በሕክምና መገልገያዎች፣ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የጤና ክብካቤ አገልግሎት ቴክኖሎጂ እና ግብዓቶች ላይ ትኩረት የሚያደርገው 6ተኛው ኢትዮ-ኸልዝ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባኤ ባሳለፍነው ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2014 በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል።
ዓውደ ርዕይ እና ጉባኤው የጤናውን ዘርፍ ልማት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ በዘርፉ ተዋናዮች መካከል የንግድ ልውውጥን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና የዕውቀት ሽግግርን በማምጣት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
የዘንድሮው ኹነት ለመጀምሪያ ጊዜ የሕንድና ባንግላዲሽ ብሔራዊ ተሳትፎ የታየበት ሲሆን፣ ጆርዳን፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ እና አሜሪካ ላይ መሠረታቸውን ያደረጉ ስምንት ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፤ ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎችም እንደጎበኙት ተገልጿል፡፡
ከዓውደ ርዕዩ በተጨማሪም በ6ኛው ኢትዮ ኸልዝ የጤና ጉባኤ በአምስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም፣ የህክምና አገልግሎት ልኅቀት፣ የታካሚ ደኅንነት፣ የጨረር እና የላብራቶሪ ምርመራዎች፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ እና መድኃኒት ላይ ተከታታይ የሕክምና ትምህርቶች በዘጠኝ የሕክምና ሙያ ማኅበራት መሠጠቱም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይ እና ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ፤ የኢትዮጵያና ሕንድ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሠነድ ተፈራርመዋል።
ዓለም ዓቀፍ ዓውደ ርዕይ እና ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ቀጥሎ፣ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 2014 እንደሚያበቃም አዲስ ማለዳ ከአዘጋጆቹ ለማወቅ ችላለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014


