ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ባሳለፍነው ቅዳሜ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 33ቱ የባልደራስ አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ ኹለቱ ማለትም ቢኒያም ታደሰ እና ሳሙኤል ዲሚትሪ ለ14 ቀን ሲቀጠሩ፣ ቀሪዎቹ 31ዱ ደግሞ ለሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 መቀጠራቸውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ።
ተከሳሾቹ ለኹለት ቡድን ተከፍለው፣ 31ዱ እስረኞች ከልደታ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ፣ ለሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ተቀጥረዋል፡፡
ጊዮርጊስ ወዳለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተወሰዱት ቢኒያም ታደሰ እና ሳሙኤል ዲሚትሪ ደግሞ ጊዮርጊስ የሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበው 14 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ባልደራስ የፍርድ ሂደቱን አስመልክቶ ከደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ፤ “31ዱን እስረኞች ፍርድ ቤት ይዞ የቀረበው መርማሪ ፖሊስ፣ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ፣ “ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በአድዋ እና ካራማራ ክብረ በዓላት ብጥብጥ እና ሁከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው፡፡ ይህንን ለማጣራት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይ የጋዜጠኞቹ ስልክ መመርመር አለበት” ማለቱን ገልጿል፡፡
ለመርማሪው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት የፓርቲው አባላት ወግደረስ ጤናው፣ ጌጥዬ ያለው እና ስንታየሁ ለማ ሲሆኑ፤ ወግደረስ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው ንግግር፣ “በወቅቱ ስናደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር በቦታው የነበሩት ፖሊሶች ታዝበዋል፡፡ በምንም መስፈርት በሁከትና ብጥብጥ ልንጠረጠር አንችልም ” ማለቱ ተገልጿል፡፡
ጌጥዬ ያለው በበኩሉ፣ “ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲሞክሩ የነበሩት፣ እኛ ሳንሆን ሲገፈታትሩን የነበሩት የፀጥታ አካላት ናቸው፡፡ለዚህ የሰጠነው ምንም አይነት የሃይል ምላሽ አልነበረም” ብሏል፡፡ ስንታየሁ ለማ ደግሞ፣ “የፀጥታ ሃይሎች ሲገፈታትሩን፣ መሪያችን በሰጠን ትዕዛዝ መሠረት በሰላማዊ ትግል መሬት ቁጭ ከማለት ባሻገር ምንም የፈፀምነው ድርጊት የለም፡፡ ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ተገቢ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታችንን ያክብርልን” በማለት መጠየቁን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ፖሊስ የጋዜጠኞች ስልክ ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግበት የተናገረውን አስመልክተው፣ ጌጥዬ እና ወግደረስ በሰጡት ምላሽ፣ “ፖሊስ ስልካችንን በተለየ ሁኔታ የሚመረምርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስልካችን በተለየ መልኩ ከተመረመረ፣ በሕገ መንግሥቱ 29 መሠረት ሃሳባችንን በነፃነት እንድንገልጽ የተቀመጠው መብት የሚጥስ ተግባር ነው የሚሆነው ” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ከ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተወሰዱት ቢኒያም እና ሳሙኤልን በተመለከተ፣ ከተለያዩ ሰፈሮች ታድነው ከተያዙ 13 የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ተደምረው፣ “ደረጄ ይበይን” በሚል የክስ መዝገብ ችሎት ፊት መቅረባቸውን ባልደራስ ገልጿል፡፡
ደረጀ ይበይን ቅዳሜ ዕለት ከተያዙት የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እሱና 14ቱ ተጠርጣሪዎች፣ “በአድዋ ክብረ በዓል ዕለት ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል፣ ፈጥረዋል ” በመባል የምርመራ መዝገብ ተከፍቶባቸዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው አቤቱታ፣ “ያልተያዙ ግብረ አብሮች አሉ፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል አለብኝ፡፡ ስለዚህም፣ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ” ማለቱን ባልደራስ ገልጿል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1ኛ ተጠርጣሪ ደረጀ ይበይን ባቀረበው አቤቱታ፣ “የታሰርነው በዓሉን በማክበራችን ብቻ ነው እንጂ፣ ምንም የተለየ ነገር አልፈፀምንም ” ብሏል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ተመሳሳይ ይዘት ያለው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ የቤተሰብ ሃላፊ ስለሆንን ወይ በነፃ ወይ በዋስትና ልንለቀቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ቢኒያም ታደሰ በበኩሉ፣ “እኔ የታሰርኩት የባልደራስ አባል ስለሆንኩኝ በቂም በቀል ነው፡፡ የአድዋን በዓል በሰላም አክብረን ወደቤታችን ገብተናል፡፡ እኔ የታሰርኩት የካራማራ የድል በዓልን በሰላም እያከበርን በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለቱም ላይ ፍፁም ሰላማዊ ነበርን” ብሏል፡፡
ቢኒያም ታደሰም ታዋቂ የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግርኳስ ክለብ አስጨፋሪ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከተከሳሾቹ መካከል አንዳንዶቹ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ለእስር የተዳረጉት የኳስ አስጨፋሪዎች በመሆናቸው ብቻ ተነጥለው ለእስር መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የእነ ቢኒያምን ችሎት ለመከታተል ታድመው ከነበሩት መካከል ናትናኤል የዓለምዘውድ ማስታወሻ ሲይዝ ተገኝቶ፣ፖሊሶች ከችሎት ከሕግ ውጭ ያስወጡት ሲሆን፣ አስካል ደምሌ ደግሞ የያዘችውን ማስታወሻ በፖሊስ መቀማቷን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በመጨረሻም፣ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ያሉት 31ዱ ተጠርጣሪዎች፣ ለሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ የተቀጠሩ ሲሆን፣ ቢኒያም እና ሳሙኤል ደግሞ፣ አብረዋቸው ከተካተቱት 13 የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር ፖሊስ በጠየቀው መሠረት የ14 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





