‹የሴቶች ቀን› መቼ ነው?

0
1033

‹‹ብነግርሽ ለውጥ ይመጣል?›› አለችኝ፤ መቅረጸ ድምጹን አስተካክዬ ድምጿ ሊሰማበት በሚችልበት ርቀት ላስቀምጠው ስሰናዳ። በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች ከደረሰባት ችግርና ካሳለፈችው በመነሳት ነበር እንዳናግራት የጠቆሙኝ። ያሳለፈችው ነገር እጅግ የሚያሳዝን ነው። ታሪኳን መግቢያ አድርጌ የማዘጋጀው ጽሑፍ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ሲነበብ፣ አንባቢ ሰውነቱን አስታውሶ እንዲነቃና የሚሆነውን ይረዳል ብዬ አመንኩ። የደረሰባትንና እውነቷንም ሰዎች ሲሰሙላት እርሷም ትተነፍሳለች፣ ድጋፍ የሚያደርግም ይገኝ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነትም ነበረኝ።

በተቀጣጠርንበት እለትና ቦታ ተገናኝተን ትንሿን መቅረጸ ድምጽ አውጥቼ ፊቷ ሳስቀምጥ ግን ሐሳቧን ቀይራ ጠበቀችኝ። ጥያቄም አብራ አነሳችብኝ፤ ‹‹ብነግርሽ ለውጥ ይመጣል?››

መገናኛ ብዙኀን በማኅበረሰብና በሁሉም የአገር ጉዳይ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለውጥ እንዲመጣ ይሠራሉ። ሰዎች መረጃ ላይ መሠረት አድርገው እንዲወስኑና እንዲንቀሳቀሱ መረጃን ያቀርባሉ። ይህን በምን ያህል እየሠሩ ወይም እየሠራን እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ ጥረቶች እንዳሉ እሙን ነው። ግን አንዲት በጦርነት መካከል ብዙ መከራን ያሳለፈች፣ በአካልም በሥነልቦናም ጉዳት ላይ ያለች፣ የተረሳች የመሰላትና ልጆቿን ይዛ መጠጊያ ያጣች ሴት ‹ብናገር ለውጥ ይመጣል ወይ?› ብላ ስትጠይቅ ምን ተብሎ ይመለሳል?

ቃለመጠይቁ ቀረ። የተወሰነ ለማግባባትና ድምጿን ሳልቀዳ እንዲሁም ማንነቷን ሳልገልጽ ታሪኳን ብቻ እንድናገር ጠየቅኳት። በጦርነቱ የተነሳ ከትውልድ አካባቢዋ መፈናቀሏን፣ ሴት መሆኗን የጠላችበትን ጊዜ እንዳሳለፈችና አሁን ብቻዋን ብትሆን ኖሮ በሕይወት መኖርን እንደማትመኝ ነገረችኝ። ‹‹በሕይወት ያለሁት ለልጆቼ መኖር እንዳለብኝ ስለማውቅ ብቻ ነው። ሴት ልጆቼ እንደ እኔ እንዳይጎዱብኝ መጠበቅ ስላለብኝ ነው ቆሜ የምታይኝ።›› አለችኝ። ከዚህ በላይ ምንም የእርሷ የሆነውንና መደበኛ ባልሆነ መንገድ በጭውውት የነገረችኝን በጋዜጣ እንዳልጽፈው አሳሰበችኝ።

‹ቢነገር ለውጥ ይመጣል?›
የሴቶች ጉዳይ እንዲህ የሴቶች ቀን ሲቃረብ የበለጠ አጀንዳ የሚሆን የሚመስለው ሰው ጥቂት አይደለም። በእርግጥ አንዳንዴ እንደዛ እንዲመስል የሚያደርጉ ኹነቶችን እናስተውላለን። ነገር ግን ያለመታከት የሴቶችን ጉዳይ እያነሱ በመገናኛ ብዙኀን በኩል አቤት የሚሉ አሉ። ሰሚው ግን የዛን ያህል አይደለም። መቼ ይሰማል? የሴቶች ቀን ሲደርስም አይደለም። ይልቁንም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባት፣ በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ መከራን የተቀበለች ወይም እንዲያ ያለ ክስተት ሲፈጠር።

አንድ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኀን የቀረበውን የሕጻን ኢክራም ያሲንን ታሪክ እናንሳ። አስገድዶ መድፈርና የተለያየ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባት ትንሽ ልጅ ናት። አደባባይ ወጥታ የሆነባትን ተናግራ ‹እኔ ሳልሆን ድርጊቱን የፈጸሙት ናቸው ማፈር ያለባቸው!› አለች። ብዙዎች ሲያደንቋትና ሲያመሰግኗት ነበር።

ነገር ግን ምን ለውጥ አመጣ ብሎ ለጠየቀ ኢክራምና ቤተሰቦቿ ይኖሩበት በነበረው አካባቢ ሰዉ ሊያኖራቸው አልቻለም። የደረሰባትን ጥቃት እያስታወሱ መልሰው መላልሰው ይጠይቋታል። ስለዚህ ትውልድ አካባቢዋን ለቅቃ አዲስ አበባ ለመክተም ተገደደች። ይህ የሆነው ማኅበረሰብ ጋር ባለው የግንዛቤ ክፍተት የተነሳ ነው። እንዲህ ያለው ክስተት በሴቶች ላይ በተለይም ጦርነት መካከል የተለያየ ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው፣ ያንን አልፈው ለተረፉት ድርብ ሸክም ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች እና ጦርነት
አርባ ዓመታትን የወሰደና ኸለቱን የዓለም ጦርነቶች ያጣቀሰ አንድ ጥናት እናውሳ። ይህ <Understanding twentieth-century wars through women and gender: forty years of Historiography> ‹የ20ኛ መቶ ክፈለ ዘመን ጦርነቶችን በሴቶችና ሥርዓተ ጾታ አንጻር መረዳት› የሚል ርዕስ ያለው ጥናቱ፣ በፈረንሳዊቷ ፍራንቼስ ቴባውድ የተዘጋጀ ነው። ፍራንቼስ በዘመናዊ ታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰር እንዲሁም በስርዓተ ጾታ ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን በአቪግኖን እንዲሁም በጄኔቭ ዩኒቨርስቲ ታገለግላለች።

አጥኚዋ እንደምትገልጸው፣ ጦርነትን በሴቶች ዐይን ማየት ሴቶች በጦርነቱ ካላቸው ተሳትፎ አንጻር በማየት ወይም በመገምገም ይጀምራል ትላለች። ይህም በቀጥታ ወታደር ሆነው ከሚሰለፉት በተጓዳኝ የጤና ባለሞያ ወይም ነርስ ሆነው ከሚያገለግሉት ጀምሮ በወንዶች ፋንታ ሥራዎችን ተክተው እየሠሩ ያሉ፣ ልጆቻቸውን ለብቻቸው እንዲያሳድጉ ግድ ያላቸውና የመሳሰሉትን የሚመለከት ነው።

ከዛም በተጨማሪ በጦርነት ወቅት ሴቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ መቃኘትንም ትጠቅሳለች። በጦርነት ግንባር እንዲሁም በቤት ግንባር ያላቸው የተሳትፎ መጠን፣ ከባህል አንጻር የየእለት ሕይወታቸው የያዘው መልክ፣ የተሸከሟቸው እንደ ብቸኝነት፣ ድህነት፣ ከባድና ድርብርብ የሥራ ጫናና ኃላፊነት ያሉ ጫናዎችና የመሳሰሉት ሁሉ ሴቶችና ጦርነት ሲነሳ አብረው መነሳት እንዳለባቸው ትዘረዝራለች። ይህም በድምሩ በአንድ ጎን ሴቶች በጦርነት መካከል የሚኖራቸው ድርሻ ሲሆን ሌላው በጦርነቱ ሳቢያ የሚያርፍባቸው ጫና ነው።
ይህ በጥናቱ የተጠቀሰው ሁሉ በኢትዮጵያ ባለፉት 14 በላይ ወራት በቆየውና አሁንም በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥም ይስተዋላል። ሴቶች በጦርነት ሳቢያ ከዛም ባለፈ የብዙ ጥቃት ሰለባ ሆነው ተገኝተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ‹‹ግጭት ባለባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች ያሉት ሴቶች ሊታሰብ የማይቻል አሰቃቂ አደጋ ደርሶባቸዋል። የደረሰውን የመደፈር ታሪክ ሰምቼም እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም።›› አሉ። እኚህ ሴት በኢትዮጵያ ለአምስት ቀናት ባደረጉት ቆይታ ትግራይ፣ አፋር እንዲሁም ሶማሌ ክልሎች ጉብኝት አድርገዋል። ከጉብኝታቸው መልስ ነው ያዩትና የሰሙት ይልቁንም በሴቶች ላይ የደረሰው ጥቃት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ያስረዱት።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ሴቶች የደረሰባቸው ጉዳት ለማሰብ የሚከብድ ነው እንደሆነ መሰከሩ። በልጆቻቸው ፊት የተደፈሩ፣ የደረሰባቸውን ጥቃት ይህ ነው ብለው መናገር የከበዳቸው እንዲሁም የደረሰባቸውን የማያስታውሱ ጭምር እንደታዘቡም ነው በሐዘኔታ የገለጹት።
ይህን ከዕይታ በመነሳት የተናገሩትን እውነት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የመሳሰሉት ተቋማት ደግሞ በተለያየ ጊዜ ባቀረቧቸው ዘገባዎች ላይ የጠቀሱት ነው። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ በቀጥታ የጥቃት ሰለባ ከነበሩ እንዲሁም ከዐይን እማኞች የተገኙ መረጃዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም ቃላቸውን ከሰጡ የጥቃት ሰለባ ከሆኑ ሴቶች መካከል ግማሾቹ በቡድን አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው ናቸው ተብሏል።

ከጦርነት አካባቢ ሸሽተው በመጠለያ የሚገኙ ሴቶችም ከጾታዊ ጥቃት አላመለጡም። በእድሜ የገፉ እናቶች፣ አካል ጉዳት ያለባቸው ሴቶችም እንደዛው። የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ያለው አምነስቲም፣ በአንድ ከተማ ብቻ በ9 ቀናት ውስጥ 71 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር መድረሱን አስታውቆ ነበር።

ከዚህ የሚብሰውና የሚከፋው ደግሞ በጦርነቱ የደረሰባቸውን ጥቃት አልፈው የሚኖሩት ላይ በማኀበረሰብና በአካባቢ ሰው የሚደርስባቸው የማግለልና የማሸማቀቅ ድርጊት ነው። ይህ በሴቶች ላይ ተደራራቢ ጫና፣ ከባድ ሸክም ይጥላል። እንደ ማኅበረሰብ ዜጎች እንዲነቁ ማድረግ የሚያሻውም ስለዚህ ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን ከላይ በተጠቀሰው ጥናት መሠረት፣ ጦርነቱን በሴቶች ዐይን ስንቃኝ ሴቶች በጦርነቱ ያላቸውን ተሳትፎ ማንሳት ተገቢ ነው። ወታደር ሆነው የማረኩ፣ ስንቅ በማቀበል የሚታገሉ፣ ጦር ሜዳ የዘመቱ፣ የትዳር አጋሮቻቸውን ክፍተት ሸፍነው ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነትን የተረከቡና ጫናውን የተሸከሙ ብዙ ናቸው።

ምን ተደረገ፣ ምንስ ተስፋ አለ?
መሠረት አሊ፤ በኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ ናቸው። 29 አባል ማኅበራት ያሉት ይህ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ ለጊዜው ከትግራይ ክልል በቀር በሁሉም ክልሎች የሴቶች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ ማህበራትና ባለድርሻዎች ጋር ይገናኛል፤ ይመክራል፤ ይወያያል፣ መረጃ ይለዋወጣል።

እንደ መሠረት ገለጻ አስቀድሞ ይህ ጦርነት እንዳይመጣ ቅንጅቱ የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል። የጦርነቱ ላይ ተሳታፊዎች ለሰላም እንዲተጉ ማሳሰብና ይህንንም በመገናኛ ብዙኀን በኩል ብዙኀን እንዲሰሙ ለማድረግ ሞክሯል። የሰላም ጥሪዎች ሁሉ ጆሮ ሳያገኙ ቀርተው፣ ጦርነቱ ተከስቶ ውድመቶች ከተፈጠሩ በኋላ ደግሞ ቅንጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የቁሳቁስ፣ የምግብ እንዲሁም የማብሰያ ዕቃዎች ድጋፎችን አድርሷል።

ታድያ የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን የሥነልቦና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውም እልፍ ናቸው። መሠረት ይህን በሚመለከት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጠር ያለ ቆይታ ሲናገሩ ‹‹የተፈጠረው የሥነልቦና ቀውስ በእኛ አቅም ሊፈታ የሚችል አይደለም።›› ብለዋል። ከዛም በላይ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱ ሲሆን፣ ቅንጅቱ በደቡብ ወሎ እንዲሁም በአፋር የተወሰኑ ክፍሎች ቅኝት ማድረጉን ተናግረዋል። ያንንም ተከትሎ በተለይ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የማኅበራዊ ጉዳይ ባለሞያዎችን በድኅረ አደጋ ሰቀቀን (Trauma) ዙሪያ ሥልጠናዎችን በመስጠት እገዛ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማኅበረሰብ ዐቀፍ የሆነ፣ በውይይትና እርስ በእርስ በመመካከር፣ በመነጋገር የድኅረ አደጋ ሰቀቀንን መቀነስና ማከም የሚቻልባቸው መንገዶች ለባለሞያዎቹ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ናቸው። መሠረት ሁኔታው እንዲያም ሆኖ ከባድ መሆኑን ሲያስረዱ፣ ለአሠልጣኝነት የሚሠለጥኑ የማኅበራዊ ጉዳይ ባለሞያዎችም ሳይቀር በሕመምና ሰቀቀን ውስጥ መሆናቸውን ያነሳሉ። እናም ጉዳዩ ትኩረትም ቅድሚያም ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህን ለማከናወን ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑም ነበር። መረጃ ማግኘት ፈትኗቸዋል፤ እየፈተናቸው ነው። በቂና ሁለገብ የሥነልቦና ድጋፍ ማግኘትም ቀላል አልሆነላቸውም። ከምንም በላይ ግን በዚህ ውስጥ ተቀናጅቶ የመሥራትን ጥቅምና ዋጋ መመልከታቸውን አስረድተዋል። በችግር ላይ ላሉ ሴቶች በሁሉም መልኩ ተደራሽ ለመሆንና ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት እርስ በእርስ ተዋውቆ ማን ምን ይሠራል የሚለውን መለየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። አሁንም ያንን አውድ መፍጠሩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ግን ለሴቶችም ለአገርም ሰላም እንዲመጣ ቀጣዩ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ ተስፋ መጣሉን መሠረት ጠቅሰዋል። ‹‹ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ላይ ሴቶች ቦታ እንዲሰጣቸው፣ ጆሮ እንዲያገኙ ደጋግመን እየጠየቅን ነው። እሱ ምላሽ ካገኘ፣ ግጭት የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ላይ መድረኩ ሲጀመር የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ከወዲሁ የማንቃት ሥራዎችን እየሠራን ነው።›› ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ የመሠረትን የግል ዕይታ ጠይቃለች። ይልቁንም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ ከተደረገው ጥረት አንጻር ሲታይ የተሳተፉ ሴቶች ጥቂት መሆናቸውን ተከትሎ፣ ‹‹ለውጥ ለማምጣት የምትሠሩትን ሥራ እርስዎ ያውቃሉ። ግን በአደባባይ ፍሬው አልታይ ሲል፣ አንዳንዴ ድካም ብቻ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ያውቃል ወይ?›› ነበር ጥያቄው።

‹‹እንደ ቅንጅት አንደክምም፣ ተስፋ አንቆርጥም። አሁንም [ተስፋ የጣልንበት] የአገራዊ ምክክር መድረክ ኮሚሽን አባላት በምን መስፈርት እንደተመረጡ ባናውቅም፣ ሴቶች በምክክሩ በሚኖራቸው ተሳትፎ በንቃት እንዲሳተፉ በተለያየ መንገድ እያዘጋጀናቸው ነው። እንደ ግለሰብ ግን ይደክማል። ቢሆንም ተስፋ አልቆርጥም።›› ሲሉ መልሰዋል።

አዲስ ማለዳ አንባቢዋን ትጠይቃለች። በየጓዳው፣ በየአካባቢው በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ብዙ ነው። ጦርነቱ ደግሞ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ፣ ተደርቦ ፈተናውን አክብዶታል። እና እውን የሴቶች ቀን መቼ ነው? የካቲት 29 ወይም ማርች 8? የሴቶች ቀን የሚሆነው ሴቶች ቀን የወጣላቸው፣ ከተደራራቢ ችግር የተላቀቁ ጊዜ አይደለ?


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here