ላለፉት ኹለት ዓመታት በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አልሚዎች ድጋፍ ሊሰጣቸው ነው

Views: 178

ባለፉት ኹለት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው አልሚዎች መንግሥት ድጎማ ለማድረግ እያስጠና ያለው ጥናት፣ በቀጣይ ኹለት ሳምንታት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በ2010 እና በ2011 በተለያዩ ዓመታት በተፈጠሩ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ጉዳት የደረሰባቸው ባለሀብቶች የድጎማው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ጉዳት በደረሰባቸው ኢንቨስትመንቶች ላይ ኮሚሽኑ ከመድን ድርጅት፣ ልማት ባንክ እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት በተውጣጣ ቡድን ሲደረግ የነበረው ጥናት በመገባደድ ላይ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ድጋፉ በቀጥታ በገንዘብ የሚደረግ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በመንግሥት ላይ የወጪ ጫና በማያስከትል መልኩ የግብር እፎይታ ጊዜ በመስጠት፣ ከቀረጥ ነፃ እድል እና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአእነዚህ ዓመታት የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ እስከ ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት እንደሆነ በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
መንግሥት በ2008 እና 2009 በተከሰቱ አለመረጋጋቶች ለባለሀብቶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርጓል ያሉት አበበ፣ ኹለተኛ ዙር ሊባል በሚችል መልኩ ባለፉት ኹለት ዓመታት በአልሚዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን በሚመለከት ሲጠና የነበረው ጥናት በኹለት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቆ መፍትሔ ይሰጣቸዋልም ብለዋል።

የሚደረገው ድጋፍ የግብር የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ እና ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚያደርግ መሆኑ ለሙስና የሚያጋልጥ እና ትክክለኛ ያልሆነ አሰራር ነው የሚሉት በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ በርካታ የምርምር ጽሑፎችን በማዘጋጀት የሚታወቁት ዓለማየሁ ገዳ ናቸው።

አሰራሩ ክስተቶቹ ሲፈጠሩ ወደ ሥራ የሚገባ በመሆኑ መስመር የያዘ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ ለባለሀብቶቹ የሚሰጠው የግብር እፎይታ ጊዜ እና ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ ያመጡትን ውጤት በትክክል ለመመዘን የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

አክለውም ባለሀብቶች ይህንን እድል በመጠቀም ደረሰኞችን ሊያጭበረብሩ እና ትልልቅ የታክስ ዋጋ ያላቸው እና ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ። ይህም የመንግሥትን ገቢ ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።

የሚደረገው ድጋፍ የደረሰውን ውድመት በገንዘብ በመተመን ገንዘቡን ለባለሀብቶቹ መስጠት የተሻለ እና ለቁጥጥር እና ለመመዘን የሚያመች በመሆኑ የገንዘብ ድጋፍ ቢደረግ የተሻለ ነው። ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት ግብሩን በተለመደው መንገድ ሊሰበስብ ይገባል። ይህም የታክስ ስርዓቱ እንዳይዛባ እና ለሙስና እንዳይጋለጥ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው፣ ለደረሱ ጥፋቶች ካሳ እና ድጋፍ ከመክፈል በላይ መንግሥት ሰላም እና ፀጥታን ለማስከበር ተግቶ መሥራት እንደሚገባው ጠቁመዋል። ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ከውጪ አልሚዎች በተጨማሪ የአገር ውስጥ ባለ ሀብቶችም የጉዳቱ ሰለባ ስለሚሆኑ መንግሥት እነርሱንም ሊመለከት እንደሚገባም ገልፀዋል።

ሰላም እና ፀጥታ ሲናጋ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ እንደ ትምህርትና ጤና ያሉ አገልግሎቶችም ጭምር የሚስተጓጎሉ በመሆኑ፣ መንግሥት ሰላምን እና ፀጥታን ለማስፈን መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል።

ድጋፉ የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እምብዛም ጥቅም የለውም። ጉዳት ቢደርስብኝ የግብር ቅነሳ አገኛለሁ ብሎ የሚመጣ አልሚ አይኖርምም ብለዋል።
አበበ አበባየሁ በበኩላቸው የሚደረገው የግብር ቅነሳም ይሁን ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ በወቅቱ የደረሰውን ጉዳት ለመተካት ብቻ የሚውል ነው ያሉ ሲሆን ማንኛውም ባለሀብት ጉዳት ላልደረሰበት ንብረት ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ እና የግብር እፎይታ እንደማያገኝ አስታውቀዋል፡፡

ለአልሚዎቹ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ድጋፍ ማድረጉ አዋጭ እንዳልሆነ የገለፁት አበበ ኮሚሽኑ የአልሚዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከ ሰላም ሚኒስቴር እና ከ ፌደራል ፖሊስ ጋር እየሰራ እንደሆነ ገልፀው የአማራ ክልልን ተሞክሮ በመውሰድ ለአልሚዎች የኢንቨስትመንት ፖሊስ የማቋቋም ሀሳብ መኖሩን ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡ የልማት እንቅስቃሴዎቹ የእኔም ናቸው ብሎ ሊጠብቃቸው ይገባል ያሉ ሲሆን አልሚዎችም ቢሆኑ በአካባቢው የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በ2009 አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኖ የተመዘገበው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በ2011 ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መውረዱን ብሔራዊ ባንክ ማሳወቁ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ፈሰስ ሲደረግ የነበረው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ2010 የአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ሲሆን፣ በ 2011 ደግሞ የሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት ከፍተኛ ማሽቆልቆል አሳይቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com