በዩክሬን ለሚገኙና ከዩክሬን ወደ ፖላንድና ሌሎች አጎራባች አገሮች በመሔድ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማግኘት የሚችሉበት ድረ-ገጽ ይፋ ማድረጉን በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
በዚህም ኤምባሲው፣ በሩስያ እና ዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምከንያት ዜጎች ወደ አጎራባች አገራት ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ከየአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቶች ጋር በመተባበር በተቻለ መጠን ያለችግር ማቋረጥ እንዲችሉ ሲሠራ መቆየቱን ነው የገለጸው፡፡
ኤምባሲው፣ ከዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በጉዳዩ ላይ በመነጋገር በተዘጋጀው አጭር ድረ-ገጽ https://cutt.ly/qAi9vBJ በመግባት ዜጎች መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ ነው ያለው፡፡
ዜጎች ድረ-ገጹን ተጠቅመው የት እንደሚገኙ እና ወደ የትኛው ድንበር ለማቋረጥ እየሄዱ እንደሆነ በማሳወቅ፣ የዩከሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የኮንሱላር ጉዳዮች ክፍል ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልግ ባሳወቀው መሠረት ድረ- ገጹን በመጠቀም ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ኤምባሲው አስታውቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014


