የግብርና ዘርፍ ልማት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት በበርካታ ተቋማዊ ችግሮች የተተበተበ ነው። ይልቁንም ወጥነት ያለው የጥሬ ዕቃና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ሰለባ በመሆኑ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ ሆኗል። ሽመልስ አረአያ (ፒኤችዲ) ይህን ነጥብ በማንሳት በተለይም አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች የገጠማቸውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለማቃለል ቢሄዱበት ያሉትን መንገድ አመላክተዋል።
አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ከግብርና እንዲጀምር ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሦስት ዐስርት ዓመታት በፊት ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ነድፎ ነበር። ብዙ ባለሙያዎች የተበታተነ የመሬት ይዞታ በመጠቀም የግብርና ልማት ማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋገሚ የሚገልጹ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግብርና መር ፖሊሲ ሁነኛ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም። ይኸውም ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር የሚኖርና ግብርና ዋነኛ የኑሮ ምንጩ በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢው በዋናነት በግብርና ምርቶች ላይ የተንተለጠለ ነው። እናም ዘርፉ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ግድ ነው።
እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ከግብርና ልማት ስትራቴጂው ውጪ ሌላ አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫ ሊኖረን ይገባ ነበር ብሎ መገመት ከባድ ይመስላል። ከሌሎች አገራት ተሞክሮ አንጻርም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት መሰረት ለመጣል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ወይም ልማት ማስመዝገብ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የግብርና ዕድገት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የፋይናንስና የገበያ እድል በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎም ታስቦ ነበር። በዚህም መሠረት የግብርና መር ስትራቴጂው የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው አገራት ልምድና ተሞክሮ የተወሰደበት ነበር።
ዛሬ በእስያ የበለጸጉ ኢኮኖሚዎችን የሚያንቀሳቅሱት የእድገት ሂደታቸው ተመሳሳይ እንደሆነ ተጠቅሷል። ጃፓን በ19ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኮሪያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን እና ቻይና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁሉም በግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ኢኮኖሚያቸውን ቀይረው ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረዋል። ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ሲሄድ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ይረዳል። የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለጥሬ ዕቃ የገበያ መዳረሻዎች ማበርከት ብቻ ሳይሆን ለግብርናውም እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የተሻሻሉ ግብአቶችንም ያቀርባል።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሳደግ በ2025 የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የመሆን ርዕይን እውን ለማድረግ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን እንዲመጣ እየተጋች ትገኛለች። የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንደስትሪ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ከማረጋገጡ በተጨማሪ በዚህ መዋቅራዊ ሽግግር በሚያስፈልግበት ወቅት ተስፋ የሚጣልበት ዘርፍ ነው።
የአግሮ ፕሮሰሲንግ-ኢንዱስትሪ ልማት የሥራ እድልን በማበረታታት፣ ለኢንተርፕራይዝ ልማት አስተዋፅዖ በማድረግ እንዲሁም የገጠር ልማትን በማፋጠንና ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በአገር ውስጥ ተመርተው ወደ ገበያ እንዲቀርቡ (import substitution) በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ለዚህም በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች (Integrated Agro Industrial Parks) ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶት የግብርና እሴት ሰንሰለት ተዋናዮችን በማቀናጀት የግብርና ምርትን ወደ ገበያነት ለማምጣት ያለመ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
በመሆኑም የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ሽግግር አጀንዳ ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል። የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ዋና ዋና የግብርና ምርቶችን ወደ ከፊል በመቀየር እና ያለቀላቸው እቃዎች በማምረትና እሴት በመጨመር በውድ ዋጋ ለመሸጥ የማምረት ልምድ ነው። በዚህም መሰረት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ልማት በድሆች ኑሮ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፤ የሥራ እድልን በመጨመርም ሆነ ለግብርና ምርቶች የገበያ ተደራሽነት እድል በመፍጠር የግብርናና የኢንዱስትሪው ትስስር የጠበቀ ያደርጋል።
በኢትዮጵያ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ ከፍተኛ መሻሻል ቢታይም ዘርፉ በዚህ የመነሻ እድገት ደረጃው ላይ የገጠሙት ፈተናዎች አሉ። የግብርና ኢንዱስትሪ ልማት በብዙ የአፍሪካ አገራት በበርካታ ተቋማዊ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም በተለይም ወጥ የሆነ የጥሬ ዕቃና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ሰለባ በመሆኑ በተፈለገው ልክ እንዳያድግ እንቅፋት ተደቅኖበታል። እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የተሰማሩ የአግሮ ፕሮሰሲንግ አንቀሳቃሾች ብዙ ጊዜ የተሻለ ጥራት ያለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ስለሚያጋጥማቸው በሙሉ አቅማቸው ለማምረት እንቅፋት እንደሆነባቸው ደጋግመው ይጠቅሳሉ።
በተጨማሪም ይህ የጥሬ ዕቃዎች እጥረት ጊዜያዊ ባለመሆኑ ለፓስታ፣ ማካሮኒ እና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ በመመደብ ስንዴና ጥጥ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን መንግሥትም ደጋግሞ ሲገልጽ ይሰማል።
ሌላው ብዙ ጊዜ በአርሶ አደሩ እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በተሰማሩ አካላት መካከል ያለው ትስስር እጅግ ደካማ በመሆኑ የተነሳ አርሶ አደሮች በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የሚፈለገውን ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ እቃ በማምረት ረገድ ያላቸው እውቀት እጅግ ውስን ነው። በእነዚህ ውሱን ትስስሮች አርሶ አደሮች ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ፣ የተሻለ ጥራት ባላቸው የግብርና ግብአቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ወይም ጥሩ የግብርና ልምዶችና አሰራሮችን እንዲከተሉ አያበረታቱም። በተጨማሪም ደላሎች ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩ በልውውጥ ሂደት ውስጥ ስለሚሳተፉ ይህም በአቅርቦት ሰንሰለቱ ቅልጥፍና ማነስ የላቀ ሚና አላቸው።
በኢትዮጵያ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ለብዙ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ማነቆ እንደሆነ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ስለሆነም አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ዘላቂና ያልተቆራረጠ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዲኖራቸው አማራጭና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ማጤን አለባቸው። ለምሳሌ በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚገኙ ዋና ዋና የምግብ አቅራቢ ሱፐርማርኬቶች እና በግብርና ንግድ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የግብርና ምርቶችን በራሳቸው እርሻ ያመርታሉ አልያም በቀጥታ ከገበሬዎች ማሳ ሸምተው ለተጠቃሚው ያቀርባሉ። የግብርና ኩባንያዎቹ እና አርሶ አደሩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ወይም ጥሬ ዕቃዎችን ያለምንም የአቅርቦት መቆራረጥ ወደተጠቃሚው እንዲደርስ ለማረጋገጥ የውል ስምምነት (Contractual agreement) ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ አሰራር አሁን አሁን በተለያዩ አገራት የተለመደ ሲሆን የኮንትራት ግብርና (Contract Farming) በመባልም ይታወቃል። የውል ስምምነቱ ኩባንያው ለአርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያመርት የሚያቀርበውን የግብርና ግብአቶች፣ የግብርናው ምርት የሚሸጥበት ዋጋ፣ የክፍያ ጊዜውን፣ የማሳ ቁጥጥርን ደረጃ እና የመሳሰሉትን ሊያካትት ይችላል።
በግብርናው ምርት በማምረት ሂደት ላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲሰበሰብ ተጽዕኖ የማሳረፍ (supervision) ስምምነት፣ ስጋቶችን መጋራት እና በውሉ ውስጥ የሚካተቱትን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ በርካታ የውል ዓይነቶች ተለይተው ይታወቃሉ። ለምሳሌ በምርት ሂደት የሚኖሩ የቁጥጥር መጠን ወይም የውል ስምምነቱ ዋና አንኳር ጉዳይ አንጻር ኮንትራቶች በሦስት ምድቦች የሚከፈሉ ሲሆን፤
(1) ገበያ ተኮር ኮንትራቶች፡- እነዚህ ኮንትራቶች ሙሉ በሙሉ በግብይት ሁኔታዎች ላይ ያተኩራሉ። በመሆኑም የኮንትራት ስምምነቱ ኩባንያው ምን ያህል እንደሚከፍል እና የሚከፈልበትን የጊዜ ሰሌዳ ይገልጻል።
(2) የግብዓት አቅርቦት የተካተተባቸው ኮንትራቶች፦ እንዲህ አይነት የአግሪ-ቢዝነስ ኩባንያ የምርት ግብዓቶችን የተወሰኑ ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ያቀርባል። በእርሻ ማሳ ዝግጅትና ሰብሉ እስኪሰበሰብ ድረስም በማሳው ላይ ክትትል ያደርጋል።
(3) የገቢ ዋስትና ኮንትራቶች፡- እነዚህ አይነት ኮንትራቶች ብዙውን ጊዜ የቀድሞዎቹ ሁለት ኮንትራቶች የምርት እና የግብይት ድንጋጌዎችን ያካትታሉ። የገበያ እና የዋጋ ስጋቶች ከገበሬው ወደ ኩባንያው በዚህ ውል ይተላለፋሉ። በሌላ በኩል፣ ኩባንያው ሙሉ የሥራውን ሂደት ክትትል የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ይወስዳል።
በኮንትራት ግብርና ውስጥ የገበሬው ተሳትፎ ስለሚኖረው ውጤት በሚመለከት የተለያዩ ተቃርኗዊ አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ። የፖለቲካል ኢኮኖሚስቶች በግብርናው ዘርፍ ያለውን የእኩልነት እጦት ችግር የበለጠ የሚያባብስ እንደሆነ ስጋታቸውን ያንጸባርቃሉ። ይኸውም ኩባንያዎች በስምምነቱ ታግዘው ገበሬዎችን የበለጠ ይበዘብዛሉ ከሚል ስጋት የመነጨ ነው። በተቃራኒው የተቋማዊ ኢኮኖሚስቶች (Institutional economists) የገበያ ውድቀት ችግሮችን በመፍታት ረገድ የኮንትራት ግብርና ያለውን ሚና በአወንታዊነት ያነሳሉ።
በመሆኑም አነስተኛ ገበሬዎች የገበያ ተሳትፏቸውን የሚገታውን ከፍተኛ የግብይት ወጪ (Transaction cost) ተግዳሮቶችን እንዳይጋፈጡ ይረዳቸዋል ይላሉ። በአጠቃላይ ለሁሉም ተመራጭ የሆነ የኮንትራት ዲዛይን ተግባራዊ በማድረግ በዚህም በዋናነት የገበሬዎችን ፍላጎት ከመነሻው ጀምሮ የሚያካትት ግልፅ እና አስገዳጅ የውል ዝግጅት ለሁለቱም ተዋዋዮች ውሉን ለማክበር እንዲያስገድድ እና የተዋዋዮችን ባህሪ ለመቆጣጠር እንዲያመች ተደርጎ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ በተለያዩ አገራት ውጤታማ የሆኑ የግብርና ኮንትራት ስምምነቶችንም በመዳሰስ ግልጽነት የተንጸባረቀበትና ለሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች ጥቅም የሚያስጠብቅ ውል ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የኮንትራት ግብርና ስምምነቶች የሚመለከቱ አንዳንድ አሠራሮች አሉ፤ ግን ያልተሟሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴርም የኮንትራት ግብርና አዋጅ ዝግጅት ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኮንትራት ግብርና ቀደም ሲል በብዙ ተዋዋይ ወገኖች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲፈረም የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን የሚረቀው ሕግ በሁሉም ዐይን ሕጋዊ ያደርጋቸዋል ማለት ነው። በዚህ አዲስ አሰራር ተጠቃሚ በመሆን አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ኩታ ገጠም የሆኑ መሬቶቻቸውን በማቀናጀት የሚፈለገውን የጥሬ ዕቃ ጥራቱን በጠበቀ አግባብ (በኮንትራት ግብርና ውሉ ላይ እንደተመለከተው) ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ያለምንም የአቅርቦት መቆራረጥ ማቅረብ ይችላሉ። ይህም የግብርና ግብይትን የሚያሳድግ ሲሆን ለአርሶ አደሩም ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ያስችላል።
ይሁን እንጂ ይህን አሰራር ውጤታማ ለማድረግ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ብዙ ዓይነት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ከላይ እንደተገለፀው አርሶ አደሮች ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ጋር ያለው ትስስር ዝቅተኛ በመሆኑ እና በሌሎችም ባለባቸው ክፍተቶች የተነሳ ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎች እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች በቀጥታ በማቅረብ ላይ አይደሉም። የብድር እጦት አርሶ አደሮች በእነዚህ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ካስገደዱ ወሳኝ ምክንያቶች አንዱ ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ገበሬዎች እነዚህን ጠቃሚ ቴክኖሎጂዎች ላለመጠቀማቸው በምክንያትነት ከሚጠቅሱት መካከል አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ነው። የወቅቱ ቴክኖሎጂ የደረሰበት ደረጃ በሚመጥን መልኩ ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች (GMOን ጨምሮ) በማምረት እጥረቱን እንዳይቀርፉም የሚዲያው ጩኸት አይጣል ነው።
በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ባንኮች (በዋናነት ከተቋቋመበትም ተልዕኮ አንጻር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ) የገበሬ ማኅበራት ለመመሥረት ፈቃደኛ የሆኑ አነስተኛ አርሶ አደሮች የኩታ-ገጠም መሬቶቻቸውን በማሰባሰብ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚሆን ጥራቱን የተረጋገጠለት ጥሬ ዕቃ በማምረት በዘላቂነት ለማቅረብ ውል ማሰር የሚፈልጉትን ወይም ፈቃደኛ የሚሆኑትን ከአካባቢው አስተዳደር እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን የኢንቨስትመንት ፋይናንሲንግ እገዛ ማድረግ አንዱና ዘላቂው መፍትሄ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ብቻ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች የገጠማቸውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ማቃለል ይችላሉ። በዚህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ትስስር በማጠናከር መዋቅራዊ ሽግግሩ ትርጉም ይኖረዋል።
ሽመልስ አርአያ (ፒኤችዲ) በኢኮኖሚክስ የሦስተኛ ዲግሪ ከጀርመኑ Justus Liebig University (JLU) Giessen ሠርተዋል። ጸሐፊውን ለማግኘት [email protected] አድራሻ መጠቀም ይቻላል።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



