
አክለውም፣ መድኃኒት ዕጥረት መከሠቱን ተከትሎ ሠላም ወዳለበት አካባቢ እስከሚመጣ ድረስ ሕመሙ ተባብሶበት አንድ የቲቢ ሕመምተኛ የካቲት 16/2014 ሕይወቱ አልፏል ብለዋል፡፡
ከአላማጣ ወደ ቆቦ ስንመጣ የሕወሓት ታጣቂ ከመንገድ ጠብቆ ይዘርፈናል የሚሉት ግለሰቡ፣ ማለፍ የቻሉት በጫካ ተጉዘው መሆኑን ጠቁመዋል።
አያይዘውም መውጣት ያልቻሉና የሚከፍሉት ብር የሌላቸው ሠዎች ታጣቂ ቡድኑ 10 ሺሕ ብር ሠጥቷቸው ከትንሽ ጊዜ በኋላ 13 ሺሕ ብር አድርገው ወለድ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014


