“በብልጽግና የስልጣን ዘመን የሞግዚት አስተዳደር ቀርቷል፤ ሁሉም ክልል እራሱ እየወሰነ ያስተዳድራል”:– የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው

0
1004

ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በብልጽግና የስልጣን ዘመን የሞግዚት አስተዳደር ቀርቷል፤ ሁሉም ክልል ስለራሱና ስለአገሩ ጉዳይ በነጻነት እየወሰነ በማስተዳደር ላይ ይገኛል ሲሉ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ ውይይት ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በህወሃት አስተዳደር ዘመን በክልሎች ላይ ተንሰራፍቶ የነበረው የሞግዚት አስተዳደር አሁን ላይ ቀርቷል። በብልጽግና የስልጣን ዘመን ሁሉም ክልል በእራሱ ሰውና በእራሱ አዕምሮ እንዲመራ ነፃነት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ክልሎች በህወሃት ዘመን ከአንድ ማዕከል በሚተላለፍ መመሪያ ይተዳደሩ ነበር ያሉት ርስቱ፤ አሁን በብልጽግና ዘመን ይህ ህገወጥ አሰራር ተቀይሯል። ብልጽግና ውስጥ ሁሉም ሃሳብ ለመስጠትና ለመወሰን ዕድሉ የተመቻቸለት በመሆኑ ክልሎችም በአገራቸውም ሆነ በክልላቸው ጉዳይ ዋነኛ ተሳታፊ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የሕዝቦች ምሬትና የለውጥ ፍላጎት የወለደው ብልጽግና በአንድ ማዕከል የሚመራ አሰራርን ሳይሆን ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ አሰራር እየተከተለ ነው ብለዋል።

ቀድሞ አጋር ናችሁ ተብለው ሲገፉ የነበሩ የክልል ፓርቲዎች ጭምር አሁን ላይ እራሳቸውን አድሰው በወሳኝነት በአገራዊ ጉዳዮች እየተሳተፉ ይገኛል። ይህ ለውጥ ቀድሞ የነበረውን ጨቋን አሰራር የቀየረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ የህወሃት ሰዎች በአንድ ብሔር በሚመራ አሰራር የብሔራዊ ደህንነቱንና የጸጥታ መዋቅሩን ተቆጣጥረውት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ርስቱ፤ ሌሎች ብሔሮች በአገራቸው የጸጥታም ሆነ ደህንነት ጉዳይ እንደማያገባቸው ሁሉ ገለል እንዲሉ ተደርገው መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ለውጡ ያመጣው ብልጽግና ፓርቲ አሳታፊ በሆነ መንገድ እየሰራ በመሆኑ ማንኛውም ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ በጸጥታና ደህንነት መዋቅሩ ውስጥ አገሩን እንዲያገለግል ዕድል ተፈጥሮለታል ሲሉ ተናግረዋል።

የየክልሉ አመራርና የብልጽግና ፓርቲ አመራር በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ እየሰጡ እንዲወስኑ የሚያስችል አሳታፊ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል። ይህም ከማዕከል የሚላክ የሞግዚት የአስተዳደር ሥርዓትን በማስቀረት ክልሎች በነፃነት ስለራሳቸው ጉዳይ እንዲመክሩና እንዲወስኑ በር ከፍቷል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ይህን አሳታፊነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ርስቱ፤ በፓርቲው አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ አባልና አመራሮቹ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል ሲሉ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የመጀመሪያው የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ከመጋቢት ሁለት እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል።
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here