ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰኔ 15 ክስተት ጋር ተያይዞ ከሕዳር 23 ቀን 2012 ጀምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ሲታይ የቆዩ ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ በተባሉ 31 ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎቱ በእያንዳንዳቸው ተከሳሾች ላይ ከእድሜ ልክ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ነው ያስተላለፈው፡፡
ከቅጣት ውሳኔው በፊት በተከሳሾች የቀረበውን የቅጣት ማቅለያ ተቀብሎ የመረመረው ችሎቱ ለአራት ተከሳሾች አምስት ማቅለያዎችን፣ ለ20 ተከሳሾች አራት ማቅለያዎችን፣ ለአራት ተከሳሾች ሦስት ማቅለያዎችን እና ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የቆዩ ሦስት ተከሳሾችን ደግሞ አንድ ማቅለያ ተቀብሏል፡፡
ማኅበራዊ አገልግሎት፣ የቤተሰብ ኀላፊነት፣ ሕመም፣ ወንጀሉን ከመፈጸማቸው በፊት የነበራቸው ለሀገር የተከፈለ ዋጋ እና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መኾኑ በቅጣት ማቅለያነት ታይቷል፡፡
ችሎቱ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የቆየውን የሻምበል መማር ጌትነት፣ በላይሰው ሰፊነው እና ልቅናው ይሁኔ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፤ በሌሎች 28 ተከሳሾች ላይ ደግሞ ከ15 ዓመት እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራት አስተላልፏል፡፡
18 ተከሳሾች በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች በ15 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ሁለት ተከሳሾች 16 ዓመት፣ አራት ተከሳሾች በ18 ዓመት እና ሁለት ተከሳሾች በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



