‹ጠብ ለኩሱ› ግብዣ

0
857

ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ሚድያዎችንም ሳይቀር በብዙ እንድንታዘብ ያደረጉን ክስተቶች ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት ውስጥ አልፈዋል። በሚድያው ዘርፍ ፊተኞችና ኋለኞች ናቸው ብለን እንገምታቸው የነበሩ ዓለማቀፍ ተቋማት፣ የኢትዮጵያን የጦርነትና አለመረጋጋት ጉዳይ የዘገቡበትን መንገድ ስንመለከት ‹ውይ! እንዲህ ኖራችኋል ለካ!› ብለን ብዙዎቻችን አዝነንባቸው ነበር።

ይልቁንም ቀና ቀናውን ትተው ድክመትና ውድቀትን መርጠው የሚያሳዩት ነገር፣ ‹ግጭት አነሳሽ› ብለው ያሻቸውን ጥለው የተመኙትን ለብዙኀን የሚያደርሱበት መንገድ ትዝብታችን ውስጥ ከቷቸዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙና አስቀድሞ ‹ምነው እንደ ቢቢሲ እና ሲኤንኤን ብትዘግቡ!› እያሉ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ቅሬታ ያቀርቡ የነበሩ ተቺዎችም፣ ‹እንኳንም ቀረብን! ፍትህና እውነት እንዲህ ነው እንዴ!› እንዲሉ ገፋፍቷቸዋል።

የጥላቻ ንግግር ጉዳይ የተነሳ እንደሆነ ደግሞ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀኑ እነፌስ ቡክ፣ እነ ትዊተር መቀመጫቸው ያለበት አገር ፖለቲካን እያደመጡ፣ ያንን መሠረት አድርገው ያሻቸውን ሲዘጉና ሲከፍቱ ከርመዋል። እንዲያም ሆኖ ለእውነት ቆምን፣ የጥላቻ ንግግርን ተቃወምን ይላሉ እንጂ አንዳች እንዳጠፉ ተሰምቷቸው አያውቅም። አቤት ጨዋነት!

አሁን ታድያ ከሳምንት የተሻገረው የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ፣ እነዚሁ አካላት ዘገባቸውና መልዕክታቸው ዓላማው በግልጽ ታየ። ብዙ ችግሮች አሉባት፣ ሥልጣኔ ይቀራታል የተባለችው አፍሪካ ላይ የበረቱት፣ ሁሉም የእነርሱ ስለነበርና ስለሆነ እንጂ ታማኝ ሆነው አልያም ለእውነት ተቆርቁረው አልነበረም።

‹ለካ አልተያየንም!› ይሏል እንዲህ ነው። በቅርቡ ማኅበራዊ ሚድያዎች ‹ከፈለጋችሁ ለተወሰነ ጊዜ የጥላቻ ንግግር እንድታደርጉ ፈቅጃለሁ› የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ይህም ሩስያን የጋራ ጠላት አድርጎ በመሣሪያ ካልሆነ በሥነልቦና እና በሐሰተኛ መረጃ ጦርነቱን እንቀላቀል የመሰለ ውሳኔ ነው።

በእርግጥ ይህ ጦርነት ሠለጠንን የሚሉ ማኅበረሰቦች ወይም መንግሥታት ምን ያህል ዘረኝነት ከደማቸው እንደተዋሀደ የታየበት ክስተትም ነው። ማኅበራዊ ሚድያውና መደበኛ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀኑ ደግሞ ይህን እውነት፣ የራሳቸውንም ደካማነት አጉልተው ዐሳይተዋል። እንግዲህ ነገሩ በእጅጉ የሚያሳዝንና እንዳሰብነው ወይም እንደምንገምተው ‹ሠለጠኑ› የምንላቸው አገራት ገና ብዙ መሠረታዊ ጉዳይ እንዳልገባቸው የሚያሳይ ሆኗል።

በእርግጥ በአንድ ጎን ጉዳዩ አፍሪካንም ሆነ በተለይ ደግሞ ከአፍሪካም ኢትዮጵያን እረፍት የሰጣት ይመስላል። አዲስ አጀንዳ ስላገኙና በዛ ላይ እየተርመሰመሱ በመሆኑ፣ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነትም ሆነ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይን ‹ይቆየን› ብለው በይደር አስቀምጠዉታል።
ከሁሉ ግን በተለይ የማኅበራዊ ሚድያው ጠብ ለኳሽና አጫሪ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮችን ለጊዜው ብሎ መፍቀዱ ለታሪክም አስገራሚ ጉዳይ ሆኖ ይዘልቃል። እንግዲህ ስድብን መርቆ እንደመስጠት ነው። የምን እየተሽሎከሎኩ መሳደብ፣ ይኸው በግብዣና በፈቃድ!


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here