ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲታወሱ!

0
1493

የንጉስ ሃርቤ ውጥን አራተኛው ስኬት ፤የብዙ አባቶች ተጋድሎ በረከት፤ የብስና የባህር እንባ፤ የዓባይ ወንዝ ፖለቲካ ማሰሪያ ገመድና የረጅም ዘመን ትግል ውጤትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ዘላለማዊው ቤታቸው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ተጠርተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 111 ግብጻውያን ሊቃነ ጳጳሳትን በታሪኳ ተቀብላለች። እነሱም በተራቸው ብዙ ቢያስተምሩም በልዩ ልዩ ምክንያት ጥቂት አስመርረዋል።
ይህ ፕትርክናና ጳጳስነትኮ ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፈሌ!
‹ንጉስ ሳይኖራቸው ሶርያና አርመን፤
መርጠው ይሾማሉ ባትርያርክና አቡን፤
ከወገኑ መርጦ ጳጳስ የማይሾም፤
ከጦብያችን በቀር ሌላ ሕዝብ የለም›
የሚል ሙሾ ያወረዱለት ነው።

ፕትርክናው፤ ገና ጥንት ቅዱስ ሃርቤ የተሟገቱለት፤ ረሃብና ጥም፤ መቀማት፤ በሽፍታና የዱር አውሬ እጅ መገደል፤ ዓባይ የበላቸው ብዙዎች ዲቁናና ቅስና ለመሾም የተንከራተቱበት፤ ብሔራዊ ታናሽነት የተገታበት፤ ወግ አጥባቂነት የተሰበረበት፤ የክርስትናን እኩልነት ያረጋገጠ፤ የዘር ልዩነት የቆመበት፤1600 ዓመታት የኮፕት ‹ግብጽ› ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አለቅነት የተገረሰሰበት፤ የትውልድ ቅብብሎሽ ትግል ውጤት፤ ከኢትዮጵያና ግብጽ አልፎ እስራኤልን ለገዳማት ይዞታ ያጨቃጨቀና ያወዛገበ፤ በቫቲካን ለመሳለሚያና ማረፊያ የተፋለመ፤… የተከበረ ክቡር ነው።

የኢትየጵያ ቤተ ክርስቲያን ግሪካውያኑም፣ የመናውያኑም፣ ግብጻውያኑም፣ አርመናውያኑም፣ ሶርያውኑም፣ ሊብያውያኑም፣ እስራኤላውኑም ብዙ ዓለማት ላይ ያሉ ዜጎች በሙሉ ዛሬም አብረው ያለልዩነት ያመለኩበት ቤት ነው።

ባለፉት ስድሳ ኹለት ዓመታት ውስጥ ‹የኢትየጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ ከሾመችበት ግዜ ጀምሮ› ፤ የአባቶች አባት፣ ልዩው፣ ብቸኛው ያርምሞው ፓትርያርክ፣ አገር ውስጥም ከአገር ውጭም ያበቱቱ ‹አባት የሆኑ›፤ በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ የተሾማባቸው፤ አንድነትንም ልዩነትንም የኖሩትና ያነበቡቱ በመጨረሻም ያረመሙቱ፤ ዓለምንም ፖለቲካንም የታዘቡቱ ዕንቁ፤ የዓባ ኣጋቶኑ ልጅ፤ በሕይወታቸውም በሥራቸውም በምልሰትም በጉዞም፤ አገር ውስጥም በማዕዶትም መንፈሳዊነቱን ያጸኑቱ፤ በተወለዱባት፣ በተማሩባት፣ በተሾሙባት፣ ከተሰደዱባትና ተመልሰው በተባረኩባት በዘመድ አዝማድ፣ በመንፈስ ልጆቻቸውና በወዳጆቸችው አብረዋቸው ባገለገሉዋቸው አባቶች ጭምር ታጅበው፤ በእናት አገር ምድራቸው ኢትዮጵያ፤ በኖሩቱ በመሰሉቱ፤ በሰማዕቱ በቅዱስ መርቆሬዎስ መታሰብያ ዕለት የካቲት 25፣2014 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም በሠላም ዓርፈዋል። መርቆሬዎስሰ መርቆሬዎስ ውእቱ ማለት ይህ ነው።

ኦርቶዶክሳውያንም ዐራተኛውን ፓትርያርክ ለመሰናበት መጋቢት 3ና4/2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል። በግብጻዊው ቅዱስ አቡነ ገብረ መንፈሰ ቅዱስ ዓመታዊ ክበረ በዓል ዋዜማ! የቀደሙ አባቶቻቸውን ፓትርያርኮቹን ቀዳሚውን አባ ባስልዮስን፤ ሰማዕቱን አባ ቴዎፍሎስን፤ መንፈሳዊውን አባ ተክለ ኃማይኖትን፤ አወዛጋቢውን አባ ጳውሎስን ተከትለው ግብዓተ መሬታቸው ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ አርምሞ የተለመደ፣ በምዕመኑም ጭምር የሚተገበር፣ በገዳማይውኑ ደግሞ የሠርክ የሆነ ተግባር ቢሆንም፣ ከኃላፊነቱም ከብዙ ነገሮች አንጻርም በታታላቆቹና የአስተዳደር ኃላፊነት ባለባቸው አባቶች በተለይ በፓትርያርኮቹ ሲዘወተር ብዙም አይታይም ወይም ለኛ አልገለጡልንም። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ግን ይህን አድርገውታል። ከባዱንም ‹እሳት› አሸንፈውታል። ምላስ አገር ባጠፋበት ዘመን፣ በዝምታ በአርምሞ በሥጋ ዓይን እኛን ምን ያህል ታዝበውን ይሆን? በነገራችን ላይ ከሦስቱ ታላላቅ የመንፈሳዊ ብቃት ማዕረጋት አንዱ ከሆነው አንዱ ንጽኃ ሥጋ ነው። የንጽኃ ሥጋ መገለጫ ከሆኑት ደግሞ አንዱና የመጀመሪያው ጽማዌ ይባላል። ይህም ከአንደበት የሚወጣን ኃጢዓት መግታትና ብዙ አለመናገር ነው። አሳቸው ይህን ከባድ ፈተና ተቋቁመው አልፈውታል።

ኹለተኛም፤ መቼም ሠው ተገዶ አገሩን አይለቅም፤ እንዲሁም አይሰደድምና አገር ውስጥም ከአገር ውጭም በተፈቀደላችወ መጠን ያስተማሩ፣ በስደት ምክንያትም ለፈተና የተጋለጡ፣ በዚያም ምክንያት ስንጥቅ የፈጠሩ ብቸኛው ፓትርያርክ ናችው። እስከ አሁን በሚያስቆጭ መልኩም ያለ ሕማምና ድካም፣ በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ በመንበራችው ላይ የተሾመባቸው አባትም ናቸው።

ክርስትና ፈተና ብቻ ሳይሆን ዕርቅም ይቅርታና ድልም ነውና የአገር ውስጡንና ገለልተኞቹን እንዲሁም የስደተኛውን ሲኖዶስ እንደ ጥንቱ ወደ አሐቲነት መልስዋል፤ በስተ ዕርግና። ከስደት መልስም የልዩነት ምክንያት ባለመሆን ከፍ ያለ አስተዋጽዖ አበርክተዋል። በአንጻሩም የፖለቲካው ትኩሳት ረመጡ ቢኖርም፣ እንዲህ እንደ ዛሬው ባልጦዘበት ዘመን፣ ከስደት መልስ የጵጵስናቸውን ጥንት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲንያንንም መሳለም የተከለከሉ አባትም በመሆናቸውም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አይረሳቸውም።

የሚያስቆጨው ደግሞ፣ ከራስ መነቀል ዘመናዊነት በመሰለበት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጎላ ፈተና በተጋረጠባት፣ ካህናቷ በቤተ መቅደስ ፊልም በሚመስል መልኩ በሚታረዱበት፣ አብያተ ክርሰቲያናትን ማቃጠል የሠርክ ዜና በሆነበት፣ የክልል ቤተ ክህነቶች በፖለቲካ ካባ በተላኩበት፣ ማተብ በሚያስቀስፍበት፣ ኦርቶዶክሳዊ ክብር ውርደቱ ጥልቅ በሆነበት፣ መንፈሳዊነት ‹መንፈሳይነት› በሆነበት፣ ወጣቱ በሚሰደድበት፣ የተቀናጀ ጥቃት በተሰነዘረበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም በተግባርም ዘመንን ባለመዋጅትም አንገት የሚያስደፋ ታሪክ በሚሰራበት፣ ልጆቿ ምዕራፍ አንድ ላይ በወደቁበት፣ ህልውናዋ ታሪካዊ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት፣ የታላላቅ አባቶች ምክርና ተግሳጽ እጅጉን በሚያስፈልግበት፣ በዚህ ወቅት መርቆሬዎስሰ መርቆሬዎስ ወደ ጠሪያቸው መጠራታቸው ነው።

ከኋላ የተሾሙቱ፤ በልዩነትም በዕርቅም የተባበሩቱ፤ የአንድ መንበር ልጆች የሆኑቱና የአባ ሰላማና የአባ ተክለ ኃይማኖቱ ስድስተኛው ፓትርያርክ፣ የሠፈራቸው ሠዎች በሠውኛ እሳቸውን በሚጎተጉቱበት፤ የቤተ ክርስቲያን ፈተናው ሠማይ በነካበት፣ ባልተለመደ መልኩ በዚህ ዘመን ብዙ ብፁዓን አባቶች ያሳረፉቱ፣ በአካለ ሥጋ ያሉቱ ፓትርያርክና ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወመንበረ ተክለ ኃይማኖት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ታላቃቸውን፣ ኹለተኛ ሆነው የተሾሙበትን ‹4ኛና 6ኛ ናቸውና› አባት በክብር ሲሸኙ ምን ይሠማቸው ይሆን?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት የራሷን ሊቀ ጳጳስ ለመሾም እንደ በቃችና የተደረገውን ትግል የዶ/ር ውዱ ጣፈጠን ‹The Ethiopian Orthodox Church: The Ethiopian State and the Alexandria see, indigenizing the Episcopacy and Forging National Identity, 1926-1991› እና የአዱኛ አመኑን ›The Ethiopian Orthodox Church becomes Autocephalous, 1969› ማንበብ ይጠቅማል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here