“የሕዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ሕዝቡ የሽፍታ ማከማቻና መደበቂያ ዋሻ ይሆናል”

0
1437

መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲ መምህርና ፖለቲከኛ ሲሆኑ፣ 1997 ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ በ2000 ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በአኅጉራዊና ክፍለ አገራዊ ልማት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከሐሮሚያ ዩኒቨርስቲ በግብርና ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡

በቤኒሸንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ ቦዴፓ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በቤኒሸንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ኹኔታና ከሙያቸው ጋር በተያያዘው የግብርና ኢኮኖሚ ላይ ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ቆይታ አደርገዋል፡፡

አዲስ ማለዳ፡- በኢትዮጵያ አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
መብራቱ አለሙ፡- አገራችን በእኔ ዕይታ ብዥታ ውስጥ ነው ያለችው። መስመሯን አጥርታ የያዘች አይመስለኝም። ለውጡንም ለማስቀጠል የታሰቡ ነገሮች ተግባራዊ አልተደረጉም። መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች አገር፣ በአንድ በኩል ኑሮ ውድነቱ ያሰቃያታል፤ በሌላ በኩል ብሔርተኝነቱ ያሰቃያታል፤ እርስ በእርስ እያባላን ነው። የዜጎች መፈናቀል በየቦታው በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራ፣ ሱማሌና አፋር መካከል ያለው ግጭት፣ በደቡብም በአማሮ በኩል አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ምናልባት ከአዲስ አበባ ውጭ በሞትና በመፈናቀል ውስጥ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

ኢኮኖሚውም በድርቅ፣ በኮረና፣ በጦርነት የደቀቀበት፣ አብዛኛው ምዕራባውያን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ፊታቸውን ያዞሩበትና በውጭ ዲፕሎማሲ የተዳከምንበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። ብዙም በጎ ነገር አለ ማለት አይቻልም።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ችግር ከሦስት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም እሰካሁን መፍትሔ ማግኘት አልቻለም። በክልሉ እንደሚንቀሳቀስ ፓርቲ አሁን ያለውን ኹኔታ እንዴት ይመለከቱታል? ለምን መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም?
እኔ የማስበው መጀመሪያውኑ ለውጡ በትክክል መካሔድ ነበረበት- በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል። ያኔ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ቤኒሻንጉል ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አልተደረገም። በፊት በሕወሓት ጊዜ የነበሩ ሰዎች ናቸው አሁንም ክልሉን እየመሩ ያሉት። ክልሉ ደግሞ የአመራር ውድቀት ያለበት ክልል ነው። የአመራር ውድቀቱ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ በክልሉ ችግር ፈጥሯል። የጉምዝ አማጽያን ተፈጥረዋል፤ የኦነግ አማጽያን ተፈጥረዋል። አማጽያኑን ደግሞ እነ ሱዳንም እነ ግብጽም ከኋላ አይዟችሁ እያሉ በገንዘብም በትጥቅም እያገዟቸው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

በዚህ ምክንያት ባለፉት ኹለት ሦስት ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል፤ በጅምላ ተቀብረዋል፤ ሙስሊሙም ክርሰቲያኑም በዶዘር አንድ ገደል ውስጥ በአንድ ላይ በጅምላ የተቀበረበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው። ብሔር ከብሔር መጠራጠር ውስጥ እንድንገባ የተደረገበት ኹኔታ ውስጥ ገብተናል።

በመሠረተ ልማት በኩል በተለይ በመተከልና በካማሽ ዞኖች የውኃና የመብራት አገልግሎት የተቋረጠበትና ሕዝብ እየተሰቃየ ያለበት ኹኔታ ተፈጥሯል። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ኹኔታ ተፈጥሯል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለ እጀባ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ለዚህ ኹሉ ክፍተት ተጠያቂው እራሱ ብልጽግና የነበረው የአመራር ክፍተት ነው። ክፍተቱን እራሱ ብልጽግና አምኗል። በዚህም የተነሳ ብዙ አመራሮች በቁጥጥር ሥር ውለው፣ የታሠሩት ደግሞ እንደገና ተፈተው፣ አማጽያኑ ደግሞ ሥልጣን እንሰጣችኋለን ተብለው ሲቀለቡ ከርመው ወደ አመጽ ተመልሰው ችግር የፈጠሩበት ኹኔታ ተፈጥሯል።

እኛም ይህንን ደርጊት ስንቃወም ነበር፤ መንግሥትም በኋላ የተጸጸተበት ሁኔታ ነው። ቤኒሻጉል ጉምዝ ላይ አሁንም ይሄ ነገር ተቀይሯል የሚል ዕምነት የለኝም። ስለዚህ የአመራር ውድቀትና ክፍተት ጸጥታው እንዳይረጋጋ፣ ሠላም እንዳይመጣ፣ ልማት እንዲስተጓጎል አድርጓል።
በዚህ ኹኔታ የክልሉን የጸጥታ ችግር መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንደኛ የጸጥታ ኃይሉን የሚመራ ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል። አብዛኛው የጸጥታ ኃይሎች የሚመሩት በአብዛኛው በጉምዝና በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ነው። ከብሔር ነጻ የሆነ የጸጥታ ኃይል መገንባት ያስፈልጋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ለታጣቂ ኃይሎች መሣሪያ ሲያቀብል ተይዞ ዕሥር ቤት ነው ያለው። የእሱ መስመርና ግንኙነት እስካሁን አልተበጣጠሰም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ውስጥ። አሶሳ ማረሚያ ቤት ውስጥ የቤነን ታጋይ የነበረ በክልሉ የበላይ አመራር ትዕዛዝ ከማረሚያ ቤት እንዲወጣ ተደርጓል። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች እያሉ ሠላም እናመጣለን ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ከአሁኑ የጸጥታ መዋቅሩን እንደገና መፈተሽ፣ በጸጥታ ኃይሉ ውስጥ ያሉ ኃይሎች የብሔረሰብ ስብጥር በደንብ መታየት አለበት።

በአብዛኛው ከ90 በመቶ በላይ የጸጥታ ኃይሉ በኹለት ብሔረሰቦች ብቻ የተሞላ ነው። ስለዚህ አማራም፣ ሽናሻም፣ ኦሮሞም፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦችም በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ ሕብረ ብሔራዊነቱን እንዲጠብቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ጸጥታውን የሚመሩ አካላት ነጻና ገለልተኛ መሆናቸው መፈተሸ አለበት። ፖለቲካው ነው ጸጥታውን እየመራ ያለው። ፖለቲካው ሲበላሽ የጸጥታ ሁኔታውም እየተበላሸ አሁን ያየናቸው ጉዳቶችና ጥፋቶች ደርሰዋል።

ከጸጥታ ኃይል ማስተካከል ውጭ መፍትሔ የለም?
ሌላው ውይይት ነው። ቤኒሻንጉል ጉምዝ ውስጥ ውይይት አልተፈጠረም፣ ሁሌ የጸጥታ ችግር ሲፈጠር የሚወያየው እራሱ የጸጥታ አካሉ እና የብልጽግና አመራሩ ነው። በዚያ ክልል ውስጥ ሠላም እንዲመጣ ከተፈለገ ባለድርሻ አካላት የመፍትሔ ሐሳቦች ማመንጨት አለባቸው።
ክልሉ ውስጥ ብዙ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፣ ከእነሱ ጋር ምን ይሻላል? እንዴት እናድርግ? ችግሩ ምንድን ነው? ብሎ መመካከር ያስፈልጋል። ችግሩ መጠናት አለበት። ከጎረቤት ክልሎችም ጋር መነጋገርር ያስፈልጋል፤ አማራ ክልል አለ፣ ኦሮሚያ ክልል አለ። የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ሊመክሩበትና የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያስቀምጡበት ይገባል።

ኹሉ እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ መንግሥት በራሱ መንገድ ይሔዳል፤ በመጨረሻ ምንም ለውጥ የለም፤ ጉዳትና ውድመት ነው እየተፈጠረ ያለው። ስለዚህ ኹሉንም ባለድርሻ አካላት ያማከለ ውይይትና ምክክር ያስፈልጋል።

በክልሉ እስካሁን ምርጫ አልተደረገም እና ስለ ምርጫ እንደ ፓርቲ ምን መሆን አለበት ትላላችሁ?
ክልሉን እየመራ ያለው ምርጫ ያላካሄደ መንግሥት ነው። ሕጋዊ መንግሥት አይደለም ያለው፤ እኛም በተደጋጋሚ ገልጸናል ያው ሕግ የሚያከብር መንግሥት አይደለም ያለው። ሕገ መንግሥቱም እየተከበረ አይደለም። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕገ መንግሥት የመንግሥት ሥልጣን አምስት ዓመት ነው የሚለው። አሁን ግን ለስምንት ዓመት ያለምንም ምርጫ እየመሩት ነው ያለው።

እንደኛ ፓርቲ፣ ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ነው። ሥልጣን ማራዘም የሚቻለውም በምርጫ ነው የሚል ጽኑ ዕምነት አለን። ያ ግን ተጥሷል። ያንን በተለያዩ መግለጫዎች አሳውቃናል። ስለዚህ ምርጫው ቢካሔድ የተለያዩ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ይሳተፋሉ፤ የማኅበረሰቡንም ችግር ከመፍታት አንጻር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

ቤኒሻንጉል ላይ ከገዥው ፓርቲ ይልቅ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ተቀባይነት አላቸው። ምርጫውን ለማካሄድ የጸጥታው ሁኔታ ለውጥ አላመጣም። የምርጫውን እንቅስቃሴዎች ለማካሄድ ምቹ ሁኔታዎች የሉም። ይሄን ደግሞ የክልሉ መንግሥት እንደ ሥልጣን ማራዘሚያ ነው የሚጠቀመው።

በዚህ ረገድ ምርጫ ቦርድም ጠንከር ያለ ዕርምጃ ቢወስድ። ምርጫውን እናካሂድ ቢባል በኹሉም ቦታዎች ማካሄድ የሚቻል አይመስለኝም። የሠላም ሚኒስቴርም፣ የጸጥታ ኃይሎችም፣ መንግሥትም መጀመሪያ ለሠላም ትኩረት ሠጥተው ከዚያ በኋላ ምርጫ ቢካሄድ መልካም ነው።

ፓርቲያችሁ ምርጫ አለመካሄዱን ተከትሎ የሥልጣን ተጋሪ ሆኗል፤ ምን ለውጥ አመጣችሁ? ምንስ ተረዳችሁ?
በጠቅላላ ጉባዔያችን አንዱ አጀንዳችን ሥልጣን ከተጋራን በኋላ ምን ለውጥ አመጣን የሚለውን የምንመለከተው ይሆናል። ሥልጣን በመቀበላችን የተፈጠረው ችግሮችም ነበሩ። እንደ ፓርቲ የመቀዛቀዝ ውሳኔታዎች እና ፓርቲውን ችላ የማለት ሁኔታዎች ገጥመውናል። በግምገማ እናስተካክለዋል።

እኛ የያዘነው አንድ የካቢኔ ወንበር ነው። አመንቴ የያዘው የገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት። እዚያ ከገባን በኋላ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዳያስፖራዎች በኩል ጥሩ ሥራዎች ሠርቷል። የዳያስፖራ ዘርፍ ኃላፊዎች ሥራውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት እስከማድረግ ደርሰዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር ምስጋና እንደተቸረው ነው የምነግርህ።

ፍትሐዊ የሆነ ኢንቨስትመንት ላይ፣ የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መስፈርቶቹን አማልቶ እስከመጣ ድረስ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችል ያረጋገጥንበት፣ ወደ ኹለት ሺሕ የሚደረሱ ኢንቨስትሮች ውዝፍ ጥያቄያቸው መልስ ያገኘበት ጊዜ ነው።
ሌላው የያዝነው ወንበር ሥራ አመራር ተቋም ነው። ሥራ አመራር ተቋም ዮሐንስ የሚመራው ነው። እሱም የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራዎችን ሠርቷል። በብዛት የአመራርነት ሥልጠና የሚሠጥበት ተቋም ነው። ተቋሙን ለማዘመን የማሻሻያ ሥራዎች እየሠራ ነው።

ክልሉ የሕዳሴው ግድብ መገኛ ከመሆኑ አንጻር ምን የተለየ ትኩረት ይሻል?
ከሠሞኑ የሕዳሴው ግድብ ሲመረቅ እኛም መግለጫ አውጥተናል እንደ ፓርቲ። የሕዳሴው ግድብ አይደለም ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካም ለዓለምም ተምሳሌት የሆነ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ዐይን ብሌኑ የሚያየው ግድብ ነው። ለዘመናት የነበረንን ቁጭት የሳየንና ዓባይ ላይ መጠቀም እንደምንችል የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት ነው።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በላይ ኢትዮጵያ ዓባይን የመጠቀም መብቷን ያረጋገጠችበት ፕሮጀክት ነው። ይሁን እንጂ ትኩረት መሰጠት ያለበትን ያክል ትኩረት አልተሰጠም። ሕዳሴው ግድብ ለመሄድ መንገድ እንኳን የለም፤ ከሕዳሴው ግድብ ግልገል በለስ ለመድረስ 15 ኪሎ ሜትር ነው፣ ነግር ግን ከግልገል በለስ ሕዳሴ ግድብ ለመሄድ፣ ከግልገል በለስ ባህር ዳር፣ ከባህር ዳር አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ በአውሮፕላን አሶሳ መጓዝ ግዴታ ሆኗል። ከአሶሳ ሕዳሴው ግድብ ለመድረስ በሔሊኮፕተር ነው የሚኬደው። የክልሉ አመራሮች የምርቃቱ ዕለት ሊደርሱ አልቻሉም።

በሚያሳዝን ሁኔታ በጸጥታ ችግር የክልሉ ባለሥልጣናት ለግድቡ ኃይል ማመንጨት ምርቃት ላይ መገኘት አልቻሉም። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሔሊኮፕተር ተልኮለት ሔዶ ማረፍ ባለመቻሉ ሳይታደም ተመልሷል። ይሄ ደግሞ በጣም አሳፋሪ ነው። መንግሥት ለአካባቢው የሠጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው። ክልሉ በጣም ተረስቷል። መሠረተ ልማት፣ የመንገድና የመብራት አገልግሎት በጣም ትኩረት ሊሠጣቸው ያስፈልጋል።

ሠሞኑን ብዙ የሕዳሴው ግድብ ሠራተኞችና አጃቢዎች በጉምዝና በሱዳን ሠርጎ ገቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ብዙ ሰዎች ተሰውተዋል። ጸጥታው አሁንም አልተረጋጋም፤ ግድቡን እየገነባ ያለው ማኅበረሰብ በሽፍታው ኃይል እየተገደለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ ምክንያት ለምንድን ነው ትኩረት የማይሰጠው የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ ይጭርብኛል። መንግሥት ለምን ዝም አለ የሚለው ጉዳይ ለእኔም እንቆቅልሽና መልስ ያጣ ጉዳይ ነው የሆነብኝ። መንግሥት አካባቢው ላይ በጸጥታ እና በመሠረተ ልማት ላይ ትኩረት ሠጥቶ መሥራት አለበት።

ክልሉ ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑት ድንበሮች ታጣቂ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ይገባሉ፤ አካባቢው ከሉዓላዊነት አንጻር ምን የተለየ ነገር ይሻል?
እኔ ባለኝ መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ሱዳን ውስጥ፣ እነማን እያደራጁ እንደሚልኩ ሁላ መረጃ አላቸው አርግጠኛ ሆኘ የምነግርህ። እነዚን የሽፍታ ኃይሎት እያደራጁ የሚልኩ እነ ማን እንደሆኑ ይታወቃል። ሱዳን ጋር ያለን ዲፕሎማሲ ደግሞ እየሻከረ ነው የመጣው። ሱዳንም በጦር ኃይሉ እና በሲቪሊያኑ ኃይል መካከል በተፈጠረው ችግር ለራሷ አልተረጋጋችም። ወታደራዊ ኃይሉ ደግሞ የግብጽ መልዕክተኛ ዓይነት ሥራ ነው እየሠራ ያለው።

ከሱዳን ጋር ያለንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር አለብን። በድንበር አካባቢ ያለውን ችግር በመነጋገር መፍታት ቢቻል፣ ወደ 900 ኪሎ ሜተር ድንብር አለን ከሱዳን ጋር። አጠቃላይ በዚያኛው ወገን ያለው የቤኒሻንጉል ድንበር ከሱዳን ጋር ይዋሰናል። የሚያዋስነው ድንበር ክፍት ስለሆነ፣ ማንኛውም ማጥቃት የሚፈልግ ኃይል ገብቶ አጥቅቶ መውጣት ይችላል።

ስለዚህ በድንበር በኩል የጸጥታ ኃይል ማሰማራት፣ ቁጥሩን ማብዛት፣ ከሱዳን ጋር በጎን ዲፕሎማሲዊ ንግግር መጀመር የግድ ይላል። ግብጽና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን አመለካከት እናውቃለን፣ ግድቡ እንዲያልቅ አይፈልጉም። ስለዚህ ለማስተጓጎል የማይፈነቅሉት ድንጋይ ስለማይኖር የዲፕሎማሲ ሥራውን ማጠናከር፣ የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር ምንም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።

ይሄ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። ትግራይ ጋር ከምትዋጋ ይልቅ፣ በሱዳን በኩል የለውን ጸጥታ በደንብ ብታጠናክር የተሻለ ለውጥ እናመጣለንብ ብዬ አስባለሁ።

በክልሉ የታጠቁ ኃይሎች ከሱዳን እየወጡ እየወጉን ነው፤ እንዴት ማስቆም ይቻላል?
በክልሉ ከሱዳን የሚገባውን የሚወጣውን ኃይል ለማስቆም አመራሩ መጥራት አለበት። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አመራር ከርዕሰ መስተዳደሩ ጀምሮ እስከ ታች ያለው መፈተሽ አለባቸው። ይበቃቸዋል፤ እነዚህን ሰዎች ሌላ ቦታ ለምን መቀየር ተፈራ? እጃቸው እንዳለበት እኮ ይታወቃል ምንም ጥያቄ የለውም፤ እነሱም ያምናሉ። በቅርቡ ከማረሚያ ቤት አመለጠ የተባለው ሽፍታ፣ ከአሶሳ ማረሚያ ቤት እንዲወጣ የተደረገው በክልሉ የበላይ አመራር ነው። ይሄ ሰውዬ ኤርትራ ውስጥም ጦር ሲመራ የነበረ ሰው ነው። ያለ ምንም ምክንያት እንዲወጣ ያደረገ የክልል መንግሥት ካልተጠየቀ እንዴት ሽፍታውንስ መቆጣጠር ይቻላል?

ስለዚህ፣ ሽፍታውን አይዞህ የሚል የአመራር አካል አለ፤ መጀመሪያ እሱን ማጥራትና ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ኹለተኛ ሕዝቡን በደንብ መቅረብ ያስፈልጋል። ሕዝብና መንግሥት ተናበው አብረው ካልሰሩ ሽፍታ የሚደበቀው ሕዝብ ውስጥ ነው። ስለዚህ ሕዝቡ መንግሥትን እንዲያግዝ ማድረግ፣ ይህንን ማድረግ የሚቻለው የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ሲቻል ነው። የሕዝብ ጥያቄ አልተመለስም፤ ሕዝቡ ተፈናቅሏል፤ ሠላም የለም፤ በልቶ እያደረ አይደለም ጨለማ ውስጥ ነው የሚኖረው። መሠረተ ልማት የለውም።

የሕዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ሕዝቡ የሽፍታ ማከማቻና መደበቂያ ዋሻ ነው የሚሆነው። ስለዚህ አመራሩን ማጽዳትና ከሕዝብ ጋር መሥራት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል እነዚህ ኃይሎች ምንድን ነው የሚፈለጉት? የሚለውን ማጥናትና ወደ ውይይት የሚመጡ ከሆነ የሚመጡበትን ሁኔታ ማየት ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያ የገባችበት የሰሜኑ ጦርነት ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ችግር ጋር እንደሚገናኝ መንግሥት ይገልጻል። የክልሉ የጸጥታ ችግር ከሕወሓት ጋር የተገናኘ ነው ከተባለ የሰሜኑን ጦርነትና የክልሉን የጸጥታ ችግር እንዴት ማስቆም ይቻላል?
ሕወሓት በክልሉ ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የመሣሪያና ቴክኒካል ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፣ የታወቀ ነው። አሁን ላይ ግን በሕወሓት ማሳበብ ጥሩ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሕወሓት የራሱን የቤት ሥራ እየሠራ ነው። ምናልባት ሱዳን ውስጥ የሕወኃት ኃይል ካለ ሊያግዝ ይችላል። ትግራይ ውስጥ ያለው ሕወሓት በየት በኩል አልፎ ነው ድጋፍ የሚያደርገው? በሕወሓት ማሳበብ አንችልም።

አሁን ማሳበብ የምንችለው የክልሉ መንግሥት በቂ የጸጥታ ኃይል አላሰማራም። የጸጥታ ኃይሉ አንደኛ ተአማኒ ነው ብዬ ለመገመት ይከብደኛል። የተወሰኑ የጸጥታ ኃይሎች አሉ የክልል ልዩ ኃይል የነበሩ። ለጸጥታ ሥራ ሲላኩ ሽፍታው ጋር የሚቀላቀሉ ከእነ መትረየስ መሣሪየቸው ሽፍታው ጋር እየገቡ ባለበት ሁኔታ ላይ በሌሎች ላይ ማሳበብ ተገቢ አይመስለንም።

ስለዚህ፣ መጀመሪያ እራስን መፈተሸ ያስፈልጋል የሚል ዕምነት አለኝ። ሌላው እንደ አገር አሁን ከገባንበት ቀውስ ውስጥ ልንወጣ የምንችል የነበረው በታሰበው አገራዊ ምክክር ነበር። እሱም የገለልተንነትና የግልጸኝነት ጥያቄ ተነስቶበታል። የኮሚሽን ማቋቋምና የኮሚሽነሮቹን ምርጫ ሒደት በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገምግመናል። በሒደቱ ላይ የሠጠናቸው ግብዓቶች ከግምት ውስጥ አልገቡም።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አሁን ጥርጣሬ ተፈጥሯል። ባለፈው የነበረው የጋራ ምክር ቤቱ ስብሳባ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የፍትሕ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ በአካል ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ወስነን ነው የተለያየነው። ሚኒስትሩ ቀርበው የማያስረዱ ከሆነ ግን ፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ አገራዊ ምክክር እራሳቸውን ሊያወጡ የሚችሉባቸው ኹኔታዎቸ ይኖራሉ። ይሄ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ አይሰጥም።

እኛ ያሰብነው አገራዊ ምክክሩ ተፋላሚ ኃይሎችንም ጭምር፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችንም ጭምር፣ ምሁራንንም ጭምር፣ ሕዝብንም ጭምር ያሳተፍ ሕገ መንግሥት እስከ መቀየር ድረስ የሚያደርስ፣ በታሪክም ሁሌ እንጣላለን፣ የባንድራ ጉዳይ አለ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳይ አለ። እነዚህ ጉዳዮች የራሳቸው ሚና አላቸው። በአገሪቱ ሠላምና ጸጥታ፣ መግባበትና አንድነት ማስፈን ካልቻልክ ሠላምን ማምጣት ይከብዳል። እነዚህ ነገሮች ላይ ከተስማማንና ወደ አንድ መምጣት ከቻልን አብዛኛው የሠላም ችግር ዜሮ መሆን ባይችልም ሊቀንስ ይችላል።

የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደ መሆንዎ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሠተው የጸጥታ ችግር ሠዎች በማፈናቀሉ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ እንዴት ይገልጹታል? ኢኮኖሚውስ ምን ይሻል?
የጸጥታ ችግሩና ጦርነቱ በግብርና ኢኮኖሚው ላይ ያሰደረውን ተጽዕኖ በጥናት ላይ ተመስርቶ ማስቀመጥ ቢቻል ጥሩ ነው። ዞሮ ዞሮ የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት የተመናመነበት፣ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች እርሻ የቆመበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደ ምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከልን ብንመለከት ሕዝቡ ተፈናቅሎ ነው ያለው። ባለፈው የምርት ዘመን አላረሰም። ዘንድሮም ካላረሰ ሕዝብ ችግር ላይ ይወድቃል። የክልሉ ሕዝብ ብቻ አይደለም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ረሃብ የሚገባበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል።

በሱማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል በተከሠተው ድርቅ እንስሳቶች የሚመገቡት መኖ ጠፍቶ ችግሩን እያየነው ነው። የዳቦ ዋጋ፣ የጤፍ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የሔደበት ሁኔታ ነው ያለው። አሶሳ አንድ ማንጎ 25 ብር እየተሸጠ ነው። አንድ ማንጎ ማለት በኹለት ብር በሦስት ብር መገዛት የነበረበት ፍራፍሬ ነው። የጦርነቱና የጸጥታ ችግሩ በመባባሱ በግብርና ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።

እኛ ደግሞ የውኃ ኃይል ቢኖረንም፣ የመስኖ ልማት አቅማችን እጅግ በጣም አናሳ ነው። ስለዚህ ቴክኖሎጅና መስኖ አርሶ አደሩ መጠቀም ይችላል ወይ ብለን ብንጠይቅ? አይችልም። ኢኮኖሚው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው። የመንግሥት ሠራተኛውን ኑሮ ብታይ የሚያገኘው ደሞዝ እጅግ በጣም አናሳ ነው። ኑሮው ሠማይ ደርሷል፣ እነዚህ ቀውሶች ምንድን ነው የሚፈጥሩት ካልን ዝርፊያን፣ አመጽን ነው የሚፈጥሩት። የኑሮ ውደነቱ በራሱ በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር የራሱ አስተዋጽዖ አለው።

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትና ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ መንግሥት ሠላምና መረጋጋትን መፍጠር የመጀመሪያ ሥራ አድርጎ መውሰድ አለበት። እራሱን ዝቅ አድርጎ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቆ ነው መንቀሳቀስ ያለበት እንጅ እናንተ አታውቁም አኔ አውቅላችኋለሁ ዓይነት ፖለቲካ እዚች አገር ውስጥ የሚያጠፋፋ እና የሚያወድም መሆኑንን ብንረዳ ይሻለናል።

ኢኮኖሚው እንዲያገግም መጀመሪያ ጦርነቱ መቆም አለበት። አሁነ እኮ አብዛኛው ኢኮኖሚ የሚዳከመው የጦር መሣሪያ በመግዛት ነው። የጦር መሣሪያ ያወጣነው ገንዘብ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ቢውል ኖሮ ኢኮኖሚው ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር። አንድ ብር በግብርና ላይ ኢንቨስት ስታደርግ ስምንት ብር ትርፍ ታገኛለህ። እዚህ አገር እንደ ግብርና አዋጭ ኢንቨስትመንት የለም። አንድ ሚሊዮን ብር ግብርና ላይ ኢንቨስት ብታደርግ ስምንት ሚሊዮን ብር ምላሽ (ሪተርን) ታገኛለህ።

የግብርና ምርትን ማሳደግ የሚቻለው በኹለት መንገድ ነው። አንደኛ የሚታረሠውን መሬት በማብዛትና የማይታረሱተን ወደ እርሻ በማስገባት። ኹለተኛ መደጋገም፣ በዓመት ኹለት ሦስት ጊዜ ማረስ ነው። ወጣቱ ግብርና ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ፤ ወጣቱን ግብርና ላይ መሥራት አይፈልግም። ግብርና ውስጥ መሰማራት የተናቀ ሥራ አደርጎ የመውሰድ ሁኔታ አለ። ይሄንን መቀየርና ወጣቱ በስፋት ግብርና ላይ እንዲሠማራ ማድረግ ያስፈልጋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here