”የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ በቤት ውስጥ መታሰር በየትኛውም የህግ አግባብ ተቀባይነት የሌለው ነው”:- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

0
1039

አርብ የካቲት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ በቤት ውስጥ መታሰር በየትኛውም የህግ አግባብ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለፀ።

ቦርዱ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በላከው ደብዳቤ፤ በዳውድ ኢብሳ ግቢ የተመደበውን ጥበቃ በማንሳት የሊቀመንበሩን የመንቀሳቀስ መብት አስከብሮ በአስቸኳይ ለቦርዱ እንዲገልጽ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23 ቀን 2014 እና ህዳር 30 ቀን 2014 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ አመራሮቻቸው እና አባሎቻቸው እየታሰሩ መሆኑን መግለፃቸውን አስታውቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቤቱታዎች የሚያጣሩ ቡድኖች በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ እና በኦሮሚያ ከልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ አስተዳደር ማቋቋሙን ገልጿል፡፡

የአጣሪ ቡድኖቹም አባላት ከገዢው ፓርቲ በከፍተኛ አመራር ላይ የሚገኝ አንድ ሰው፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለት ባለሙያዎች፣ አቤቱታውን ካቀረቡት ፓርቲዎች አንድ አንድ ሰው የተወከሉ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

በዚሁ የማጣራት ሂደት ውስጥ ለኦሮሚያ ክልል አጣሪ ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 24 ቀን 2013 ጀምሮ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገው የቁም እስረኛ እንደሆኑ አቤቱታ ማቅረቡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ይህንኑ አቤቱታ ለማጣራት የቡድኑ ሁለት አባላት የካቲት 21 ቀን 2014 ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ በዳውድ ኢብሳ ቤት በመሄድ ሁኔታውን እንዲያጣሩ መደረጉንም ተናግሯል፡፡

አጣሪዎቹ በሪፖርታቸው እንዳቀረቡት የቡድኑም አባላት የሊቀመንበሩ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ አንኳኩተው የከፈቱላቸው ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሠራተኞች መሆናቸውን፤ ማንም ሰው መግባት እንደማይፈቀድለት ገልጸው ገብተው ለማየት መጀመሪያ ፈቃድ መጠየቅ ያለበት በመሆኑ ከየት እንደመጡ እና ለምን እንደመጡ መጠየቃቸውን፥ በመጨረሻም እንዲጎበኗቸው እንደተፈቀደላቸው ተገልጿል።

የቡድኑም አባላት ከዳውድ ኢብሣ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የያዙት ቦርሣ መፈተሹን፣ አንዲሁም ስልካቸውን ይዘው መግባት እንደማይችሉ እንደተገለፀላቸው በመጨረሻም ይህንኑ በመፈጸም ከሊቀመንበሩ ጋር እንደተገናኙ ለቦርዱ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

የአጣሪው ቡድንም አባላት ከዳውድ ኢብሳ ጋር ካደረጉት ውይይት የተረዱት ከመጋቢት 24 ቀን 2013 ጀምሮ ከቤት እንዳይወጡ የታጠቁ ሰዎች ግቢያቸው ውስጥ ተመድበው የከለከሏቸው መሆኑን ነው፡፡ ቦርዱም ዳውድ ኢብሳ የቤት ውስጥ እስረኛ ሆነው የመንቀሳቀስ መብታቸው እንደተገደበ መገንዘቡን ገልጿል፡፡

በመሆኑም ቦርዱ እኚህን የፓርቲ አመራር በየትኛውም የህግ አግባብ ተቀባይነት በሌለው ሁኔታ የሚገኙበት የቤት ውስጥ እስር በአፋጣኝ መቆም ያለበት መሆኑን እያስገነዘበ ተቋማቸሁ ዳውድ ኢብሳ ግቢ የተመደበውን ጥበቃ በማንሳት የሊቀመንበሩን የመንቀሳቀስ መብት አስከብሮ በአስቸኳይ ለቦርዱ እንዲገልጽ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን ጠይቋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here