ከሠሞኑ ዘይት 1ሺሕ ብር በላይ ሆነ በሚል የኑሮ መወደድ ምሳሌ ተደርጎ ሲቀርብ ነበር። ዘይት መሠረታዊ የሠው ልጆች ፍላጎት ውስጥ የማይመደብ የአስፈላጊው ምግብ ማጣፈጫ ቢሆንም፣ ለተንሰራፋው የኑሮ ውድነት መገለጫ ሊሆን የሚችል ነው። ይህ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ጠፋ ሳይባል ከ500 ብር ገደማ ተነስቶ 700 ሲገባ ያን ያህል ትኩረት ሳያገኝ ቀርቶ፣ አሁን ሺሕ ብር ገባ ሲባል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚልና የሚያሾፍም በዝቷል።
ዘይት ተወደደ ወይም ጠፋ ሲባል ለምን ሆነ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው ቢባልም፣ ያን ያህል ማጋነኑ ግን ከወቅቱ የአገሪቱ ኹኔታ አኳያ ተገቢ ነው ለማለት ያስቸግራል። አሁንም ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ዘራቸውና ዕምነታቸው እየታየ እየተገደሉ ባለበት አገር፣ ዘይት ጠፋ ብሎ ሕዝብን ማነሳሳት ትኩረት ለመሳብ ካልሆነ በቀር የበለጠ አሳሳቢውን ጉዳይ እንዳያስረሳ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።
በወለጋ አሁንም ድረስ ንጹኃን በታጣቂዎች ያለርህራሄ እየተገደሉ ባለበት ወቅት፣ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች ሕዝብን አስከፉ ተብሎ አላግባብ ወደ ዘይት ሥርጭቱ የሕዝቡን ትኩረት ለመውሰድ የሚሞከርበት አሠራር ሊታሰብበት ይገባል። የዘይት መወደድ በዕጥረት ሳይሆን በአሻጥር የተከሠተ መሆኑ በሚነገርበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፣ አንድን ጉዳይ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ አድርጎ ሕዝብን ማነሳሳቱ በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
ፖለቲከኞች በተከፋፈሉ ቁጥር እርስ በርስ ለመፎካከርና ለመጣጣል በሚፈጽሙት ሴራና አሻጥር፣ ሕዝብ መጎዳት እንደሌለበት ሊታወቅ ይገባል። ሕዝብ በአንዱ ቡድን ላይ እንዲነሳበት ሌላው አንጃ የሚፈጽመው ነው እየተባለ ለማባበል መሞከሩም አያዋጣም። እውነትን ሕዝቡ በጊዜ ሒደት ማወቁ ስለማይቀር ነገሮችን በሕግ አግባብ ከመነሻው በማጋለጥ ነዋሪ እንዳይጎዳ መደረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ዘይት በብዛት ሊመረትና ሊረክስ ነው ተብሎ ከተወራ ከጥቂት ወራት በኋላ እንዲህ አንገብጋቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደረጉ፣ አስቀድመው ሊዘጋጁ ይገባቸው የነበሩ የመንግሥት አካላትም ሊጠየቁ ይገባል። የሕዝቡን ትኩሳት ተረድተው ዘግይተውም ቢሆን 40 ሚሊየን ሊትር ዘይት ሊሠራጭ ነው ብለው ሕዝብን ማጓጓትም አንደወንጀል ሊታይ ይገባል። ገና የታሠበን ነገር አጋግሎ ችግሩ እንደሚፈታ አድርጎ ማቅረቡ፣ ዕልባት ሊፈልጉ የሚችሉ አካላትን ስለሚያዘናጋም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይደገም ሊታሰብበት ግድ ይላል። ውሸት ሁኖ ከተገኘም ይህን የተናገረውን ብቻ ሳይሆን ያሳሳተውም ጭምር መጠየቅ ይኖርበታል።
ዘይት ያን ያህል አንገብጋቢ የሠው ልጆች ፍላጎት ነው አይደለም የሚለውን ክርክር እንተወውና፣ አብዛኛው የገጠሩ ኢትዮጵያዊ ያለዘይትም ሆነ ሽንኩርት እንደሚበላ ይታወቃል። በከተማም ቢሆን ሽሮን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት ምግቦችን ከዓመታት በፊት ያለምንም ዘይት አብስለን እንመገብ እንደነበር የሚያውቅ በርካታ ሠው ይኖራል። ይህ በሆነበት ኹኔታ አሁን እየተለመደ ያለ የዘይት አጠቃቀም ከአቅርቦቱ ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ እያደር ችግር ላይ እንደጣለን ይነገራል።
የዘይትም ሆነ የሌሎች ምግቦችና ሸቀጦች መወደድ ለመንግሥት ሕልውና አደገኛ እንደመሆናቸው በአስቸኳይ ለራሱ ሲል ዕልባት ሊፈልግላቸው ይገባዋል። ለሕዝብ ሲባል መደረግ የነበረበት ቀደም ብሎ ችግሩ ተፈጥሮ ሕብረተሰቡ ዕሮሮ ከማሰማቱ በፊት ቢሆንም፣ አሁንም ጊዜው ሙሉ በሙሉ ስላልረፈደ መፍትሔውን ማምጣት ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ወደሸቀጦች አድርጎ የዜጎችን ሕይወት መታደግን እንደኹለተኛ ኃላፊነቱ አድርጎ መውሰድ የለበትም።
በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በርካቶች ለሞት፣ ለመፈናቀልና ጉስቁልና መዳረጋቸው ይታወቃል። እነዚህ በማንነታቸው ሳቢያ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን ዜጎች ለመታደግም ሆነ ከሰቆቃቸው ለማዳን እና ወደነበሩበት ሕይወት ለመመለስ መንግሥት መሥራት የሚጠበቅበትን እስካሁን እንዳላከናወነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ለውጥ የተባለው የባለሥልጣናት መተካካት ከተካሄደ ከአራት ዓመት ገደማ ወዲህ፣ የተለያዩ ዜጎች ለሞት፣ለመፈናቀልና ለችግር መዳረጋቸው ይታወቃል። በባለሥልጣናት ሽኩቻ ሳቢያ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሠተው የዜጎች መከራ፣ በጉጂ ዞን፣ በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመ ግፍ እስካሁን ጠባሳው አልጠፋም። አሁንም ድረስ ተመሳሳይ የዜጎች ሠቆቃ የሚሠማ ቢሆንም፣ መንግሥት ለሕልውናው አደጋ ከሆነው ከሰሜኑ ጦርነት በስተቀር የሚገባውን ትኩረት ሠጥቶ ባለማስቀረቱ አሁንም የዜጎች መከራና ሥጋት እንደቀጠለ ነው።
መንግሥት እንደሰሜኑ ጦርነት፣ “አቅም አንሶኛል፤ ዕርዱኝ!” ቢል የሚያግዘው እንደማያጣ ግልጽ ነው። ነገር ግን፣ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሠቆቃዎችን ሠምቶ መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት እንደማይሠጥ ለማወቅ የመንግሥት ሚዲያዎችም ሆኑ ካድሬዎቹ ምንና የት የተፈጸሙ ችግሮች ላይ ትኩረት እንደሚሠጡ ወደኃላ ትንሽ ሔዶ የሠሩትን መታዘብ ይቻላል።
ዜጎች ተፈናቅለው የሚረዳቸው ሳያጡ፣ ጎናቸውን አሳርፈው የሚረዱበት ቦታ ተቸግረው እስኪንገላቱ ድረስ የሕዝብ ሠቆቃ የተናቀበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። የመንግሥት ዋነኛ ዓላማና ግዴታ የዜጎቹን ደኅንነት ማስጠበቅ ሆኖ ሳለ፣ ከግለሰቦችና ከቡድኖች ጋር እንካሰላንቲያ ይመስል ሲበሻሸቅ ይታያል። ነፍስን ለማጥፋት ሌት ተቀን የማይቦዝኑ በበረከቱበት ዘመን መንግሥት ስሜ ጠፋ፣ ተሰደብኩ እያለ ዘይትንም ሆነ የሕዝብ በዓልን ተንተርሶ አምቧጓሮ ለመፍጠር መሯሯጡ ከአንድ በውጥረት ውስጥ ካለ መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም።
በረባ ባረባው አደባባይ እየወጡ፣ በሶሻሊስቱ ጎራ የተለመዱ ዓይነት ሠፋፊ ንግግሮችን እየደጋገሙ ሲያደርጉ የሚስተዋሉት ባለሥልጣኖች፣ የተፈጥሮ አደጋን አሊያም በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱትን ካልሆነ በስተቀር ሌላውን ተፈናቃይ ሆነ የተጎጂ ቤተሰቦች ለመጠየቅም ሆነ ለመርዳት ሲጣደፉ አይታይም። በክፉ ጊዜም ወገንተኛ ከመሆን ሹመኞችም ሆኑ ግለሰብ ፖቲከኞች እንዲቆጠቡ አዲስ ማለዳ አጽንዖት ሠጥታ ታሳስባለች።
በዜጎች ላይ የሚፈጸም መድሎ ይቅርና፣ የውጭ ዜጋ ላይ እንኳን የሚደረግ መድሏዊ አሠራር ምን ያህል እንደሚያሳፍርና የጠለቀ ጥላቻ እንደሚፈጥር ከወቅታዊው የዩክሬን ጥቁር ስደተኞች ታሪክ መማር ግድ ይላል። አገሪቷ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ስትገባ ዜጎች በገፍ ወደ ፖላንድና ጎረቤት የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ተሰደው ነበር። እነዚህ አገራት ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሶሪያና ሌሎች ስደተኞች ቦታ የለንም ብለው አጥር እያጠሩ፣ “አንድም ሰው አንቀበልም” እያሉ፣ አንዳንዶቹም ለዚህ ተግባራቸው ከሀብታሞቹ ክፍያ ሲቀበሉበት ነበር። ያ የታሪክ ቁስል ገና ጠባሳ ሳይሆን፣ አሁን በሚሊዮን ለመቀበል ሲሻሙ ማየት ቁስሉ እንዲመረቅዝና እንዲጠዘጥዝ አድርጓል።
መተዛዘንን ማየት ቢያስደስትም፣ ነጭ ለነጭ ብቻ ተብሎ ልዩነት መኖሩ ግን ብዙዎችን ማስከፋቱን፣ አንዱ ባለሥልጣኖቻችንን ማስተማር ያለበት ታሪክ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይባስ ብለው ጥቁሮችን ለይተው መሠደድ አትችሉም ብለው ጎረቤት አገር መግባት እንዳይችሉ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ ድንበር ላይ የመለሱበትን ምክንያት መሔጃ ያጡት ሲናገሩ ቂም ያስቋጥራል። ጠመንጃ ያዙና ለዩክሬን ተዋጉ እያሉ፣ እንደእንግዳ ይቅርና እንደዜጋ ሳያከብሩዋቸው በግድ ሙቱልን ማለታቸው አሳፋሪ ነው። ተወራሪ ናቸው ተብሎ ፕሮፓጋንዳ እንደተሠራላቸው ያልተገነዘበና ሲራራላቸው የነበረ የድሃ አገር ዜጋ በሠማው ሥራቸው እንኳን ሊያዝንላቸው፣ “ደግ አደረጓቸው” እያለ እንደሆነ ከተለያዩ ሚዲያዎች ዘገባ መረዳት ይቻላል።
ይህ የምዕራባውያኑ ቅሌት ዐይን አፍጦ ገሃድ የወጣው በችግር ጊዜ እንደመሆኑ፣ ጦርነት ላይ ቢሆኑም መሠራት ያለበትን ከሌለበት መለየት አለመቻላቸው፣ እንዲሁም መቅደም ያለበትን ጉዳይ ማወቅ እንደተሠናቸው ማሳየቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ነግ በኔ ብሎ ከነሱ ስህተትም ሆነ ከራሱ ጥፋት ጊዜ ሳይወስድ ሊማር ይገባዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



