በእነዋሪ አሁንም ግለሰቦች በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ አስታወቁ

Views: 296

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ ከተማ የሚገኙ የወንጌላውያን አማኞች አሁንም በስጋት እና በፍራቻ ውስጥ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሙሉ ወንጌል ቤተክርስትያን አመራር እንዳስታወቁት፣ ከመጋቢት 1 እስከ 3/2012 የእነዋሪ ከተማ ነዋሪዎች በሆኑ ወጣቶች በቤተ እምነታቸው እና በአማኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ቢሆኑም፤ የሚመለከተው አካል ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም ደግሞ ወደ ሕግ መሔዳቸውን ካላቆሙ እና የጀመሩትንም ክስ ካላቋረጡ ጉዳት እንደሚያደርሱባቸው በየቀኑ እንደሚዝቱባቸው ጠቅሰዋል።
ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ላይ በእሳት በማቃጠል ጉዳት በደረሰበት ወቅት በምእመናን ላይም ድብደባ የደረሰ ሲሆን፣ በርካታ ንብረቶችም እንደተዘረፉ ለማወቅ ተችሏል። ይህንም ተከትሎ በደረሰባቸው ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ግለሰቦች በደብረ ብረሃን ከተማ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በእጃቸው ላይ ስብራት፣ በወገባቸው ላይ የመቀጥቀጥ እንዲሁም በከባድ ሁኔታ የመፈንከት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

የቤተክርስትያኑ አመራር ጨምረው እንደገለጹት፤ በወቅቱ የግንባታ ብረቶች፣ ለ30 ዓመታት የተደራጁ የሙዚቃ መሣሪያዎች እና ሌሎች 47 ዓይነት፣ በአጠቃላይ 15 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ተዘርፈዋል። አመራሩ አያይዘው፤ ችግሩ የተፈጠረው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለማስገንባት በሒደት ላይ በነበረበት ወቅት ስለነበር፣ የግንባታ ብረቶች ሙሉ በሙሉ ተዘርፈው እንደነበርና ከሌሎች ዕቃዎች ጋርም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እየተመለሱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን ላይ የዛቻ እና የማስፈራራት ድርጊቶች እየደረሱባቸው ሲሆን፣ የዞኑ ፖሊስ መምሪያም ጉዳዮን ለማርገብ ወጣቶችን በማስተማር እና በማወያየት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህ ጉዳይ ግን ያለፈውን ክስተት ድጋሚ እንደማይከሰት ማስተማመኛ እንደማይሆን ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አመራሩ አክለውም በቤተ ክርስቲያኗ አማካኝነት የሕክምና ባለሙያ የሆኑ እስራኤላውያን ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ተከትሎ የተደራጁ ወጣቶች ወደ ስፍራው በመምጣት ‹‹የምትሰጡት መድኃኒት የፍስክ ነው፣ ስዕል ረግጣችኋል›› እና መሰል ምክንያቶችን በማንሳት፣ ጉዳት እንዳደረሱ አስታውቀዋል። ይህንም ተከትሎ የእስራኤላውያን የሕክምና መሣሪያ ሙሉ በሙሉ መዘረፉን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ይሁን እንጂ አመራሩ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ በእርግጥ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይህን እንደማይፈጽሙ እና ያውም በጾም ወቅት እንዲህ ያለ ጸያፍ ተግባር ውስጥ እንደማይሳተፉ ግልጽ ነው። ነገር ግን ከጀርባ ወጣቶችን አደራጅቶ የፖለቲካ ሥራውን ለመሥራት የሚፈልግ ቡድን እንዳለ ይሰማኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ጉዳዩን በሚመለከት የሰሜን ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ፖሊስ እና የዞኑ አቃቤ ሕግ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ስለ ጉዳዮ ምክክር ላይ እንደሚገኙና ይህም በቅርቡ እልባት ላይ እንደሚያደርሳቸው አስታውቀዋል። ጽሕፈት ቤቱ አያይዞም ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ግለሰቦች በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com