ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው እንጀራ የመሸጫ ዋጋው በየጊዜው ከፍና ዝቅ ማለቱን ተከትሎ አሳንሶ መሸጥ የማይቻልበት ዝቅተኛ የዋጋ ተመን ሊወሰን መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገር እንጀራን የሚልኩ ሠዎች በፈለጉት ዋጋ እየላኩ በመሆኑ የመሸጫ ዋጋው ከፍ ወይም ዝቅ ስለሚል የመላኪያ ቋሚ ዋጋ ሊተመንለት መሆኑን የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አስራት አያሌው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ከውሳኔው በኋላ እንጀራ ወደ ውጭ አገር የሚላክበት ዝቅተኛ ዋጋ እንደሚታወቅና ከሚወሠነው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ በታች መሸጥ እንደማይቻል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ላኪዎቹ በፈለጉት መልኩ ይልኩታል እንጂ ቋሚ ዋጋ አልነበረውም የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በዝቅተኛ ዋጋ ሲላክ የዶላር ገቢው ያነሰ ስለሚሆን ቋሚ ተመን ሲወጣለት ችግሩን በመቅረፍ ገቢን ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም፣ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት አንድ እንጀራ ወደ ውጭ የሚላክበት ዋጋ ከ0.5 እስከ አንድ ዶላር ነው ብለዋል፡፡
የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የግብርና ምርቶች ተማራማሪው መላኩ አገኘ በበኩላቸው፣ ወደ ውጭ በሚላኩና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ “አንደር ኢንቮይስ እና ኦቨር ኢንቮይስ” አላቸው ያሉ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ወደ ውጭ ሲልኩ ዋጋውን ዝቅ በማድረግ (አንደር ኢንቮይስ)፣ ሌሎቹ ደግሞ የሚያስገቡበትን ዋጋ ከፍ (ኦቨር ኢንቮይስ) ስለሚያደርጉት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ዋጋውን ሚዛናዊ የማድረግ ዕቅድ መያዙን አብራርተዋል፡፡
ተመራማሪው በተያያዘም፣ የአንዱ ዋጋ ከፍ የሌላኛው ዝቅ የሚልበት ምክንያት ምን እንደሆነ ነቅሶ በማውጣት የመላኪያ ዋጋውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማስተካከል ዝቅተኛና ከፍተኛ የሚባልበትን ዋጋ አሳውቆ ወደ ውጭ ገበያ እንዲልኩ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
አብዛኛዎቹ እንጀራ ላኪዎች ዳያስፖራ የነበሩ ሰዎች እንደሆኑ የጠቆሙት መላኩ፣ በነበሩበት ውጭ አገር ያለ ቤተሰባቸው ወይም በቅርበት የሚያውቋቸው የገበያ ማዕከላት ያሏቸው ሠዎች ስለሚኖሩ አንዳንዶቹ በትክክለኛው ዋጋ የሚልኩበት ኹኔታ እንዳለም አመላክተዋል፡፡ ተመራማሪው አያይዘውም፣ ምንም እንኳ ወደ ውጭ የሚወጡ ቁሳቁሶች በከፍተኛ ዋጋ መላካቸው ጥሩ ገቢ ቢያስገኝም፣ በዝቅተኛ ዋጋ የሚላኩትና በከፍተኛ ወጭ የሚገቡት ግን ሌላ ጥያቄን ማስከተላቸው እንደማይቀር ነው የተናገሩት፡፡
አክለውም፣ አንዳንዶቹ ላኪዎች ደግሞ ዶላሩ የሚመጡት እንጀራው ከተላከ በኋላ ስለሆነ ዶላሩን ለማስቀረት የሚያልሙበት ዕሳቤ አለ የሚል ጥርጣሬ እንዳለ ገልጸው፣ ጉዳዩን የመቆጣጠር ኃላፊነቱ ብሔራዊ ባንክን ስለሚመለከት በጉዳዩ ላይ በጋራ ውይይት እንደሚያደርጉበትም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ደረቅና እርጥብ እንጀራ ሲሆን፣ አንድ እንጀራ ከ0.5 እስከ አንድ ዶላር ስለሚሸጥ ገቢው እምብዛም የከፋ ባይሆንም፣ ለመላክ የሚከፈለው ዋጋ ግን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው ተብሏል፡፡ በካርጎ ለመላክ የሚወጣው ገንዘብ ከመሸጫ ዋጋው 50 በመቶ በላይ መሆኑንም መላኩ ተናግረዋል፡፡
እንደ መላኩ ገለጻ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እንጀራ የምትልክባቸው የውጭ አገራት እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ጣሊያን፣ ዱባይ፣ እንዱሁም ሳዑዲ ዐረቢያ ናቸው፡፡ እንጀራ በብዛት የሚላከው ወደ አውሮፓ አገሮች ሲሆን፣ ወደ ደቡብ አፍሪካም በተወሠነ መልኩ እንደሚላክ መላኩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
መላኩ በመጨረሻም፣ ዕቅዱ ተግባራዊ ሲደረግ እንጀራ ወደ ውጭ ተልኮ “ከዚህ በታች ከተሸጠ ዝቅተኛ ነው ከዚህ በላይ ከተገዛ ከፍተኛ ነው” የሚል ውሳኔ በማስቀመጥ መሸጥ የማይቻልበትን ዝቅተኛ ዋጋ ለማሳወቅ ታቅዷል ነው ያሉት፡፡ አክለውም፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንጀራ ከመላክ እንደምታገኝ ጠቁመዋል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014



