የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት ያልጀመሩና ያቋረጡ ሰዎች ለኮቪድ19 ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው ተባለ

Views: 529
በኮቪድ19 ላይ ዓለማቀፍ መረጃ በማቅረብ ላይ ከሚገኘው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተወሰደ ፎቶ

 

 

 

የዓለም አቀፍ ወረርሺኙ ኮቪድ19 በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ላይ ጫናው የበረታ እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት በተደጋጋሚ አስታውቋል። በኢትዮጵያ ከ 600 ሺህ በላይ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች አሉ ተብሎ ሲገመት ከዚህ ውስጥ ከ 110 ሺህ በላዩ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተመርምረው ያላወቁ፣ አውቀው መድሃኒት መውሰድ ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ እንደሆኑ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ በኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ለአመታት አማካሪ በመሆን ያገለገሉት ቤዛዊት አድማሱ  እንደሚሉት መድሃኒታቸውን ባግባቡ እየወሰዱ ያሉ እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው በመደበኛ ሁኔታ ላይ ያሉ ሰዎች የተለየ ስጋት የለባቸውም። ነገር ግን አምስቱን የኮቪድ19 የመከላከያ እርምጃዎች ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ዝቅተኛ የበሽታ መከላከል አቅም ላላቸው ሰዎች ሲባል ባግባቡ መተግበር ይገባቸዋል ይላሉ።

‹‹ ቫይረሱ ይኖርብኛል ብለው ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ቢኖራቸውም ሄደው ለመመርመር ያልደፈሩ፣ ሃኪም የኤች አይ ቪ ቫይረስ እንዳለባቸው ቢያረጋግጥላቸውም መድሃኒቱን ያልጀመሩ ወይም ጀምረው ያቋረጡ ሰዎች ግን ቢቻል ዛሬ ወይም ነገ መድሃኒቱን መጀመር አለባቸው›› ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

‹‹ ከዚህ ባሻገር የአመጋገብ ስርአታቸውን እና የበሽታ መከላከል አቅምን የሚቀንሱ እንደ ሱስ ያሉ ልምዶችን በፍጥነት ማቆም እና የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚመከሩ እርምጃዎችን ሳያወላውሉ መፈፀም አለባቸው›› እንደ ቤዛዊት ገለጻ።

አምስቱ ምክሮች ምንድናቸው ?

  1. በቋሚነት እና ቶሎ ቶሎ እጅን በሳሙና መታጠብ፤ ወይም በአልኮል ነክ የእጅ ማፅጃዎች እጅን ማፅዳት
  2. ከሚያስነጥስ ወይም ከሚስል ሰው ቢያንስ የአንድ ሜትር ርቀት ላይ መሆን
  3. አፍ፣ አፍንጫን እና አይንን በእጅ ከመንካት መቆጠብ
  4. እጅን በንፅና ከጠበቁ በኋላ እርሶም ሆኑ በቅርበት ያለ ማንኛውም ሰው ሲያስነጥስም ሆነ ሲያስል አፉን መሸፈኑን ማረጋገጥ፣ አፍን በክንድ መሸፈን የሚመከር ሲሆን በሶፍት ከሸፈኑ ደግሞ ባግባቡ ሶፍቱን ያስወግዱ
  5. የህመም ስሜት ካሎት ከቤት አይውጡ፤ ህመሙ ትኩሳት፣ ደረቅ ሳል እና የመተንፈስ ችግር ካስከተለ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም ይሂዱ ወይም በ8335 እና 952 ተጨማሪ መረጃ እና እርዳታ ይጠይቁ።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ በኢትዮጵያ የተረጋገጡ የ ኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 11 ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ ያለ ነዋሪ በበሽታው ያለመያዙን እና ስርጭቱም ለግዜው ከውጪ አገር የመጣ እና አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት በመመልከት መረዳት ይቻላል።

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት 0.9 በመቶ ላይ እንደሚገኝ የፌደራል የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የመጨረሻ ሪፖርት ያሳይል። አገራዊ ስርጭቱ ከ አንድ በመቶ በታች ይሁን እንጂ በክልሎች ግን ከፍተኛ የስርጭት መጠን አለው።

በጋምቤላ 4.8 በመቶ፣ በአዲስ አበባ 3.4 በመቶ፣ ትግራይ እና አማራ እያንዳንዳቸው 1.2 በመቶ ስርጭት እንዳለ የመቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤቱ ሪፖርት ያሳያል። በዚህ መሰረትም አዲስ አበባ ያለው የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት በኢትዮጵያ ከጋምቤላ በመቀጠል ከፍተኛው ነው።

ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት ያለባቸው የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ደግሞ የበለጠ ተጠቂ መሆናቸው አይቀርም። ይህ በተለይም በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች ትኩረትን አንደሚጠይቅ ቤዛ ይናገራሉ። ተቋማቸውም ባለፈው አንድ ሳምንት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችን አግኝቶ በመሬት ላይ ያለውን ችገር መዳሰሱን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የምሽት መዝናኛዎች እንዲዘጉ ከተወሰነ ገና ጥቂት ቀን ቢሆንም የቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከተሰማ ወዲህ የምሽት እንቅስቃሴዎች ቀዝቅዘዋል። ወትሮውን እንቅልፍ የማውቃቸውና መሸታ ቤቶች በብዛት የሚገኙባቸው  ሰፈሮች አሁን ፀጥ ረጭ ብለዋል።

ታዲያ ህይወታቸውን በእነዚህ ቤቶች ላይ የመሰረቱ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የእለት ጉርስም አብሮ ቆሟል። ነገር ግን የምሽት መዝናኛዎቹ ባይዘጉ ደግሞ በ ኮቪድ19 የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ይቀጥላል። በጠባብ ቤት ውስጥ ብዙ ሰዎች በጋራ ሆነው መቆየት፣ በእጅ መጨባበጥ እና ከማያውቁት ሰው ጋር ማደር ለኮሮና ይበልጥ ተጋላጭ ሆነው እዲቀጥሉ ያደርጋል።

ቤዛዊት እንደሚሉት ደግሞ የኤች አይቪ ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ ተሰራጭቶ በሚገኝበት በዚህ የስራ መስክ የኮሮና ቫይረስ ከተጨመረ አደጋው ከባድ ይሆናል።

‹‹እንግዲህ የህይወት ጥያቄ ነው፣ ሁሉንም በገንዘብ ወይም በምግብ መደገፍ ባንችልም የምንችለውን ለማድረግ እሞክራለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፌደራል የኤች አይቪ ኤድስ መከላል እና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት በበኩሉ እስከ አሁን ኮሮና እና ኤች አይቪን ያቀናጀ የመከላከል ስራ አለመጀመሩን ገልጿል። ከዚህ ቀደም ያሉ ምርመራን እና መድሃኒት መውሰድን የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎች አሁንም መቀጠላቸውን የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዳንኤል በትረ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በመላው ዓለም 38 ሚሊዮን በላይ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸውን የአለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል። ከእነዚህ ውስጥም 36 ሚሊዮኑ አቃቂዎች፣ 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት እድሜአቸው ከ 15 ዓመት በታች የሆኑ እና ቀሪዎቹ ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን እንኳን የማያውቁ ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት የኤች አይ ቪ ክንፍ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች የበለጠ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ናቸው ሲል አስታውቋል። ይህም በእድሜያቸው የገፉ፣ ልብ እና የሳምባ ህመም ካለባቸው ደግሞ ጫናው የከፋ ይሆናል ብሏል። ዩኤን ኤድስ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ሃኪሞቻቸውን እንዲያማክሩ እና መሰረታዊ የሆኑት መድሃኒቶችን በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን እንዲያረጋግጡም ይመክራል።

ቤዛዊትም ሆኑ የተባበሩት መንግስታት አለማችን ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ወረርሺኝ የወሰደቻቸው ልምዶች ኮቪድ19ኝን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ትግል ከፍተኛ ትምህርት ሰጥተው ያልፋሉ ሲሉ ይስማማሉ። ይህም መፍትሄ ለማግኘት የቫይረሱን ተጠቂዎች ያሳተፈ መንገድ መከተል፣ ማግለል እና መድሎን በማሰቀረት መደጋገፍ፣ አብሮ በመቆም እና የመከላከያ እርምጃዎችን ባግባቡ በመተግበር ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ ማምጣት ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

ቤዛ የኤች አይቪ መድሃኒትም ሆነ ምርመራ በነፃ በመንግስት የሚቀርብ ስለሆነ ይህንን ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠይቀው ውሳኔ ብቻ ነው ይላሉ። ‹‹በኮሮና አይን አንድ ቀን ዋጋ አለው፣ ከነገ ዛሬ ይሻላል›› ብለዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com