ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በፀጥታ፣ በድህንነት፣ በትምህርት፣ በስልጠና እና በሰላም ማስከበር በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።
9ኛው የኢትዮ- ጅቡቲ የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ስብሰባ በአዲስ አበባ የመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ተካሒዷል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጅቡቲ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ዘካሪያ ሼክ ኢብራሒም፣ የሁለቱ አገራት ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና ጀነራል መኮንኖች እንዲሁም በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር በተገኙበት በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የፈረሙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ታሪካዊና የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን አውስተው፣ በባህልና በቋንቋም የጋራ አንድነት ያላቸው ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ብለዋል።
የሁለቱ አገራት ጥምር የመከላከያ ሰራዊት ኮሚቴ በስትራተጂክና በቴክኒክ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱ ለቀጣናዊው ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ገልፀዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ አገራቱ በሰላም ማስከበር ተልዕኮም ያላቸውን ሚና አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ጀነራል ዘካሪያ ሼክ ኢብራሒም በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል የሁለቱ አገራት ፌዴራል ፖሊሶች በድንበር አካባቢ የተለያዩ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል መፈራረማቸውን ገልፀው፣ አሁን ላይ በመከላከያ ደረጃ በትብብር ለመስራት ያደረግናቸው ስምምነቶች ለሁላችንም የሚጠቅም ወሳኝ ስምምነቶች ናቸው ብለዋል።
የመከላከያ ውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብ/ጀ ቡልቲ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በጋራ ድንበራቸው ላይ ቅኝት ማድረግ፣ በመረጃ ልውውጥ፣ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን በመከላከል፣ በባህል ልውውጥ ፣ በስልጠና እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከልና በሰላም ማስከበር ተግባራት አንድነታቸውን ለማጠናከር ፊርማቸውን ማኖረቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የጅቡቲ ወታደሮች በአገራችን የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን የወሰዱ መሆናቸውን አውስተው፤ ቀጣይም የዕውቀት ሽግግሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n







