ለሠው ልጅ እንደመጠሪያ ሥሙ ለጆሮው የሚጥም ሙዚቃ የለም እንዲሉ፣ የራስን ባህል፣ ኃይማኖት፣ እንዲሁም የሚደግፉትን ቡድንና የፖለቲካ ፓርቲ ከፍታ ሠጥቶ ሌላኛውን ዝቅ በማድረግ፣ በ “የኔው ይብለጥ” አጉል ዕሠጥ አገባ እርስበርስ መናቆር አንድነታችን ነፍጎን እየከፋፈለን ስለመምጣቱ በርካቶች አስተያየታቸውን እየሠጡበት ነው።
በፖለቲካ መበሻሸቅ ከድሮ ጀምሮ የቆዬ እንጂ አሁናዊ ክስተት አይደለም። ከተወሠኑ ጊዜያት ወዲህ ያለው ኹኔታ ግን አንድነትን ከማጥፋትም አልፎ፣ ለለየለት ጦርነት እያደረሰን ስለመሆኑ በዙዎች ይናገራሉ።
በንግግር መተነኳኮስ፣ ዘመናዊነት መጥቶ ከተሞች ከመስፋፋታቸው በፊት በድሮ ጊዜ በየጫካው ከብት ሲያሠማሩ የነበሩ ዕረኞች ሲተገብሩት እንደነበር ይነገራል።
አባቶች በበኩላቸው፣ በሠርግ፣ በተዝካር፣ እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ መጠጥ ጠጥተው ሞቅታ ሲሠማቸው በአሽሙር ከመተራረብ አንስቶ፣ ዱላ እስከመማዘዝ የሚደርሱበት ኹኔታም እንደነበር ይወሳል።
እንደዛሬው ማኅበራዊ ሚዲያ ባልነበረበት ወቅት፣ እረኞች እንደ ሠብዓዊ ኢንተርኔት እንደነበሩና አንዱ ሌላኛውን በመናናቅ ፖለቲካ ይተነኩስ እንደነበር በዲላ ዩኒቨርስቲ በማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ኮሌጅ የታሪክና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተመራማሪና መምህሩ አብዱ አሕመድ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ታዲያ የፖለቲካ ብሽሽቁ በእረኞች ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሥልጣን በሚያቀኑ ገዢዎችም ጭምር እንደነበር ሲወሳ የሚደመጥ ሲሆን፣ ገዢዎች ወደ ሥልጣን ሲያቀኑ የባላባት ልጅ ካልሆኑ በንቀት ስድብ ያበሽቋቸው እንደነበር፣ አብዱ አፄ ቴዎድሮስ ተብለው የነገሱትን የካሳ ኃይሉን ታሪክ በማንሳት እንደሚከተለው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ካሳ ኃይሉ (አጼ ቴዎድሮስ) ሸፍተው በነበሩበት ወቅት የንጉሠ ዘር የሆነችውን ተዋበችን ሲዳሩ፣ የኮሶ ሻጭ ልጅ በመሆናቸው እና የሠለሞናዊ ዝርያ የላቸውም ይባሉ ስለነበር እረኞች፣
“የካሳ ኃይሉን ጉድ ስሙልኝ በሞቴ
ሚስቴ ልላት ነው ወይስ እመቤቴ” በሚል ቃላዊ ግጥም ያበሽቋቸው እንደነበር ነው።
ማኅበረሰቡ ከመሪዎቹ ሳይሆን መሪዎቻችን ከማኅበረሰቡ የወጡ ናቸው የሚሉት አብዱ፣ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሸዋና በወሎ ነገሠታት ቤተሰቦች መካከልም የፖለቲካ ብሽሽቅ እንደነበር ይናገራሉ።
እንደ ታሪክ መምህሩ ገለጻ ከሆነ፣ የሸዋና የወሎ ባላባቶች ለረጅም ጊዜ በነበራቸው የግዛት ፉክክር፣ ዳግማዊ ምኒልክ የወሎ ቤተ-አምሐራን ግዛት በፖለቲካዊ ሥልት ለመያዝ ራስ ሚካኤልን ለልጃቸው ለሸዋረገድ ድረውላቸው የነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ሸዋረገድ ሞተው ግሸን ማርያም ሲቀበሩ የሸዋ ሠው “ሸዋረገድ እንዳልነበር ሆነች
አንኮበር ተወልዳ ግሸን ተቀበረች”
ብሎ ነበር። እረኞች ደግሞ፣
“ያቺ ሸዋረገድ አንኮበር ተወልዳ ግሸን ብትቀበር፣
ግማደ መስቀሉ ባረፈበት አገር፤
ከሚካኤል ወዲያስ ባል ማን ይገኝ ነበር”
ሲሉ በፖለቲካዊ ቃል ግጥም ይበሻሸቁ እንደነበር ነው ያብራሩት።
ታዲያ ይህ ልማድ ቀስ በቀስ እየተዋሃደን የመጣ ሲሆን፣ በተለይም ዘመኑን ተከትሎ አብዛኛው ሠው እጁ ላይ ያለው ቴክኖሎጅ ዓለም ውስጥ ያለውን ክስተት በቀላሉ ለመመከት ስላስቻለው ጎራ ለይቶ መበሻሸቁና መነታረኩ እየሠፋ የመጣ ይመስላል። የጥላቻ ንግግር ማድረግ ወይም የትኛውንም ግለሰብ ሆነ ቡድንን መሳደብ በሕግ የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ ችግሩ ግን መላ ሳይሰጠው ቀጥሏል።
የተጻፈው ሕግ የሚተገበረው መቼ ነው?
በኢትዮጵያ ውስጥ የተጻፉ ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑበት ቀን መቼ ነው? የብዙኃኑ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ የተጻፉ ሕጎች ድሃ እንዳልሆነች በየወቅቱ የሚደነገጉ ሕግጋትን መመልከት በቂ ነው። ይሁን እንጂ ተፈጻሚነታቸው ግን ሕልም ሆኖ የቀረ ስለመሆኑ አገሪቱ አሁን ላይ ያለችበት ሁኔታ በቂ ምስክር ነው።
ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሕግ ድንጋጌ ጀምሮ እስከ ኹሉም የዕምነት ተቋማት ድረስ የተጻፉ ሕጎች በርካታ መሆናቸው ይታወቃል። በኃይማኖት በኩል የአንዱን ዕምነት ከሌላኛው ዝቅ አድርጎ ማየት የትዕቢት ምልክት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲሰበክ ይስተዋላል። ነገር ግን፣ ፕሮቴስታንቱ ኦርቶዶክስን፤ ኦርቶዶክስ ፕሮቴስታንቱን፤ ኦርቶዶክሱ ሙሰሊሙን፣ ሙስሊሙ ኦርቶዶክሱን፤ ከፍ ወይም ዝቅ አድረጎ በማየት የኔው ይበልጣል በሚል ትዕቢት ተወጥሮ የፉክክር መድረክ በመክፈቱ መከፈፋልና አለመግባባቶች መስተዋል መጀመራቸው ሠንበትብት ያለ እውነት ነው።
በሕገ መንግሥቱ በኩል ስንመልከት፣ ሕግጋት ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ በመባል ተሰናስለውና ፍንትው ብለው ተቀምጠዋል። ኃይማኖትና ብሔር ላይ ያተኮረ ጥቃት መሸንዘር በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በጥብቅ የተከለከለ ድርጊት ቢሆንም፤ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የወለጋ አካባቢዎች፣ በመተከል ዞን፣ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ባሉ ዜጎች ላይ ብሔራቸውና እምነታቸውን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከመሠንዘሩ በፊት የውስጥ ለውስጥ የብሽሽቅ ፖለቲካዎች አስተናግደዋል።
አማራና ትግሬ በጋብቻ የተሳሰረ የአንድ አገር ዜጋ ሆኖ እያለ፣ አንድነቱን ከመዘንጋት አልፎ ወደ ለየለት የመገዳደል አሳፋሪ ተግባር ከመግባቱ በፊት፣ አክቲቪስቱ በመድረኩመ ተከታዮቻቸው በግል በይነ መረባቸው በርካታ የፖለቲካ ብሽሽቅን አስተናግደዋል።
ነገር ግን፣ መስረቅ ልማድ ከሆነበት በኋላ ስለስርቆት መጥፎነት እናቱ ስትነግረው “በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” እንዳለው ልጅ፣ የጥላቻ ንግግሩ በሕግ ሳይዳኝ በዝምታ መታለፉ አንድነትን ከማጥፋትም አልፎ እርስ በርስ ለመገዳዳልም እንዳበቃን የአሁኗ ምስቅልቅል ኢትዮጵያ ትመስክር።
ሕግ የሚጻፈው አገርም ዜጋም ሠላም እንዲሆን ቢሆንም፣ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የራስ የሆነን ጉዳይ ከፍ የሌላውን ዝቅ በሚያደርግ የጥላቻ ንግግርና ብሽሽቅ አብዛኛው ሠው ወገን መያዙ ለሠላም መደፍረስ እንዳበቃን ብዙዎች እየተናገሩ ነው።
የፖለቲካ መበሻሸቅ ለአሁኗ ኢትዮጵያ
ለአሁና ምስቅልቅል ላለችው ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካው መበሻሸቅ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ቀድመው ተረድተው እንደበርና ክስተቱ እንዳይፈጠር ምክራቸውን ለግሰው እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ይህ ቀስበቀስ እየተለመደ የመጣው የፖለቲካ ብሽሽቅ፣ “በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ያለው የኢሕአዴግ አንጃ ሕወሓትና የብልጽግና አመራሮች እየተከተሉት ያለው የብሽሽቅ ፖለቲካ፣ ወደ ማንወጣው ጦርነት ሊከተን እንደሚችል፣ ከኹለት ዓመት በፊት ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ውይይት አድርጌበት ማኅበረሰቡ እንዲያየው አየር ላይ አልዋለም‘” የሚሉት አብዱ አሕመድ ናቸው።
አክለውም፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደጋግመው የፖለቲካ ብሽሽቁ ይቁም ቢሉም፣ ከሕወሓትና ከብልጽግና በኩል የሚሠነዘረው የጥላቻ ንግግርና የፖለቲካ ብሽሽቅ አሁንም እንዳልቆመ ነው የገለፁት።
ታላቅ ለታናሹ፣ መሪው ለተመሪው አርዓያ መሆን እንዳለበት የሚታመን ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ግን በተቃራነው በመሆኑ ወደ ጦርነትና መከፋፋል ለመግባት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው።
ይህን በተመለከተም አብዱ መሪዎቻቻን ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ባልሆኑበት አገር ውስጥ፣ ብሽሽቅ ታች ወርዶ ወጣቱ አድዋን፣ ካራማራን አስመልክቶ መበሻሸቁ የሚገርም እንዳልሆነ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህ ድርጊት የኋላ ቀርነታችን መገለጫ ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ብሽሽቅ አንዱና ዋነኛው መገለጫው እኔና የኔ ብቻ ይሁን ማለቱ ላይ እንደሆነ የሚነገሩት አብዱ፣ ችግሩ እንዲቀረፍ ከተፈለገ ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ዜጋ የአስተሳሰብ ለውጥ ያሥፈልገዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አስከትለውም፣ አውሮፓውያን ለአምስት ዓመት የአስተሳሰብ አብዮት ላይ እንደሠሩ የጠቆሙ ሲሆን፣ የተሻለ የፖለቲካ አድማስ ይኖረን ዘንድ ኢትዮጵያውያንም የተሻለ የአስተሳሰብ አብዮት እንደሚያስፈልገቸውና ይህ ካልሆነ ግን በወቅቱ እየተስተዋለ ያለው የፖለቲካ ብሽሽቅ ወደ ተጨማሪ ጦርነት ሊያመራን እንደሚችል ነው የተገነዘቡትን የተናገሩት።
ለ500 ቀናት በጦርነት ውስጥ ቆይተናል የሚሉት አብዱ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በአጼ ዮሐንስና ምኒልክ ቤተ-መንግሥት የተቀመጡት ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ከመወያየት ይልቅ ወደፖለቲካ ብሽሽቅ ማምራታቸው ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግር ከሕጉ አንጻር
የጥላቻ ንግግርን በድምፅ፣ በጽሑፍ፣ በምስል እንዲሁም በሌሎች የመልዕክት ማሠራጫ መንገዶች ማስተላለፍ በሕግ የተከለከለ ስለመሆኑ በዘርፉ ምሁራንና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል ።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማንኛውም ሠው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካካት በጽሑፍ፣ በቃል፣ በምስል፣ እንዲሁም በሌሎች የሐሳብ ማሠራጫ መንገዶች የማስተላላፍ ሙሉ መብት ቢኖረውም፣ በሕግ የሚገደብበት ደረጃ ግን አለው የሚሉት የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ናቸው።
ማንኛውም ሠው የማይጣስና የማይገረሰስ መብት ባለቤት ቢሆንም፣ ከመብቱ ጀርባ የተሰካ ግዴታ መኖሩ የሚታወቅ ነው። የሕጉ ተፈጻሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላላ በመምጣቱ ብዙዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ አለ እንዴ?” ሲሉ ይደመጣሉ።
ከንግግራቸው መረዳት የሚቻለው የተጻፈ ሕግ ቢኖርም፣ በተግባር የተገለጸ ተፈፃሚነት ከሌለው ሕግ አለ ብሎ ለመናገር እንደማያስችል ነው። የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃን በተመለከተ የሕግ ባለሙያው ካፒታል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ፍንትው ብሎ ራሱን የቻለ ገደብ ያለው ስለመሆኑ ነው።
የሕግ ባለሙያው አስከትለውም፣ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትንና የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ በ2012 የፀደቀ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ተብሎ ሕግ ተቀምጧል ነው ያሉት።
የጥላቻ ንግግር በየትኛውም የመልዕክት ማሠራጫ መንገድ እንዳይተላለፍ ሕጉ ቢገድብም፣ መሬት ላይ እየሆነ ያለው ሃቅ ግን በተቃራኒው ስለመሆኑ በ2014 የተፈፀሙ የለየላቸው የጥላቻ ንግግሮችና ምስሎችን መለስ ብሎ መመልከት በቂ ነው።
ለአብነት ያህል ብናነሳ አንኳ በ2014 የካቲት 23 የተከበረውን የአድዋን በዓል ማስታወስ የሚቻል ሲሆን፣ በበዓሉ በበርካቶች በኩል የጥላቻ ንግግሮችና ተግባሮች ሲከናወኑ ተስተውሏል።
በሌላ በኩል፣ በ2014 በተከበረው የጥምቀት በዓል ወቅት፣ ሠንደቅ ዓላማ ለምን ያዛችሁ በሚል ሠበብ ብዙ ትርምሶችና ጥፋቶች ተስተውለው ነበር። ይህ በመሆኑም፣ አሁን አሁን አንዱ የሌላውን ባህልና ታሪክ በማክበር በዓላትን ያለመነቃቃፍ ማክበር እየተዘነጋ የመጣ ይመስላል። የጥላቻ ንግግር ማለት በግለሰብ ወይም በተደራጀ ቡድን አማካይነት ብሔርን፣ ዘርን፣ ፆታን፣ ባህልንና የመሳሰሉትን መሠረት በማድርግ ጥቃት መሠንዘር፣ ዝቅ የሚያደርግ ንግግርን መናገር መሆኑን የሕግ ባለሙያው ካፒታል ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
የጥላቻ ንግግር የሚያስቀጣ መሆኑ በሕግ ይቀመጥ እንጂ፣ ተፈጻሚነቱን ችላ ያለው ታች ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ አገርን መምራትና ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት ያላቸው ባለሥልጣናትም ጭምር ናቸው።
ለአብነት ብንጠቅስ እንኳ በሕወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተፈጠሩት አለማግባባቶች ጥፋተኛ የሆነን አካል በሕግ መጠየቅ እየተቻለ የጥላቻ ሥም ሲሠጣጡ ተስተውሏል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሕወሓት መሪዎችን “የቀን ጅብ፣ ጁንታ” የሚል ሥያሜ ሰጥተዋቸዋል። ምንም እንኳ የሕወሓት ግብር ከዚህም በላይ ያስብላል ብሎ መከራከር ቢቻልም፣ ከፍትሕ አንጻር ሲታይ ግን ትክክል እንዳልሆነ የተደነገገው ሕግ ይመሰክራል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



