ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጉለሌ ክፍለ ከተማ በአራት መጋዘን ያለአግባብ የተከማቸ የምግብ ዘይት በተቋቋመው ግብረሃይል መያዙ ተገለፀ፡፡
የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ሰው ሰራሽ የዋጋ ውድነት በመፍጠርና ምርቶችን በመደበቅ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ህገወጥ ደላሎችንና ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከትናንት በስትያ ጀምሮ ግብረ ሃይል አቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት ግብረሃይሉ እያደረገ ባለው ቁጥጥር በዛሬው ዕለት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ስሙ ሙሉጌታ መናፈሻ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህብረተሰቡ ጥቆማ በአራት መጋዘን ውስጥ የምግብ ዘይት ክምችቱን መያዝ ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በርካታ ሌሎች ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ገልፆ፤ በተጨማሪም ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረሃይል በየአካባቢው ሰፊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
አሁንም ቢሆን ቁጥጥሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስታወቀው የከተማው አስተዳደሩ ፤ የከተማው ነዋሪም እንደተለመደው ጥቆማዎችን በማቅረብ የጋራ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






